ፈልግ

የኒውክለር ቦንብ በሂሮሽማ ከተማ ላይ በተጣለበት ወቅት የነበረው ፍንዳታ የኒውክለር ቦንብ በሂሮሽማ ከተማ ላይ በተጣለበት ወቅት የነበረው ፍንዳታ  

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ የኒውክሌር ጦር መሳሪያዎችን መጠቀም እና መያዝ ተገቢ አይደለም ማለታቸው ተገለጸ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በሚያዝያ 26/2014 ዓ.ም ከጃፓኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ጋር ባደረጉት የስልክ ንግግር የኒውክሌር ጦር መሳሪያዎችን መጠቀም እና መያዝ ሊታሰብ የሚገባው ጉዳይ ሊሆን አይገባውም ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ረቡዕ ማለዳ ከጃፓኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ጋር ባደረጉት ውይይት የኑክሌር ጦር መሳሪያ አጠቃቀምን እና ይዞታን ማስፋፋት ሙሉ በሙሉ የሚቃወመውን አቋማቸውን ደግመው ገልጸዋል።

የቅድስት መንበር የፕሬስ ጽህፈት ቤት ዳይሬክተር ማትዮ ብሩኒ እንዳሉት፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ፉሚዮ ኪሺዳ እና ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ለ25 ደቂቃ በፈጀው ውይይት የኒውክሌር ጦር መሣሪያዎችን መጠቀም እና መያዝ በራሱ ሊታሰብ የሚገባው ነገር አይደለም ብለዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ይህንን አስተያየት ሲሰጡ የመጀመሪያቸው አይደለም። እ.አ.አ በ2019 ዓ.ም በጃፓን ባደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት በሂሮሺማ የሰላም መታሰቢያ ሥፍራ ላይ ጸሎት አድርገው እንደነበርና ከቦምብ ጥቃት የተረፉ ሰዎችን ማግኘታቸውን በማስታወስ የኒውክሌር ጥቃት በሄሮሺማ ላይ የተፈጸመበትን 75ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ ለበዓሉ አዘጋጆች መልእክት ልከዋል።

"ሰላም እንዲሰፍን ሁሉም ሰዎች የጦር መሳሪያዎችን እና በተለይም በጣም ኃይለኛ እና አውዳሚ የሆነውን የጦር መሳሪያዎች ማለትም የኒውክሌር መሳሪያዎች ከተሞችን እና ሀገሮችን በሙሉ እንደሚያወድሙ ግልጽ ሆኖ ሊታወቅ ይገባል” ማለታቸው ተገልጿል።

በዚያ ጉብኝት ወቅት፣ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ የአቶሚክ የጦር መሣሪያዎችን መያዝ ወይም ማሰራጨት ሥነ ምግባር የጎደለው መሆኑን ገልጸው፣ እንዲወገዱም ደጋግመው ጠይቀው የኑክሌር ጦር መሣሪያ ክልከላ ስምምነትን እንደሚደግፉ መግለጻቸው ይታወሳል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ከኅዳር 09-16/2012 ዓ.ም ድረስ በታይላንድ እና በጃፓን በቅደም ተከተል ባደረጉት 32ኛው ሐዋርያዊ ጉብኝት አድርገው እንደ ነበረ የሚታወስ ሲሆን በጃፓን በነበራቸው ቆይታ የአቶሚክ ኃይልን ለጦርነት መጠቀምና ይህንን መሣሪያ ማከማቸት ሥነ ምግባር የጎደለው ተግባር ነው ማለታቸው ይታወሳል።

