ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በባሕሬን የሚያደርጉት ጉብኝት የሰላም እና የውይይት ነው ተባለ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በባሕሬን የሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት አጭር ቢሆንም ከልዩ ልዩ ባለ ሥልጣናት ጋር ተገናኝተው ጠንካራ መልዕክቶችን የሚያስተላልፉበት እንደሆነ ታውቋል። በጥቅምት ወር መጨረሻ አካባቢ የሚያደርጉት ይህ ሐዋርያዊ ጉብኝት 39ኛው ዓለም አቀፍ ጉብኝት እንደሚሆን ታውቋል። “በምድርም በጎ ፈቃድ ላላቸው ሰዎች ሁሉ ሰላም ይሁን” የሚለው የሐዋርያዊ ጉብኝታቸው መሪ ቃል በጦርነት እና በመከፋፈል በቆሰለው ዓለም ውስጥ ወቅታዊ መልዕክት እንደሚያስተላልፍ ታውቋል። የመላዋ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ባሕሬንን ሲጎበኙ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የመጀመሪያው እንደሚሆኑ ታውቋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በባሕሬን በሚያደርጉት የሐዋርያዊ ጉብኝት ቀናት ውስጥ ማናማን እና አዋሊ ከተሞችን የሚጎበኟቸው ሲሆን፣ “የምሥራቁ እና የምዕራቡ ዓለም ለሰው ልጆች አብሮ መኖር” በሚል ርዕሥ በሚዘጋጀው የውይይት መድረክ ላይ ቅዱስነታቸው እንደሚገኙ ይጠበቃል።
ቅዱስነታቸው ከእገሪቱ ንጉሥ ጋርም ይገናኛሉ
ሐሙስ ጥቅምት 3/2015 ዓ. ም. በሮም የሰዓት አቆጣጠር ከጠዋቱ 3፡30 ላይ ከሮም አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ፊውሚቺኖ ተነስተው በመሃል ባሕሬን ግዛት ወደ ምትገኘው አዋሊ ከተማ እንደሚያቀኑ የጉብኝታቸው መርሃ ግብር አመልክቷል። የቅድስት መንበር ጋዜጣዊ መግለጫ ክፍል መስከረም 26/2015 ዓ. ም. ይፋ ባደረገው መርሃ ግብር መሠረት ቅዱስነታቸው በአካባቢው የሰዓት አቆጣጠር ከሰዓት 10፡45 ላይ ወደ ሳኪር አየር ማረፊያ ሲደርሱ ኦፊሴላዊ አቀባበል እንደሚደረግላቸው ታውቋል።
ቅዱስነታቸው በመቀጠልም በ11፡30 ላይ እ. አ. አ በታኅሳስ 10/2021 ዓ. ም በአረቡ ዓለም የፋርስ ባሕረ ሰላጤ ጠባቂ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ካቴድራል ምስረታ ምክንያት በማድረግ ብፁዕ ካርዲናል ሉዊስ አንቶኒዮ ታግሌ የቅዱስነታቸውን መልዕክት ያቀረቡላቸውን የባሕሬን ንጉሥ ሃማድ ቢን ኢሳ አል ካሊፋን እንደሚጎበኟቸው ታውቋል። ንጉሡ ለቅዱስነታቸው በሰጡት ምላሽ "አንድ ቀን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳትን በባሕሬን ለማየት ታላቅ ፍላጎት አለኝ” ማለታቸው ይታወሳል። በዚህም መሠረት ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በሳኪር ንጉሣዊ ቤተ መንግሥት ውስጥ በሚደረገው ሥነ-ሥርዓት ላይ ተገኝተው ከከፍተኛ የመንግሥት ተካዮች እና ባለሥልጣናት ጋር እንዲሁም የሲቪል ማኅበረሰብ ተወካዮች እና ዲፕሎማሲያዊ አካላት ጋር ተገናኝተው ከአምስቱ ንግግሮች መካከል የመጀመሪያ አቅርበው የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት እንደሚያቀርቡ ታውቋል።
ከአብያተ ክርስቲያናት መሪዎች ጋር ሆነው የሰላም ጸሎት ያቀርባሉ
ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ዓርብ ጥቅምት 25/2015 ዓ. ም. ከረፋዱ አራት ሰዓት ላይ በሳኪር ንጉሣዊ ቤተ መንግሥት ውስጥ በአል-ፊዳ አደባባይ በተዘጋጀ "የባሕሬን የውይይት መድረክ" መዝጊያ ሥነ ሥርዓት ላይ እንደሚገኙ ታውቋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በዚሁ ዕለትም ንግግር የሚያደርጉ ሲሆን ከሰዓት በኋላ በአሥር ሰዓት ላይ ወዳጃቸው ከሆኑት ታላቁ ኢማም አል-አዝሃር አህመድ አል-ጣይብ ጋር በግል የሚገናኙ ሲሆን፣ በቅርቡ በካዛኪስታን በተካሄደው የዓለም ሃይማኖቶች እና ባሕላዊ እምነቶች መሪዎች ስብሰባ ወቅት ጨምሮ በሌሎች አጋጣሚዎችም መገናኘታቸው ይታወሳል።
