ፈልግ

2022.06.06 ቅዱስነታቸው በጳጳሳዊ ምክር ቤት፣ የሐይማኖት ተቋማት የጋራ ውይይት አስተባባሪ ጽሕፈት ቤት ስብሰባ ተካፋዮችን ሲቀበሉ 2022.06.06 ቅዱስነታቸው በጳጳሳዊ ምክር ቤት፣ የሐይማኖት ተቋማት የጋራ ውይይት አስተባባሪ ጽሕፈት ቤት ስብሰባ ተካፋዮችን ሲቀበሉ   (Vatican Media)

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ በሃይማኖቶች መካከል የሚደረግ ውይይት ለሰላም ግንባታ ወሳኝ መሆኑ ገለጹ

በጳጳሳዊ ምክር ቤት፣ የሐይማኖት ተቋማት የጋራ ውይይት አስተባባሪ ጽሕፈት ቤት፣ ግንቦት 29/2014 ዓ. ም. ምልአተ ጉባኤውን አካሂዷል። ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ለጉባኤው ተካፋዮች ባስተላለፉት መልዕክት፣ የእምነት ታሪኮቻቸውን፣ የተከታዮቻቸውን ፍላጎቶች፣ ቁስሎች እና ሕልሞች ማሰብ እንደሚያስፈልግ አሳስበው፣ የሰው ሕይወት እና ንብረት እንዲጠፋ በሚያደርግ አመጽ እና ግዴለሽነት መካከል፣ ሁል ጊዜ በወንድማማችነት እየኖሩ እግዚአብሔርን ለማግኘት በሚደረግ ፍለጋ ውስጥ ዘወትር መልካም አማራጮች መኖራቸውን አስረድተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ዓለም አቀፍ ግንኙነቶች በፍጥነት እየተከናወኑ ባሉበት በዚህ ዘመን የጋራ ውይይት ወሳኝ መሆኑን፣ ውይይቱ በተለያዩ የእምነት ተቋማት መካከልም ሊደረግ እንደሚገባ፣ ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በቀለሜጦስ ሐዋርያዊ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ለተቀበሏቸው፣ የሐይማኖት ተቋማት የጋራ ውይይት አስተባባሪ ጽሕፈት ቤት ስብሰባ ተካፋዮች ገልጸዋል። የጋራ ውይይት አስተባባሪ ጽሕፈት ቤቱ፣ ክርስቲያን ያልሆኑ የእምነት ተቋማትን ጨምሮ በሌሎች ሃይማኖቶች ተከታዮች፣ በተለያዩ ባህሎች ፣ ቋንቋዎች እና ማኅበረሰቦች መካከል ያለው ግንኙነት ጉልህ እድገትን እንዲያሳይ የሚረዳ ጽሕፈት ቤት እንደሆነ የቀድሞ ር. ሊ. ጳ ቅዱስ ጳውሎስ 6ኛ እ. አ. አ  በ 1964 ዓ. ም. ማስገንዘባቸው ይታወሳል። 

የውይይት አስተባባሪው ጽ/ቤት ተልዕኮ

“ዛሬ የሃይማኖቶች ውይይቶች በተግባር፣ በሥነ-መለኮት ልውውጥ እና በመንፈሳዊ ልምድ ተጨባጭ መሆን እንዳለባቸው እንገነዘባለን” ያሉት ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ በጳጳሳዊ ምክር ቤት፣ የሐይማኖት ተቋማት የጋራ ውይይት አስተባባሪ ጽሕፈት ቤት ዋና ተግባር “እግዚአብሔርን በሰዎች መካከል መፈለግን” ማስተማር መሆኑን አስረድተዋል። ቅዱስነታቸው በማከልም፣ የጳጳሳዊ ምክር ቤቱ ተልእኮ ከሌሎች አማኞች ጋር በወንድማማችነት እና በታማኝነት እግዚአብሔርን የመፈለግ መንገድ ማስተዋወቅ፣ በረቂቅ መንገድ ሳይሆን በተጨባጭ መንገድ ታሪካቸውን፣ ምኞታቸውን፣ ያለፈው ቁስሎቻቸውን እና ህልማቸውንም በመረዳት የልዩ ልዩ እምነቶች ተከታዮችን ማስገንዘብ መሆኑን ገልጸዋል።