ቅዱስነታቸው በእዚያ በጃፓን በነበራቸው ቆይታ በሁለተኛ የዓለም ጦርነት ወቅት በኒውክለር የጦር መሣርያ ድብደባ ምክንያት ከፍተኛ ውድመት የደረሰባቸውን እና እጅግ በጣም ብዙ የሆኑ የሰው ልጆች ሕይወት የተቀጠፈበት አደጋ ተከስቶ የነበረባቸውን ኔጋሳኪ እና ሂሮስሺማን መጎብኘታቸው ይታወሳል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በጃፓን ያደረጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝት የጀመሩት ቀደም ሲል እንደ ተገለጸው በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ከፍተኛ ጉዳት ከደረሰባቸው ስፍራዎች አንዷ በሆነቺው ሄሮሽማ እንደ ነበረ የሚታወስ ሲሆን ቅዱስነታቸው በእዚያው “የሂሮሺማ የሰላም መታሰቢያ” በመባል በሚታወቀው የመታሰቢያ ስፍራ ለተገኘው ሕዝብ ባደርጉት ንግግር እንደ ገለጹት “የአቶሚክ ኃይልን ለጦርነት መጠቀምና ይህንን መሣሪያ ማከማቸት ሥነ ምግባር የጎደለው ተግባር ነው” በማለት በአጽኖት መናገራቸው ይታወሳል።

በጃፓን በነበራቸው የመጀመሪያው ቀን ሐዋርያዊ ጉብኝት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ “የሂሮሺማ የሰላም መታሰቢያ” ሥፍራን በጎበኙበት ወቅት ይህ “የሂሮሺማ የሰላም መታሰቢያ” ስፍራ ሞትና ሕይወት ፣ ኪሳራ እና ዳግም ልደት ፣ ሥቃይና ርህራሄ የተገናኙበት ስፍራ እንደሆነ” መግለጻቸው ይታወሳል። ለጦርነት ዓላማ አቶሚክ ኃይል መጠቀምና ማከማቸት በራሱ ሥነ-ምግባር የጎደለው ተግባር መሆኑን ከታሪክ መማር እንደ ሚቻል ቅዱስነታቸው ጨምረው ታንግረው ነበር።

እ.አ.አ በነሐሴ 6/1945 ዓ.ም 8፡15 ደቂቃ ላይ በሂሮሺማ ከተማ ላይ በተጣለው የመጀመሪያው አቶሚክ ቦንብ በወቅቱ ከተማይቱን ሙሉ በሙሉ እንድትወድም ማድርጉ የሚታወስ ሲሆን ከእዚህም ጋር በተያያዘ መልኩ በእዚህ አቶሚክ ቦንብ አማካይነት በቅጽበት ከ70 ሺህ በላይ ሰዎች ሕይወታቸው ማለፉ ይታወሳል፣ ከእዚያም በመቀጠል ደግሞ የአቶሚክ ቦንቡ ባደርሰው የጨረር አደጋ ቀስ በቀስ የ 70 ሺህ ሰዎችን ሕይወት መቅጠፉ ይታወሳል።

ከእዚህ ከተጣለው የአቶሚክ ቦንብ መሣርያ ፍንዳታ የተረፈው ብቸኛው ሕንፃ የጄንባኩ ዶም በመባል የሚታወቀው የፈረሰ ሕንጻ ሲሆን ይህ ሕንጻ በሰው ልጆች ላይ እና በአጠቃላይ በሰብዓዊነት ላይ ከፍተኛ ጉዳት እና ውድመት ያስከተለ እጅግ አስከፊ የሆነ አደጋ መሆኑን ለማስታወስ፣ ይህ ስፍራ ዛሬ በሂሮሺማ የሰላም መታሰቢያ ፓርክ እምብርት ላይ ቆሞ ይታያል።

የኑክሌር ጦርነት ሥነ ምግባር የጎደለው ነው

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በወቅቱ ባደረጉት ንግግር “የአቶሚክ ኃይልን ተጠቅሞ ጦርነት ማካሄድ ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ዛሬ፣ በሰው ልጆች ክብር ላይ ብቻ ሳይሆን ለወደፊቱ የጋራ መኖርያ ቤታችን በሆነች በምድራችን ላይ የሚፈጸም በደል ነው፣ የአቶሚክ ኃይል ለጦርነት መጠቀም ሥነ ምግባር የጎደለው ተግባር እንደመሆኑ መጠን፣ የአቶሚክ የጦር መሥርያ አምርቶ ማከማቸት በራሱ ሥነ ምግባር የጎደለው ተግባር ነው” በማለት መናገራቸው ይታወሳል። “ስለሰላም ብቻ በማውራት ሰላምን ግን በተጨባጭ በምድር ላይ በሚኖሩ ሕዝቦች መካከል ለማምጣት ባለመቻላችን ምጪው ትውልድ በእኛ ላይ እንደ ሚፈርድ” የገለጹ ሲሆን  አክለውም “ሰላም በእውነት ላይ የተመሠረተ ፣ በፍትህ የተገነባ ፣ በልግስና የተሟላ እና ነጻነትን የሚያስገኝ መሆን አለበት” ብለው ነበር።