የጋራ ውይይቱ ከቀኑ አሥር ሰዓት ገደማ በ “ሳኪር ንጉሣዊ ቤተ መንግሥት” አካባቢ በሚገኘው ጳጳስ መኖሪያ ውስጥ እንደሚደረግ ታውቋል። ቀጥሎም ከሰዓት አሥር ሰዓት ተኩል ገደማ ከ “ሙስሊም ሽማግሌዎች ምክር ቤት” አባላት ጋር በሳኪር ንጉሣዊ ቤተ መንግሥት ግቢ በሚገኝ መስጊድ ውስጥ ለመገናኘት አዲስ ቀጠሮ እንደሚያዝ ታውቋል። በዚህ አጋጣሚም ቅዱስነታቸው ንግግር እንደሚያደርጉ ታቅዷል። በመጨረሻም ር. ሊ. ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በአረቡ ዓለም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ካቴድራል ውስጥ በሚደረገው የአብያተ ክርስቲያናት ስብሰባ እና የሰላም ጸሎት ሥነ ሥርዓት ላይ እንደሚገኙ ታውቋል።
በአዋሊ ከተማ በሚገኝ የ "ባሕሬን ብሔራዊ ስታዲዬም" ውስጥ፣ የቅዱስነታቸው ሦስተኛ የጉብኝት ቀን በሚሆነው ቅዳሜ ጥቅምት 26/2015 ዓ. ም. ከጠዋቱ ሁለት ሰዓት ተኩል ላይ የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ሥነ-ሥርዓት የሚፈጸም መሆኑ ታውቋል። ቅዱስነታቸው ቀጥለውም ከሰዓት በኋላ በአሥራ አንድ ሰዓት ላይ በቅዱስ ልበ ኢየሱስ ትምህርት ቤት ቅጥር ግቢ ከወጣቶች ጋርም እንደሚገናኙ ታውቋል።
በዋና ከተማው ማናማ
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ባሕሬንን ከመሰናበታቸው በፊት እሑድ ጥቅምት 27/2015 ዓ. ም. የቀድሞ ዋና ከተማዋን ማናማን እንደሚጎበኙ ታውቋል። ከመላው የሀገሪቱ ህዝብ መካከል አንድ አራተኛው በሚኖርባት በማናማ ከተማ ውስጥ ቅዱስነታቸው ከብጹዓን ጳጳሳት፣ ከካህናት፣ ገዳማውያን እና ገዳማውያት፣ የዘርዓ ክህነት ተማሪዎች፣ የሐዋርያዊ አገልግሎት ተባባሪዎች እና መላው ምዕመናን ጋር በቅዱስ ልበ ኢየሱስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የኅብረት ጸሎት ካደረሱ በኋላ የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎትን እንደሚያቀርቡ ታውቋል። ከዚያም ወደ አዋሊ ከተማ ተመልሰው በአገሩ የሰዓት አቆጣጠር ስድስት ሰዓት ተኩል ላይ የስንብት ሥነ-ሥርዓቱ በ "ሳኪር አየር ማረፊያ" ውስጥ እንደሚከናወን ታቅዷል። ከቀኑ ሰባት ሰዓት ላይ ከአውሮፕላን ማረፊያ ተነስተው በሮም የሰዓት አቆጣጠር ከሰዓት በኋላ ወደ አሥራ አንድ ሰዓት አካባቢ ወደ ሮም ፊውሚቺኖ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ እንደሚደርሱ የሐዋርያዊ ጉብኝታቸው መርሃ ግብር ያመለክታል።
የመሪ ቃል እና የዓርማ ዝግጅት
የቅድስት መንበር ጋዜጣዊ መግለጫ ክፍል፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ወደ ባሕሬን ከሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት መርሃ ግብር በተጨማሪ፣ የጉብኝታቸውን መሪ ቃል እና አርማ ይፋማድረጉ ታውቋል። መሪ ቃሉ፣ በሉቃ. 2:14 ላይ እንደተጠቀሰው፣ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ልደት መላዕክት፣ “በምድርም በጎ ፈቃድ ላላቸው ሰዎች ሁሉ ሰላም ይሁን” በማለት የዘመሩት መሆኑን መግለጫ ክፍሉ አስታውቋል። በሌላ በኩል ዓርማው የባሕሬን መንግሥት እና የቅድስት መንበር ሰንደቅ ዓላማዎችን የያዘ ሲሆን፣ ትርጉሙም ለእግዚአብሔር የተከፈቱ ሁለት እጆችን፣ እንዲሁም ሕዝቦች እና አገራት በግልጽ መንፈስ ያለ አድልዎ እንደ ወንድም እና እህት እርስ በርስ ለመገናኘት ያላቸውን ቁርጠኝነት የሚገልጽ መሆኑ ተመልክቷል። የወንድማማችነት ግንኙነት ፍሬ የሰላም ስጦታ፣ በሁለት እጆች መሃል በሚታይ የወይራ ቅርንጫፍ መመሰሉ ተመልክቷል። “ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ” የሚለው ጽሁፍ በሰማያዊ ቀለም የተፃፈው ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው፣ “የአረቡ ዓለም እመቤታችን” በሚል ስያሜ ለምትከበር እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት አደራ የተጣለበት መሆኑን የሚገልጽ ሲሆን፣ ተመሳሳይ ስም በባሕሬን በታነጸው የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ካቴድራል ውስጥ እንደሚገኝ ታውቋል።