ፈልግ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በሳምንታዊ የጠቅላላ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ወቅት ሕጻናትን ሲቀበሉ  ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በሳምንታዊ የጠቅላላ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ወቅት ሕጻናትን ሲቀበሉ  

የዩክሬን ፕሬዚደንት ዜለኒስኪ ለር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ምስጋና አቀረቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳ ፍራንችስኮስ ዓርብ ነሐሴ 6/2014 ዓ. ም. ከዩክሬኑ ፕሬዝደንት ከአቶ ቮሎድሚር ዜለኒስኪ ጋር የስልክ መልዕክት ተለዋውጠዋል። የዩክሬን ፕሬዝዳንት ዘሌኒስኪ ለር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በላኩት የትዊተር መልዕክት በዩክሬን ሕዝብ ላይ እየተፈጸመ ስላለው ወረራ አብራርተው፣ ቅዱስነታቸው የዩክሬንን ሕዝብ በጸሎት ማስታወሳቸውን በመግለጽ ምስጋናቸውን አቅርበውላቸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ እና በፕሬዝደንት ዜለኒስኪ መካከል የተደረገው የስልክ ውይይት በዩክሬን ጦርነቱ ከተጀመረ ከስድስት ወር በኋላ መሆኑ ታውቋል። በሁለቱ መካከል የተደረገው ውይይት ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ከዚህ በፊት ለመላው የዩክሬን ሕዝብ ያላቸውን ወዳጅነት ከገለጹባቸው መንገዶች መካከል አንዱ መሆኑ ታውቋል። ፕሬዝደንት ዜለንስኪ በትዊተር ገፃቸው በኩል እንደገለጹት፣ ሩሲያ ዩክሬንን ከወረረችበት ከየካቲት 17/2014 ዓ. ም. ጀምሮ በሕዝቡ ላይ እያደረሰ ያለውን አሰቃቂ አደጋን ገልጸው፣ በእነዚህ የመከራ ጊዜያት ቅዱስነታቸው የዩክሬንን ሕዝብ በጸሎታቸው በማስታወሳቸው ምስጋናቸውን አቅርበውላቸዋል። በቅድስት መንበር የዩክሬን አምባሳደር የሆኑት ክቡር አቶ አንድሪ ዩራሽ በትዊተር ገፃቸው ላይ ባሰፈሩት መልዕክት በር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ እና በዩክሬኑ ፕሬዝደንት በአቶ ዘሌኒስኪ መካከል የስልክ ውይይት መካሄዱን ገልጸው፣ መንግሥታቸው እና መላው የዩክሬን ሕዝብ ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስንን በዩክሬን ዋና ከተማ ኪዬቭ ሐዋርያዊ ጉብኝት የሚያደርጉ ከሆነ በክብር ተቀብለው ለማስተናገድ ደስተኞች መሆናቸውን ገልጸዋል።

ሌሎች ንግግሮች

ፕሬዝደንት ዜለኒስኪ መጋቢት 13/2014 ዓ. ም. ለጣሊያን ፓርላማ ባሰሙት የቪዲዮ ንግግር፣ ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ጠቃሚ ሃሳቦችን ማካፈላቸውን አስታውሰው፣ ሩሲያ ዩክሬንን ከወረረችበት ከሁለት ቀናት በኋላ ማለትም ከየካቲት 17/2014 ዓ. ም. በኋላ ከቅዱስነታቸው ጋር የስልክ መልዕክት መለዋወጣቸውን አስታውሰው በዚህ ውይይታቸው በአገሪቱ ውስጥ በሚታይ መከራ የተሰማቸውን ከፍተኛ ሐዘን መግለጻቸውን አስታውሰዋል። ፕሬዝደንት ዜለኒስኪ በዩክሬን ውስጥ ጦርነት ቆሞ ሰላም እንዲወርድ በማለት ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ለሚያደርጉት የጸሎት ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበው፣ የዩክሬን ሕዝብ የቅዱስነታቸው መንፈሳዊ ድጋፍ እንደሚሰማው ገልጸዋል።

የ. ር. ጳ ፍራንችስኮስ ጥሪዎች

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በሩሲያ እና በዩክሬን መካከል ጦርነቱ ከተቀስቀሰበት ከየካቲት 17/2014 ዓ. ም. ጀምሮ በተለያዩ አጋጣሚዎች የዩክሬንን ሕዝብ ሲያስታውሱ መቆየታቸው ታውቋል። ነሐሴ 4/2014 ዓ. ም. ባቀረቡት ሳምንታዊ የጠቅላላ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮአቸው በዩክሬን ውስጥ በመካሄድ ላይ የሚገኘው ጦርነት በሕዝቡ ላይ እያደረሰ ያለውን ስቃይ በማስታወስ እስከ ዛሬ በዚህ አሰቃቂ ጦርነት የሚሰቃዩትን በመጥቀስ በርካታ ሰዎች በመሰደድ ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በሩሲያ እና ዩክሬን መካከል የሚካሄደውን ጦርነት በማስመልከት ባለፉት ወራት ውስጥ ባስተላለፉት መልዕክት ጦርነቱ መቀጠል እንደሌለበት አሳስበው፣ ጎረቤት አገራቱ የጦርነቱ ሰለባ የሆኑትን ተቀብለው ከመርዳት ጀምሮ መልካምን ሁሉ ከማድረግ ወደ ኋላ እንዳይሉ ጥሪ ማቅረባቸው ይታወሳል።

13 August 2022, 16:28