ፈልግ

በተለያዩ በሽታ ለሚሰቃዩ ሕሙማን ዕርዳታ የሚያደጉ ማኅበራት ተወካዮችን በቫቲካን ተቀብለው ሰላምታቸውን አቅርበውላቸዋል በተለያዩ በሽታ ለሚሰቃዩ ሕሙማን ዕርዳታ የሚያደጉ ማኅበራት ተወካዮችን በቫቲካን ተቀብለው ሰላምታቸውን አቅርበውላቸዋል  

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ የአልዛይመር በሽታ ያለባቸውን ሰዎች በጸሎት እንድናግዛቸው አሳሰቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ረቡዕ መስከረም 11/2015 ዓ. ም. የተከበረውን ዓለም አቀፍ የአልዛይመር ቀን በማስታወስ፣ ሳምንታዊ የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮአቸውን ለመከታተል በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተገኙት ምዕመናን መልዕክት አስተላልፈዋል። ቅዱስነታቸው ለታዳሚዎቹ ባስተላለፉት መልዕክት፣ በበሽታው ለሚሰቃዩት ሰዎች እንድንጸልይላቸው እና ለሚንከባከቧቸው ቤተሰቦችም ድጋፍ እንድናደርግላቸው ጠይቀዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ቅዱስነታቸው በሳምንታዊ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮአቸው ማጠቃለያ ላይ ባሰሙት ንግግር በዓመቱ መስከረም 11 በአልዛይመር በሽታ የሚሰቃዩ ሰዎች የሚታሰቡበት ዓለም አቀፍ ቀን መሆኑን አስታውሰው፣ በሽታው በርካታ ሰዎችን እንደሚያጠቃ እና በችግር ይበልጥ የሚጎዱት በሕመሙ ምክንያት ከማኅበረሰቡ እንዲገለሉ የሚደረጉ መሆናቸው አስረድተው፣ በበሽታው ለሚሰቃዩት፣ ለቤተሰቦቻቸው እና በፍቅር ለሚንከባከቧቸው ሰዎች የበለጠ ድጋፍ እና ዕርዳታ እንዲያገኝ በጸሎት ልናግዛቸው ይገባል ብለዋል።

ቅዱስነታቸው ከማሳሰቢያቸው በተጨማሪ፣ በአደባባዩ የተገኙ የኩላሊት እጥበት እና የአካል ክፍል ንቅለ ተከላ ለሚያደርጉ ማኅበራት ተወካዮች ሰላምታቸውን አቅርበው፣ በጸሎታቸውም እንደሚያግዟቸው አረጋግጠውላቸዋል። ዓለም አቀፍ የአልዛይመር ቀን የሚከበረው በመስከረም ወር እንደሆነ እና ወሩም አልዛይመር በሽታ የሚታወስበት ወር መሆኑ ይታወቃል።

በዓለም ዙሪያ ስለ በሽታው ኅብረተሰቡ ግንዛቤ እንዲኖረው ለማሳድረግ እና በበሽታው ምክንያት በሕሙማኑ ላይ የሚደረግ ማገለልን ለመቃወም ሰፊ ዘመቻ እየተደረገ መሆኑ ታውቋል። ዋና ግቡ ሕዝቡ የተሻለ ግንዛቤ እንዲኖረው ማድረግ፣ የአመለካከት ለውጦችን ለማምጣት እና በሕመሙ የሚሰቃዩትን እና እነርሱን ለመንከባከብ ጥረት የሚያደርጉ ቤተሰቦችን ለመርዳት እና የላቀ ዕርዳታን ለማሰባሰብ እንደሆነ ታውቋል።

ዘንድሮ የተካሄደው ዘመቻ ጥረት ስለ አልዛይመር በሽታ የሚደረግ ምርምር ተከትሎ የበሽታው ተጠቂዎችን እና ቤተሰቦችን እንዴት መደገፍ እንደሚቻል፣ ልዩ ትኩረት እየሰጡ ዘመናዊ ሕክምናዎችን የሚያገኙበትን መንገድ ማመቻቸት እና በቂ ዕርዳታን ለማሰባሰብ መሆኑ ታውቋል።

የዓለም ጤና ድርጅት እንደገለጸው በዓለም ዙሪያ ከ 55 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ከባድ የመርሳት ችግር እንዳለባቸው፣ በየዓመቱ ወደ 10 ሚሊዮን የሚጠጉ በሽታው የጠናባቸው አዳዲስ ሕሙማን እንደሚመዘገቡ አስታውቋል። የአልዛይመር በሽታ በዓለማችን ውስጥ በስፋት የሚከሰት የመርሳት በሽታ ሲሆን፣ በበሽታው የሚጠቁትም ከ60-70% እንደሚገመቱ የገለጸው የዓለም ጤና ድርጅት ሪፖርቱ፣ የአልዛይመር በሽታ ሰዎችን ለሞት ከሚዳርጉ ሌሎች በሽታዎች መካከል በሰባተኛ ደረጃ የተቀመጠ መሆኑን አስረድቷል።

22 September 2022, 16:56