ፈልግ

በኩባ ግዙፉ የነዳጅ ማጠራቀሚያ ላይ የደረሰ የእሳት አደጋ በኩባ ግዙፉ የነዳጅ ማጠራቀሚያ ላይ የደረሰ የእሳት አደጋ  

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በኩባ የነዳጅ ማከማቻ ላይ በደረሰው አደጋ የተጎዱን ሰዎች በጸሎት አስታወሱ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ኩባ ውስጥ በአንድ የነዳጅ ማከማቻ ላይ ዓርብ ሐምሌ 29/2014 ዓ. ም. በደረሰ ከፍተኛ የእሳት ቃጠሎ የተጎዱትን ሰዎች በጸሎታቸው አስታውሰዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ቅዱስነታቸው በሳምንቱ መጨረሻ በኩባ ማታንዛስ ወደብ በሚገኝ ግዙፍ የነዳጅ ማከማቻ ላይ በደረሰ ከፍተኛ የነዳጅ ዘይት ቃጠሎ ለተጎዱት ሰዎች እና ለመላው የኩባ ሕዝብ ያላቸውን ቅርበት ገልጸዋል። እሳቱ የተቀጣጠለው ዓርብ ምሽት በማታንዛስ በሚገኝ የነዳጅ ማጠራቀሚያ ላይ መብረቅ ከወደቀ በኋላ መሆኑ ታውቋል። እሳቱ ቅዳሜ ጧትም ወደ ሁለተኛው የነዳጅ ማጠራቀሚያ በመዛመት ተጨማሪ ፍንዳታዎችን ማስከተሉ ታውቋል።

እሑድ ነሐሴ 1/2014 ዓ. ም. ኩባ እሳቱን በቁጥጥር ሥር በማዋል አንዳንድ መሻሻሎችን ያሳየች ቢመስልም ከሌሎች አገራት በተላኩ ልዩ ቡድኖች በመታገዝ አደጋውን መቆጣጠር መቻሏ ታውቋል። በዜና ዘገባዎች መሠረት በእሳቱ ቢያንስ አንድ ሰው ሲሞት፣ 17 የእሳት አደጋ ተከላካዮች መጠፋታቸው እና 121 ሰዎች መቁሰላቸው ታውቋል።

የር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ የቴሌግራም መልዕክት

የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብፁዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን ለኩባ ካቶሊካዊ ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዝዳንት ለሆኑት ለብጹዕ አቡነ ኤሚሊዮ አራንጉረን የቅዱስነታቸውን ስሜት በመግለጽ ሰኞ ነሐሴ 2/2014 ዓ. ም. የቴሌግራም መልዕክት አስተላልፈዋል። በማታንዛስ ግዙፉ የነዳጅ ማጠራቀሚያ ላይ በደረሰ የእሳት አደጋ ቢያንስ የአንድ ሰው ሕይወት ማለፉን፣ በርካቶች መቁሰላቸውን ቅዱስነታቸው በሐዘን ተከታትለዋል።

ከዚህም በተጨማሪም ቅዱስነታቸው ለኩባ ሕዝብ ባላቸው መንፈሳዊ ቅርበት በአደጋው የተጎዱትን ቤተሰቦች አስታውሰው፣ በዚህ የሕመም ጊዜ እሳቱን ለማጥፋት እና የጠፉትን ለማግኘት በፍለጋ የተሰማሩትን እግዚአብሔር እንዲረዳቸው፣ የአደጋው ሰለባ ቤተሰቦችን በጸሎታቸው በማስታወስ፣ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በትንሳኤው የተስፋ ቃል መጽናናትን እንዲሰጣቸው በመለመን ሐዋርያዊ ቡራኬአቸውን ልከውላቸዋል።

09 August 2022, 16:35