ፈልግ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በካዛኪስታን መዲና ኑር-ሱልጣን ሐዋርያዊ ጉብኝት አድርገዋል ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በካዛኪስታን መዲና ኑር-ሱልጣን ሐዋርያዊ ጉብኝት አድርገዋል 

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ለካዛኪስታን ሰላም እና አንድነት የእግዚአብሔርን ቡራኬ ለምነዋል

በካዛኪስታን መዲና ኑር-ሱልጣን የዓለም ሃይማኖቶች እና ባሕላዊ እምነቶች መሪዎች ጉባኤን ከመስከረም 3 – 5/2015 ዓ. ም ድረስ ተካፍለው የተመለሱት ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ በዚያች አገር የተደረገላቸውን ደማቅ አቀባበል እና መልካም መስተንግዶን በማስታወስ ለአገሪቱ ፕሬዚዳንት ለክቡር አቶ ቶካዬቭ የምስጋና መልዕክት ልከዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የዓለም ሃይማኖቶች እና ባህላው እምነቶች መሪዎች ጉባኤ ከተጠናቀቀ በኋላ ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ወደ አውሮፕላን ማረፊያ በመሄድ ጉዞአቸውን ወደ ሮም አቅንተዋል። ጉባኤው የተጠናቀቀው የመጨረሻ መግለጫ ከተነበበ በኋላ ሲሆን፣ የጉባኤው ጠቅላላ ሰነዱ ለዓለም ሰላምና አብሮ በጋራ የመኖር ጠቀሜታ የተረጋገጠበት መሆኑ ታውቋል። ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ወደ ሮም ከማቅናታቸው በፊት በአውሮፕላን ማረፊያ በተዘጋጀላቸው የእንግዳ መቀበያ ውስጥ ከካዛኪስታን ፕሬዝዳንት ክቡር አቶ ካሲም ዮማርት ቶካዬቭ ጋር አጭር የግል ውይይት ማድረጋቸው ታውቋል።

በሥነ ሥርዓቱ ላይ የካዛኪስታን ርዕሰ መስተዳድር ክቡር አቶ ካሲም ዮማርት ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በንግግራቸው ላይ የጠቀሱትን የካዛኪስታን ባሕላዊ የሙዚቃ መሣሪያን በስጦታ አበርክተውላቸዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከአገሪቱ የክብር ዘብ እና ከፍተኛ ልዑካን ሰላምታ ከቀረበላቸው በኋላ ጉዞአቸውን ወደ ጣሊያን አድርገው ወደ ሮም በሰላም ተመልሰዋል። ቅዱስነታቸው ወደ ሮም ባደረጉት ጉዞ ወቅት ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡ ሲሆን ወደ 80 ከሚጠጉ እና አብረዋቸው ከተጓዙት ጋዜጠኞች ለቀረቡላቸው ጥያቄውች ምላሽ ሰጥተዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከካዛኪስታን ከተነሱ በኋላ @Pontifex በሚለው የትዊተር ገፃቸው በኩል የካዛኪስታኑ ፕሬዝዳንት ክቡር አቶ ካሲም ዮማርት ቶካዬቭ እና መላው የእስያ አህጉር ሕዝብ ምስጋናቸውን አቅርበው፣ ለተደረገላቸው ደማቅ አቀባበል እና ከበርካታ የዓለም ሃይማኖቶች እና ባሕላዊ እምነቶች መሪዎች ጋር የወንድማማችነት ውይይቶች ለማድረግ ዕድል ስለተሰጣቸው ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

የሰላም ሐዋርያዊ ንግደት ነበር

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በመካከለኛው የእስያ አገር ካዛኪስታን ሐዋርያዊ ጉብኝት ከመጀመራቸው አስቀድመው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ከመሩት የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት በኋላ ባሰሙት ንግግር ወደ ካዛኪስታን የሚያደርጉት ጉዞ “የሰላም ንግደት” ነው በማለት መናገራቸው ይታወሳል። ቅዱስነታቸው በዓለም ሃይማኖቶች እና ባሕላዊ እምነቶች መሪዎች ጉባኤ ላይ እንደተናገሩት፣ “ሁከት እና ብጥብጥ በፍፁም ፍትሃዊ መሆን እንደሌለበት አፅንዖት ሰጥተው፣ የተቀደሰውን የእግዚአብሔር ስም ለክፉ ተግባር መሣሪያ እንዲሆን አንፍቀድ” ብለዋል። ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በካዛክስታን ለሃይማኖት መሪዎች ባሰሙት ንግግር፣ “የእርስ በእርስ ግንኙነት ምሳሌ” ተብሎ የተተረጎመው የሃይማኖት መሪዎች ጉባኤ በግጭቶች መካከል ሰላምን የሚፈጥር አዲስ የዕድገት መንገድ መሆኑን አስገንዝበዋል።

ቅዱስነታቸው ከኑር-ሱልጣን ወደ ሮም ተመልሰዋል

የካዛኪታን ሕዝብ መልካም አቀባበል እና ምስጋናን ይዘው የተመለሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ሰላም፣ የጋራ ውይይት እና ማንኛውንም ዓይነት ሁከት እና ብጥብጥ መቃወም፣ ቅዱስነታቸው ወደ እስያ አህጉር ያደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት ምልክቶች መሆናቸውን የቫቲካን ሬዲዮ ሓላፊ አቶ ማሲሚላኖ ሜኒኬቲ ከኑር ሱልጣን አውሮፕላን ማረፊያ ከመነሳታቸው በፊት በሰጡት አስተያየት ገልጸዋል።

17 September 2022, 18:25