ፈልግ

በብራዚል ውስጥ በወጣቶች የሚከናወን የቤተ ክርስቲያን ተልዕኮ በብራዚል ውስጥ በወጣቶች የሚከናወን የቤተ ክርስቲያን ተልዕኮ   (Arquivo POM Brasil)

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፥ “የወንጌል ተልዕኮን ለማሳካት እግዚአብሔርን መምሰል ያስፈልጋል!”

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በፈረንሳይ ሊዮን ከተማ ከሰኞ ግንቦት 8 - 15/2014 ዓ. ም. ድረስ ጠቅላላ ጉባኤያቸውን በማካሄድ ላይ ለሚገኙት ጳጳሳዊ የተልዕኮ አገልግሎት ማኅበር ተካፋዮች መልዕክት ልከዋል። ከዚህ ጋር በተያያዘ ዜና መጭው እሑድ ግንቦት 13/2014 ዓ. ም.፣ የማኅበሩ መሥራች የነበረች የፖሊን ጃሪኮ ብጽዕና አዋጅን፣ በቅድስት መንበር ለሕዝቦች የወንጌል አገልግሎት ማስፋፊያ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት አስተባባሪ፣ ብጹዕ ካርዲናል ሉዊስ አንቶኒዮ ታግለ በከተማው ተገኝተው ይፋ እንደሚያደርጉ ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ቤተ ክርስቲያን የአገልግሎት ተልዕኮ እንዳለባት ዘወትር የምትገልጽ የማኅበሩ መሥራች ፖሊን፣ የተጠመቀ ሁሉ ይህን አገልግሎት ለማበርከት የተጠራ መሆኑን ስትናገር መቆየቷ ታውቋል። ግንዛቤው እንዲኖር መርዳት ጳጳሳዊ የተልዕኮ ማኅበር የመጀመሪያ አገልግሎት መሆኑን ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ፣ የማኅበራቸውን ጠቅላላ ጉባኤ ከሰኞ ግንቦት 8 - 15/2014 ዓ. ም.  ድረስ በማካሄድ ላይ ለሚገኙ አባላት በላኩት መልዕክት አስታውቀዋል። ጠቅላላ ጉባኤውን በመካፈል ላይ የሚገኙት የብሔራዊ ማኅበር አለቆች ቁጥር 120 ገደማ ሲሆን፣ ጠቅላይ ሰብሳቢያቸው ብጹዕ አቡነ ጃምፔትሮ ማሆናቸው ታውቋል። ፖሊን ጃሪኮ ከ200 ዓመታት በፊት፣ ከአራቱ የተልዕኮ ማኅበር መካከል የእምነት ማስፋፊያ አገልግሎት ተብሎ የሚጠራውን ማኅበር መመሥረቷ ይታወሳል።

ፖሊን ጃሪኮ የቤተ ክርስቲያን ተልዕኮ እንቅስቃሴ መደገፍ  የጀመረችው በ23 ዓመት ዕድሜዋ መሆኑ ሲነገር፣
ከጥቂት ዓመታት በኋላ “ሕያው የመቁጠሪያ ጸሎት” የተባለ የጸሎት እና የመባ አቅርቦት እንቅስቃሴ መመሥረቱ ይታወሳል። ፖሊን ጃሪኮ፣ ከሀብታም ቤተሰብ ተወልዳ በድህነት ሕይወት መሞቷን የገለጹት ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ ቤተ ክርስቲያን በሰማይ ውድ ሀብት ማከማቸት የቻለችው መንፈሳዊ አገልግሎታቸውን በድፍረት ለማበርከት በሚነሱ የቤተ ክርስቲያን ልጆች በተግባር በገለጹት የሕይወት ምስጢር አማካይነት እንደሆነ አስረድተው፣ መያዝ የሚቻለው በመስጠት፣ እንደገና ማግኘት የሚቻለውም በማጣት ብቻ እንደሆነ አስረድተዋል።

እ. አ. አ በ2022 የሚከበሩ ክብረ በዓላት

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ የማኅበራቸውን ጠቅላላ ጉባኤ በመካፈል ላይ ለሚገኙት የብሔራዊ ማኅበር አለቆች በላኩት መልዕክት አክለውም፣ ዘንድሮ ጳጳሳዊ ማኅበር የሆነበት መቶኛ ዓመቱን የሚያከብረው የእምነት ማስፋፊያ አገልግሎት፣ ከሕጻንነት ቅድስና ማኅበር እና ከሐዋርያው ​​ቅዱስ ጴጥሮስ ማኅበር ጋር ሦስቱ በኅብረት ወደ ጳጳሳዊ ማኅበርነት ከፍ መደረጋቸውን አብስረዋል። እንዲሁም በዚህ ዓመት ጳጳሳዊ የተልዕኮ ማኅብራት ኅብረት መሥራች የነበሩ ብፁዕ አቡነ ፓውሎ ማና የተወለዱበት 150ኛ ዓመት እንደሚከበር ያስታወቁት ቅዱስነታቸው፣ ማኅበራቱ በኅብረት የሚያከብሩት በዓላት፣ የእምነት ማስፋፊያ አገልግሎት ማኅበር ምሥረታ 400ኛ ዓመት በዓል አካል መሆናቸውን ገልጸዋል።  ቅዱስነታቸው አክለውም የሐዋርያዊ ተልዕኮ ማኅበራት በቅርበት እንደሚሰሩ እና ማኅበራቱን ለማስተባበር አደራ ከተሰጠው የቅድስት መንበር ጳጳሳዊ ምክር ቤት ጋራ በመተባበር ቤተ ክርስቲያናትን ለመደገፍ እና ለማስተባበር የተቋቋሙ መሆናቸውን አስረድተዋል።

