ፈልግ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ወደ ካዛኪስታን የሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ወደ ካዛኪስታን የሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት 

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በካዛኪስታን የሚያደርጉትን 38ኛ ሐዋርያዊ ጉብኝት ጀመሩ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በካዛኪስታን የሚያደርጉትን የሦስት ቀናት ሐዋርያዊ ጉብኝት ማክሰኞ መስከረም 3/2015 ዓ. ም. ጀምረዋል። ከሮም-ፊዩሚቺኖ አውሮፕላን ጣቢያ አብረዋቸው ጉዞ ለጀመሩት ጋዜጠኞች መልካም የሥራ ጊዜን ተመኝተውላቸዋል። ለሐዋርያዊ ጉብኝታቸው በወጣው መርሃ ግብር መሠረት በሮም የሰዓት አቆጣጠር ከጠዋቱ አንድ ሰዓት ከሰላሳ ስድስት ደቂቃ ላይ ከፊዩሚቺኖ አየር ማረፊያ መነሳታቸው ታውቋል። ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ወደ ካዛኪስታን ያደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት ዋና ዓላማ በአገሪቱ መዲና ኑር-ሱልጣን ውስጥ ከመስከረም 3 - 5/2015 ዓ. ም. በሚካሄደው 7ኛው የዓለም ሃይማኖቶች እና ባሕላዊ እምነቶች መሪዎች ጉባኤ ላይ ለመገኘት እንደሆነ ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

እሑድ መስከረም 1/2015 ዓ. ም. በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ከተሰበሰቡት ምዕመና ጋር የመልዓከ እግዚአብሔር ጸሎት ካቀረቡ በኋላ ባደረጉት ንግግር፣ በካዛኪስታን የሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት ከዓለም ሐይማኖቶች እና ባሕላዊ እምነቶች መሪዎች እና ተወካዮች እንዲሁም በዓለማችን ሰላምን ለማስፈን የጋራ ፍላጎት ካላቸው ወንድሞች ጋር መገናኘቱ መልካም አጋጣሚን እንደሚፈጥርላቸው ገልጸው፣ ምዕመናኑ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን በጸሎት እንዲደግፉት አደራ ማለታቸው ይታወሳል። ቅዱስነታቸው

ቅዱስነታቸው በካዛኪስታን የሚያደርጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝት ጭብጥ በሚያብራራው አርማ ላይ እንደተመከተው፣ ከወይራ ቅጠል ጋር የሚታዩ ሁለቱ እጆች የሰላም እና የአንድነት መልዕክተኞችን የሚያመላክት ሲሆን፣ በሁለት ቋንቋዎች ማለትም በካዛኪስታን እና በሩሲያ ቋንቋዎች የተመለከተው ጽሑፍ “የሰላምና የአንድነት መልእክተኞች” የሚለውን የር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ሐዋርያዊ ጉብኝት መሪ ቃል የሚገልጽ መሆኑን የቅድስት መንበር ጋዜጣዊ መግለጫ ክፍሉ አስታውቋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቀድሞዋ የሶቪዬት ኅብረት ሪፓብሊክ በነበረች ካዛኪስታን ከመስከረም 3 - 5/2015 ዓ. ም. ድረስ የሚያደርጉትን 38ኛ ዓለም አቀፍ ሐዋርያዊ ጉብኝት ዛሬ ማለዳ ላይ መጀመራቸው ታውቋል።

የማዕከላዊ እስያ አገር የሆነች ካዛኪስታን ከሁለቱ አገራት ማለትም ከቻይና እና ከሩሲያ የተወረሱ የባሕል፣ የእምነት እና ልዩ ልዩ ጎሳዎች የሚገኙባት አገር መሆኗ ታውቋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በዚያች አገር የሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት፣ ልዩ ልዩ እምነቶች እና ሕዝቦች በመካከላቸው የሚፈጥሩትን መግባባት እና የሚያበረክቱትን አወንታዊ አስተዋፅዖ ለማረጋገጥ ሲሆን፣ በዚህ 7ኛው የዓለም ሃይማኖቶች እና ባሕላዊ እምነቶች መሪዎች እና ተወካዮች ጉባኤ ላይ መሳተፉ መልካም አጋጣሚ እንደሚሆን ተመልክቷል። ከዚህም በተጨማሪም ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በካዛኪስታን የሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት ሌላ ዓላማ ከካዛኪስታ 19 ሚሊዮን ነዋሪዎች መካከል አንድ ከመቶ የሚደርሰውን የአገሪቱን ካቶሊካዊ ማኅበረሰብን ለመገናኘት፣ ለማበረታታት እና እምነታቸውን ለማደስ መሆኑ ታውቋል።

ሐዋርያዊ ጉዞ አቸውን ከሮም ሲጀምሩ

በቫቲካን ውስጥ ከሚገኘው የብጹዓን ጳጳሳት መኖሪያ ቤት ከማለዳው አሥራ ሁለት ሰዓት ተኩል ገደማ ወጥተው ወደ ሮም-ፊዩሚቺኖ አውሮፕላን ጣቢያ ከደረሱ በኋላ በጣሊያን አየር መንገድ ኤርባስ A330፣ በሮም ሰዓት አቆጣጠር ከጠዋቱ አንድ ሰዓት ከሰላሳ ስድስት ደቂቃ ወደ ካዛኪታን ጉዞ መጀመራቸው ታውቋል። ስድስት ሰዓት ከሰላሳ ደቂቃ ከወሰደ ጉዞ በኋላ ቅዱስነታቸው በካዛኪስታን ዋና ከተማ ኑር-ሱልጣን ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ መድረሳቸው ታውቋል።

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ወደ ካዛኪስታን ባደረጉት በረራ የጣሊያን ፣ የክሮኤሺያ ፣ የቦስኒያ-ሄርዞጎቪና ፣ የሰርቢያ ፣ የሞንቴኔግሮ ፣ የቡልጋሪያ ፣ የቱርክ ፣ የጆርጂያ እና የአዘርባጃን የአየር ክልሎችን ያቋረጡ ሲሆን፣ ከሮም ፊዩሚቺኖ አውሮፕላን ጣቢያ ከመነሳታቸው በፊት ለጣሊያን ሪፓብሊክ ፕሬዝዳንት ለክቡር አቶ ሴርጂዮ ማታሬላ የቴሌግራም መልዕክት ልከዋል። ቅዱስነታቸው በዚህ መልዕክታቸው ለአገሪቱ ርዕሰ መስተዳድር እና ለመላው የጣሊያን ሕዝብ የአክብሮት ሰላምቸውን ልከውላቸዋል። ቅዱስነታቸው በማከልም ለአገሪቱ መልካም እና ዕድገትን ተመኝተው በጸሎት የሚያስታውሷቸው መሆኑን አረጋግጠውላቸዋል።

13 September 2022, 12:04