ፈልግ

አንቶኒ ጉይዶቲ አንቶኒ ጉይዶቲ 

የቅዱስ ፍራንችስኮስ መርሆዎች የሕዝቦችን የኑሮ አለመመጣጠን ሊያስተካክሉ እንደሚችሉ ተገለጸ

በጣሊያን አሲሲ ከተማ ከመስከረም 12-14/2015 ዓ. ም. ድረስ የሚካሄደው የር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች ስብሰባ በቅዱስ ፍራንችስኮስን እሴቶች እና መርሆዎች በመታገዝ በሕዝቦች የኑሮ አለመመጣጠን ዙሪያ ላይ ያሉ እውነታዎች በሚገባ ለመረዳት እንደሚያግዘው ከሰሜን አሜሪካ የመጣ አንድ የምጣኔ ሃብት ተመራማሪ ገልጿል። ወጣት አንቶኒ ጊዶቲ ከመስከረም 12-14/2015 ዓ. ም. በማዕከላዊ የጣሊያን ከተማ አሲሲ ውስጥ በመካሄድ ላይ የሚገኝ የር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች ስብሰባ ተካፋዮች መካከል አንዱ መሆኑ ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የኑሮ አለመመጣጠንን መዋጋት

ወጣት አንቶኒ ጉይዶቲ ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ፣ በአሲሲ ከተማ በመካሄድ ላይ የሚገኝ የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች ስብሰባ በርካታ የመወያያ ርዕሦች ያሉት፣ እያንዳንዱ ርዕሥ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩር መሆኑን ገልጾ፣ በምድቡ ከሌሎች የስብሰባው ተካፋዮች ጋር በመሆን የሚወያይበት የሕዝቦች የኑሮ አለመመጣጠን ርዕሠ ከዘላቂነት እና ከኢ-ፍትሃዊነት ጋር የተያያዘ ብቻ ሳይሆን ከኑሮ አለመመጣጠን ጋር ከተያያዙ በሁሉም የእኩልነት ጎራዎች ማለት ከዕድሎች፣ ከገንዘብ አቅም እና ከሥነ-ምህዳር ጋር የተያያዙ ርዕሠ ጉዳዮችንም የሚያካትት መሆኑን አስረድቷል።

ወጣት አንቶኒ ጥናታዊ ምርምሩን ያካሄደው የምጣኔ ሃብት በሚያስገኘው ክብር እና በማኅበረሰብ ሃብት ግንባታ ላይ ያተኮረ መሆኑን አስረድቶ በማከልም፣ ይፋ ለማድረግ የሞከራቸው ሃሳቦች ከፖሊሲ አውጪዎች ጋር በመተባበር በአካባቢ ደረጃ ባካሄደው ጥናት መሠረት የሰዎችን ሕይወት እንዴት ማሻሻል እና መቀየር እንደሚቻል ያየበት አካሄድ መሆኑን ተናግሯል። የምርምር ሥራውን እንዴት ተጨባጭ ማድረግ እንዳለበት ባያውቅም፣ ከሁሉ አስቀድሞ የመጀመሪያ ተግባሩ እሴቶችን እና መርሆዎችን ለይቶ ማውጣት እንደሚያስፈልግ ገልጾ፣ የሕዝብን ፖሊሲ ለማነፃፀር የሚረዳ መደበኛ መሠረት ከሌለን ሕዝባዊ ፖሊሲያችን ከጋራ ጥቅም ይልቅ ሃብታም የሆኑ ጥቂት ሰዎችን ብቻ የሚያገለግሉ እንደሚሆኑ አስጠንቅቋል። የምጣኔ ሃብት ባለሙያው ወጣት አንቶኒ ይህን ግምት ውስጥ በማስገባት፣ መደረግ ያለበት የመጀመሪያው ነገር የማኅበረሰብ እሴቶች እና መርሆዎች በትክክል ተናግሮ ውይይት የሚደረግበት መድረክ ማዘጋጀት እንደሚያስፈልግ እና ይህ ከተመቻቸ አብሮ መሥራት እንደሚቻል እና የሕዝብ ፖሊሲ ምን እንደሆነ ማወቅ የሚቻል መሆኑን አስረድቷል።

እሴቶች እና መርሆዎች

“እሴቶች እና መርሆዎች በተለይም እንደ አሲሲ ባሉ ቦታዎች ላይ በጣም ግልፅ ናቸው” ያለው ወጣት አንቶኒ፣ ከመላው ዓለም የመጡ በርካታ ሰዎች በአንድነት ሲሰባሰቡ ሁሉም ሰው በበኩሉ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ እንዳለ ተናግሮ፣ በአሲሲ እየተካሄደ ያለው ስብሰባ አስፈላጊ ገጽታ እና በተግባር ለመግለጽ እየተሞከረ ያለው ጥረትም ይህ መሆኑን አስረድቷል። “እንቅስቃሴው ዓለም አቀፋዊ ይዘት እንዲኖረው እንፈልጋለን” ያለው ወጣት አንቶኒ፣ ለውይይት ከምናመጣው ርዕሠ ጉዳይ በላይ ከተቀረው ዓለም ጋር ለውይይት ክፍት መሆን እና ማድመጥ እንደሚያስፈልግ አሳስቧል። ከሰሜን አሜሪካ በመምጣት በአሲሲ ከተማ በማካሄድ ላይ የሚገኝ ስብሰባን በመካፈል ላይ የሚገኝ ወጣት አንቶኒ፣ ስለ ሕዝቦች የኑሮ አለመመጣጠን እና ስለ ትክክለኛ የሕዝብ ፖሊሲ መማር የሚችለው ከተለያዩ አገራት ከመጡ የምጣኔ ሃብት ባለሙያ ጓደኞቹ ጋር በመተባበር፣ በመደማመጥ እና እርስ በእርስ በመተሳሰር መሆኑን አስታውቋል። 

ከር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ጋር ለመገናኘት ያለው ጉጉት

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በጣሊያን አሲሲ ከተማ ከመስከረም 12 ጀምሮ በመካሄድ ላይ በሚገኝ የር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች ስብሰባ የመጨረሻ ቀን ላይ ለመገኘት ቅዳሜ መስከረም 14/2015 ዓ. ም. ወደ አሲሲ እንደሚጓዙ ታውቋል። በዕለቱ ከር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ጋር ለመገናኘት ከፍተኛ ጉጉት እንዳለው የገለጸው ወጣት አንቶኒ፣ ቅዱስነታቸው በዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ የሚሰጡትን አመራር በቀዳሚነት ለመቀበል ዕድል በማግኘቱ የተሰማውን ደስታ ገልጿል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ "የማዳመጥን እና የመቀበልን እሴቶች የሚያሳዩ" መሆናቸው የተናገረው ወጣት አንቶኒ፣ በስብሰባው ላይ በተካተቱ ርዕሠ ጉዳዮች ላይ የቅዱስነታቸው አመራር እጅግ አስፈላጊ እንደሆነ እምነቱን ገልጾ፣ በዘመናዊው ዓለም ስለ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ስናስብ፣ የዛሬዎቹን ተግዳሮቶች እንዴት አስተናግደን የወደ ፊት ሃላፊነታችንን እንዴት መወጣት እንዳለብን ጠቃሚ ምክሮችን ማግኘት እንደሚቻል ወጣት አንቶኒ ለቫቲካን የዜና አገልግሎት አስረድቷል።

22 September 2022, 17:14