ፈልግ

የቅዱስ ቁርባን ቡራኬ ጸሎት የቅዱስ ቁርባን ቡራኬ ጸሎት  

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፥ “ቅዱስ ቁርባን እግዚአብሔርን በየቀኑ በሕይወታችን እንድናስገባው ይጋብዘናል!”

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ረቡዕ ሰኔ 8/2014 ዓ. ም. በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡት ምዕመናን ሳምንታዊ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምሮአቸውን አቅርበዋል። ለምዕመናኑ በዕለቱ ባስተላለፉት መልዕክት፣ ሰኔ 9/2014 ዓ. ም. የቅዱስ ቁርባን ዓመታዊ በዓል እንደሚከበር አስታውሰዋል። በዚህ መሠረት የጎርጎሮሳውያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ ካቶሊካዊ ምዕመናን ዘንድ ዛሬ ሰኔ 9/2014 ዓ. ም. የቅዱስ ቁርባን በዓል በታላቅ መንፈሳዊነት መከበሩ ታውቋል። ቅዱስነታቸው ሳምንታዊ አስተምህሮአቸውን ለመከታተል በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተገኙት ምዕመናን ባቀረቡት ስብከት፣ ቅዱስ ቁርባን ከእግዚአብሔር ጋር በየዕለቱ እንድንጓዝ እንደሚጋብዘን አስረድተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡት ምዕመናን ሰላምታቸውን ካቀረቡላቸው በኋላ ባቀረቡት ስብከት፣ እራስን ለአገልግሎት በማዘጋጀት፣ በተለይ በልዩ ልዩ ችግሮች ውስጥ ወድቀው ዕርዳታ የሚያስፈልጋቸውን በደስታ ማገልገል የምንችልበትን ኃይል እግዚአብሔር እንዲሰጠን በጸሎት መጠየቅ ያስፈልጋል ብለዋል። ሐሙስ ሰኔ 9/2014 ዓ. ም. የቅዱስ ቁርባን ዓመታዊ በዓል፣ በቫቲካን በሚገኘው ቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ውስጥ በቀረበው የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ተከብሯል። ከረፋዱ አራት ሰዓት ተኩል ላይ የተጀመረውን የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት የመሩት፣ በቫቲካን የቅዱስ ጴጥሮስ ባሲሊካ ሊቀ ጳጳስ እና የከተማው የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ረዳት አስተዳዳሪ ብፁዕ ካርዲናል ማውሮ ጋምቤቲ መሆናችው ታውቋል።

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ ቅዱስ ቁርባን የዕለት ተዕለት ሕይወታችንን ከእግዚአብሔር ጋር እንድንጓዝ፣ በደስታም ሆነ በችግር ወቅት ከእግዚአብሔር ጋር ለመሆን እንደሚጋብዘን አስረድተዋል። በመሆኑም ይህን ታላቅ መንፈሳዊ ስጦታን በመቀበል፣ የቅዱስ ቁርባን ሰዎች እንድንሆን፣ ከቅዱስ ቁርባን ለምንቀበለው ስጦታ አመስጋኞች እንድንሆን እና እራስን በደስታ ለአገልግሎት እንድናቀርብ፣ በተለይም ችግር ውስጥ የሚገኙትን መርዳት የምንችልበትን ኃይል ለማግኘት በጸሎት እግዚአብሔርን እንድንለምን አደራ ብለውናል።

ለኢየሱስ ሥጋ እና ደም የእግዚአብሔርን ፍቅር መለማመድ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ የጀርመን፣ የስፔን፣ የፖላድ እና የሌሎች አገራት ነጋዲያንን ጨምሮ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተገኙት ምዕመናን በሙሉ ባቀረቡት ስብከት፣ በእንጀራ እና በወይን ጠጅ መልክ የሚዘጋጀው ቅዱስ ቁርባን፣ እግዚአብሔር በቅዱስ ቁርባን ውስጥ በእውነት እንደሚገኝ ያስታውሰናል ብለዋል። የቅዱስ ቁርባን ዓመታዊ ክብረ በዓልን ምክንያት በማድረግ በፖላንድ የተካሄደው የስብከተ ወንጌል ኮንሰርት፣ የኢየሱስ ክርስቶስን ሥጋና ደም በመቀበል፣ ፍቅሩን በጥልቀት እንድንለማመድ እና እምነት በሁሉም ዘንድ እንዲቀሰቀስ የሚያደርግ መሆኑን ቅዱስነታቸው ተናግረዋል። ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በመጨረሻም፣ የኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ሥጋው እና ክቡር ደሙ ዓመታዊ በዓል በጣሊያን በሚገኙ ካቶሊካዊ ሀገረ ስብከቶች መጭው እሑድ ሰኔ 11/2014 ዓ. ም. እንደሚከበር አስታውሰው፣የእውነተኛ ፍቅር ምስጢር የሆነው ቅዱስ ቁርባን፣ ለሁላችንም ጸጋ እና የሕይወት መንገዳችንን የሚያበራ፣ በችግር ውስጥ ለሚገኙት ድጋፍ፣ ለሚያጋጥመን ሥቃይ ታላቅ መጽናኛ እንዲሆነን በመመኘት ስብከታቸውን ደምድመዋል።

16 June 2022, 15:37