ውይይት ማድረግ ሁሌም ይቻላል

"ሁሉም ሰው በሰላም የሚኖርባትን ዓለም መገንባት የሚቻለው በጋራ ውይይት ነው" ያሉት ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ ተከታታይ ቀውሶች እና ግጭቶች ሲያጋጥሙ አንዳንድ ሰዎች ራሳቸውን በመሸሸግ ከእውነታው ለማምለጥ እንደሚሞክሩ እና ሌሎች ደግሞ ጥቃትን እንደሚጋፈጡ ገልጸው፣ ነገር ግን በራስ ወዳድነት፣ በግድ የለሽነት እና በኃይለኛ አመጽ እና ተቃውሞ መካከል ዘወትር አማራጮች መኖራቸውን አስረድተዋል።

የተሻለ ዓለምን ለመገንባት ልዩነቶችን ማስተናገድ

"ልዩነቶችን መቀበል ከሌሎች ጋር ወደ ፊት አስደሳች ሕይወትን እንድናስብ እና እንድንገነባ ያግዛል” ያሉት ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፣ ሰዎች እርስ በእርሱ የሚያደርጓቸው ውይይቶች፣  በእያንዳንዱ ሰው ልብ ውስጥ የኅብረት እና የአንድነት ፍላጎት መኖሩን፣ ሃሳብን የመለዋወጥ እና ወደ ፊት አብሮ የመኖር ምኞትን ያስረዳል” በማለት ምስጋናቸውን አቅርበዋል። ልዩነቶችን ተቀብሎ በጋራ መኖር ማኅበራዊነትን እንደሚያሳድግ የገለጹ ቅዱስነታቸው፣ አብሮ መኖር ማለት ሌላውን ሳይጫኑ ሰብዓዊ ማንነትን ጠብቆ እና አክብሮ መኖርን እንደሚጠይቅ ገልጸው፣ ከዚህ አንፃር ልዩነቶችን ተቀብሎ ማስተናገድ፣ መበታተንን እና ግጭቶችን የማስወገድ ፖለቲካዊ አማራጭ ጠቀሜታ እንዳለው አስረድተዋል።

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ በጳጳሳዊ ምክር ቤት የሐይማኖት ተቋማት የጋራ ውይይት አስተባባሪ ጽሕፈት ቤት ያዘጋጀውን ስብሰባ ለተካፈሉት አባላት ባሰሙት የማበረታቻ ንግግር፣ “ኢየሱስ ክርስቶስ ከኃጢአተኞች እና ከክፉዎች ጋር መተባበሩን፣ ከቀራጮች እና ከሁሉ ዓይነት ሰዎች ጋር ያለውን ወዳጅነቱ አጽንቷል” ብለው፣ ወዳጅነቱን እና አንድነቱን የገለጸላቸው ሁል ጊዜ እራሱን እንደ አገልጋይ እና ታማኝ ጓደኛ በማሳየት እንደሆነ ገልጸው፣ በትንሣኤው ከሁሉም ጋር አብሮ የመኖር ጸጋን ሰጥቶናል” ብለዋል።

የሐይማኖት ተቋማት የጋራ ውይይት አስተባባሪ ጽሕፈት ቤት ስብሰባ

በጳጳሳዊ ምክር ቤት፣ የሐይማኖት ተቋማት የጋራ ውይይት አስተባባሪ ጽሕፈት ቤት አባላት እና የአማካሪዎቻቸው ስብሰባ ከሰኞ ግንቦት 29 እስከ ሰኔ 1/2014 ዓ. ም. ድረስ የሚካሄድ ሲሆን፣ የስብሰባው መሪ ርዕስ “በሃይማኖቶች መካከል የሚደረግ ውይይት እና ዘላቂ አንድነት” የሚል እንደሆነ ታውቋል። በስብሰባው ወቅት ከተለያዩ አካባቢዎች የሚቀርቡ ሪፖርቶች የሚደመጡ ሲሆን በሪፖርቶቹ ላይ በማሰላሰል ሃሳብን የሚለዋወጡበት ጊዜ እንደሚኖር ታውቋል። ስብሰባው በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች እየተካሄደ ባለው የሐይማኖቶች ውይይቶች ወቅታዊ ሁኔታዎች ላይ በማሰላሰል፣ በልዩ ልዩ ሃይማኖታዊ ትውፊቶች መካከል ያለውን ወንድማማችነት በማሳደግ፣ የክርስቲያን ማኅበረሰብ ሚና ምን መሆን እንደሚገባ በመመልከት፣ እያንዳንዱ የእምነት ተቋም ለሰው ልጅ ጥቅም በማለት የበኩሉን አስተዋፅዖ እንዲያበረክት ለማድረግ መሆኑ ታውቋል። 

07 June 2022, 16:23