በእጆቻችን ላይ የሚገኙ የኒውክለር የጦር መሣሪያዎችን እናስወግድ

“ይበልጡኑ ፍትሃዊ እና ደህንነቱ የተጠበቀ ማህበረሰብ መገንባት ከፈለግን በእጆቻችን ላይ የሚገኙትን የኒውክለር የጦር መሣሪያዎችን ማስወገድ ይኖርብናል” በማለት በወቅቱ የተናገሩት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ “ግጭቶችን ለመፍታት እና ለግጭቶች መፍትሄ ለመስጠት የኑውክሌር ጦርነት መሳሪያ ይህንን ስጋት ለመቀረፍ የሚያስችል  ሕጋዊ የሆነ መስመር ነው ብለን በማሰብ የኒውክሌር የጦር መሳሪያዎችን ለማጋበስ በምናደርገው ሩጫ የተነሳ እንዴት ሰላምን ማረጋገጥ እንችላለን?” በማለት ቅዱስነታቸው ጥያቄ ማንሳታቸው ይታወሳል። “እውነተኛ ሰላም የሚረጋገጠው የጦር መሳሪያዎችን በማስወገድ ብቻ አይደለም ፣ ምክንያቱም ሰላም ማለት የጦርነት አለመኖር ብቻ ማለት ስላልሆነ! በአንጻሩ ሰላም ማለት ከታሪክ እንደ ተማርነው እና እንደ ተረዳነው የፍትህ፣ የልማት፣ የአንድነት፣ የጋራ መኖሪያ ቤታችን የሆነችውን ምድራችንን መንከባከብ እና የጋራ ተጠቃሚነትን ማስፈን”  ሲቻል ቢቻ ነው በማለት አክለው መናገራቸው ይታወሳል።

እ.አ.አ በነሐሴ 6/1945 ዓ.ም 8፡15 ደቂቃ ላይ በሂሮሽማ ከተማ ላይ የተጣለው አቶሚክ ቦንብ ጥቃቱ  የሄሮሺማን ከተማ  ሙሉ በሙሉ እንድትወድም ማድርጉ የሚታወስ ሲሆን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በጃፓን አድርገውት በነበረው ሐዋርያዊ ጉብኝት ይህችን ከተማ መጎብኘታቸው ይታወሳል፣ “የሂሮሺማ የሰላም መታሰቢያ” ሥፍራን በጎበኙበት ወቅት ቀደም ሲል ያደረጉትን ንግግር ባጠቃለሉበት ወቅት ባቀረቡት መማጸኛ “በአቶሚክ ቦንብ ፍንዳታ እና ሙከራዎች፣ ግጭቶች ምክንያት ሰለባ በሆኑ ሰዎች ስም ሆነን ለእግዚአብሔር እና ለሁሉም መልካም እና በጎ ፈቃድ ያላችው ወንዶች እና ሴቶች ሁሉ፣ አንድ ድምጽ ሆነን፡ ከአሁን በኋላ ጦርነት ያብቃ፣ በጦር መሳሪያ የታገዙ ግጭቶች ያብቁ፣ በጭራሽ ከእዚህ የበለጠ መከራ እና ስቃይ በሰው ልጆች ላይ እንዳይደርስ እና የሰው ልጆች ስቃይ እንዲያበቃ” ለሁሉም ድምጼን አሰማለሁ ማለታቸው ይታወሳል።

04 May 2022, 11:53