ቤተ ክርስቲያን እና የወንጌል አገልግሎት

"ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ወንጌልን ለእግዚአብሔር ሕዝብ መስብከን ፈጽሞ አታቁርጥም” ያሉት ቅዱስነታቸው፣ የቅዱስ ወንጌል ምሥክርነት ምንጊዜም የቤተ ክርስቲያን መሠረታዊ የአገልግሎት ጥሪ ሆኖ እንደሚኖር አጽንዖት ሰጥተዋል። በዚህም ምክንያት ቅዱስነታቸው በቅድስት መንበር ጳጳሳዊ ምክር ቤቶች ላይ ባደረጉት ማሻሻያ፣ ሐዋርያዊ የስብከተ ወንጌል መመሪያ ደንብን በማጽደቅ፣ በቅድስት መንበር ለሕዝቦች የወንጌል አገልግሎት ማስፋፊያ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት፣ በስብከተ ወንጌል አገልግሎት ልዩ ሚና እንዲጫወት ማድረጋቸው ይታወሳል። "የቤተ ክርስቲያን የተልዕኮ ሚናን ማዳበር ማለት፣ ምዕመናን ሐይማኖታቸውን እንዲለውጥ ማድረግ ሳይሆን፣ ወንጌልን በቆራጥነት እና በድፍረት መመስከር ማለት እንደሆነ፡ ከግለኝነት ወጥቶ የእግዚአብሔርን ነፃ እና አዳኝ ፍቅሩን በተግባር በመመስከር ወንድማማቾች እና እህትማማቾች ለመሆን የተጠራንበት ነው” በማለት አስረድተዋል።

ሚስዮናዊ ለውጥ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ለጉባኤው ተካፋዮች በላኩት መልዕክት ለመንፈስ ቅዱስ ሥራ ምስጋናቸውን አቅርበው፣ 

በእምነት ማስፋፊያ አገልግሎት አማካይነት ወንጌል እንዲስፋፋ ከፍተኛ አስተዋፅዖን ያበረከቱ ሶስት ገጽታዎች እንዳሉ፣ እነርሱም ሚስዮናዊ ለውጥ፣ ብርቱ ጸሎት እና የበጎ ሥራ ተጨባጭነት መሆናቸውን አስረድተዋል። መጀመርያውን በተመለከተ “የተልዕኮ መልካምነት፣ ከግለኝነት ወጥቶ ሕይወትን በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ለማድረግ ባለው ፍላጎት ላይ እንደሚወሰን በመግለጽ፣ ኢየሱስ ክርስቶስም ወደ ዓለም የመጣው ሌሎችን ለማገልገል እንጂ ለመገልገል እንዳልሆነ አስረድተዋል። ለዚህ ዓብይ ምሳሌ የምትሆነን ፓሊን ጃሪኮ፣ የኢየሱስ ክርስቶስ ፍቅር በሰዎች ሁሉ ላይ ይበራ ዘንድ፣ ኢየሱስ ክርስቶስን እና እራሷን በደረሰባት መከራ ለማሳየት መሞከሯን ገልጸዋል። ቅዱስነታቸው በማከልም፣ የወንጌል ተልዕኮ እውን በማድረግ እምነትን ወደ ዓለም ማድረስ የሚቻለው ዕለት ዕለት እግዚአብሔርን በመምሰል እንደሆነ አስረድተዋል።

ጸሎት

ስለ ጸሎት አስፈላጊነት አጽንዖት የሰጡት ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ ጸሎት የመጀመሪያው የተልዕኮ ዓይነት እንደሆነ ገልጸው፣ ፖሊን ከእምነት ማስፋፊያ አገልግሎት እና ከሕያው የመቁጠሪያ ጸሎት እንቅስቃሴዎች ጋር መተባበሯ በአጋጣሚ እንዳልሆነ፣ ነገር ግን  ተልዕኮ የሚጀምረው በጸሎት እንደሆነ እና ያለ ጸሎት ምንም መፈጸም እንደማይቻል ገልጸው፣ መልካም ሥራዎቻችን ማበርከት የምንችለው በኢየሱስ ክርስቶስ መንፈስ እና በጸጋው እንደሆነ፣ ያለበለዚያ ተልዕኮው ከንቱ ሩጫ እንደሚሆን አስረድተዋል።

የበጎ አድራጎት ተጨባጭነት

ከጸሎት ቀጥሎ ቁሳዊ ዕርዳታ እና በጎ አድራጎት ሊኖር እንደሚገባ የተናገሩት ቅዱስነታቸው፣ ፓሊን ጃሪኮ በጸሎት የጀመረችው ተልዕኮ ወደ ፊት እንዲጓዝ የረዳት በሚስዮናዊ ሕይወት እንቅስቃሴ ላይ የነበራት መረጃ እና የሰዎች ልግስና መሆኑን አስታውሰዋል።

የፓሊን ጃሪኮ ፈለግ መከተል

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በፈረንሳይ ሊዮን ከተማ ከሰኞ ግንቦት 8 - 15/2014 ዓ. ም.  ድረስ ጠቅላላ ጉባኤያቸውን በማካሄድ ላይ ለሚገኙት ጳጳሳዊ የተልዕኮ አገልግሎት ማኅበር አባላት የላኩትን መልዕክት ሲያጠቃልሉ፣ ለማኅበሩ አባላት በሙሉ መልካምን ተመኝተው፣ ፓሊን ጃሪኮ “ታላቅ ሚስዮናዊት ሴት” መሆኗን በማስታወስ፣ ተጨባጭ እምነቷን፣ ለተልዕኮ የነበራትን ድፍረት እና ደግነቷን እንዲከተሉ በማሳሰብ መልዕክታቸውን ደምድመዋል።

17 May 2022, 17:01