ፈልግ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፥ “አረጋዊያን ጥበብን ስለሚያወርሱን አክብሮት ሊሰጣቸው ይገባል!”

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ግንቦት 3/2014 ዓ. ም. በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተገኙት ምዕመናን ሳምታዊ የጠቅላላ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮአቸውን አቅርበዋል። በብሉይ ኪዳን መጽሐፍ ውስጥ የሚገኘውን የዮዲት ታሪክ መሠረት በማድረግ ባቀረቡት አስተምህሮአቸው፣ ዮዲት የእስራኤልን ሕዝብ ከሚደርስበት ጥቃት በጥበብ ለመከላከል ያደረገችውን ብርቱ ተጋድሎ እና ጥረት አስታውሰው፣ የዕድሜ ባለጸጎች በልግስናቸው ለቤተሰብም ሆነ እና ለኅብረተሰብ ሊያበረክቱ የሚችሉት አስተዋፅዖ ከፍተኛ እንደሆነ ገልጸው፣ በአረጋውያን እና ወጣቶች መካከል ያለውን ግንኙነት የበለጠ ፍሬያማ እንዲሆን ለማድረግ በትውልዶች መካከል ያለው ግንኙነት ሊጠናከር እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የእስራኤልን ሕዝብ ከጠላቶቹ የጠበቀች፣ በእርጅናዋ ዘመን በጥበብ እራሷን የለየች የብሉይ ኪዳን ዘመን ገፀ ባሕሪ የዮዲት ሕይወት በዘመናችን ለሚገኙት አረጋውያን የሚያበረክተው ብዙ ትምህርት እንዳለ ቅዱስነታቸው ገልጸዋል። በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተገኙት ምዕመናን ባቀረቡት ሳምታዊ አስተምህሮአቸው፣ የብሉይ ኪዳን ዘመን ብርቱ ሴት ዮዲት በ105 ዓመት ዕድሜዋ ያደረገቻቸውን ተግባራት ​​በመጥቀስ፣ ብርቱነት በአንዳንድ ሰዎች አእምሮ ውስጥ የሚመላለሱ የታላላቅ ክንውኖች ውጤት ብቻ እንዳልሆነ ጠቁመው፣ ብርቱነት በፍቅር ጽናት ውስጥ ለሚገኝ ቤተሰብ የሚደረግ የማኅበረሰብ ድጋፍ እንደሆነ አስረድተዋል።

በአረጋውያን ሕይወት ላይ በማስተንተን ማቅረብ የጀመሩት ሳምንትዊ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምሮ ክፍል ዘጠኝ፣ በዮዲት ረጅም ዕድሜ ላይ ያተኮሩ ሲሆን፣ "ከጡረታ በኋላ በርካታ ተጨማሪ ዓመታትን መኖር ዛሬ የተለመደ እንደሆነ ገልጸው፣ የጡረታ ጊዜን ተስፋ በማድረግ፣ ከአድካሚ ሥራ የሚገላገሉበት የዕረፍት ጊዜ አድርገው የሚመለከቱ፣ ጊዜያቸውን እንዴት ማሳለፍ እንደሚገባ በማሰብ ጭንቅት ውስጥ እንደሚወድቁ አስረድተዋል። ለአንዳንድ የዕድሜ ባለጸጎች የልጅ ልጅን ማሳደግ ደስታን የሚሰጥ ቢሆንም ቁርጠኝነትን የሚጠይቅ መሆኑን ገልጸው፣ በዛሬው ዘመን የልጅ ልጅን በማሳደግ አያቶች በቤተሰብ ውስጥ ትልቅ ሚናን እንደሚጫወቱ አስረድተዋል። አረጋውያን በቤተሰብ ደረጃ በሚያበረክቱት እገዛ ላይ ብቻ በማትኮር፣ ሌሎች የትምህርት ዘርፎችን ለአያቶች በአደራ ለመስጠት ማመንታት እንዳለ የገለጹት ቅዱስነታቸው፣ በትውልዶች መካከል ያለው ባሕላዊ ጥምረት እንደገና እንዲቀረጽ የሚጠይቁ፣ በትምህርት እና በወላጅ ግንኙነት ውስጥ የሚታዩ አዳዲስ ፍላጎቶች መኖራቸውን ገልጸዋል።

ሰብዓዊ ፍቅርን የሚጋራ ትውልዶች ኅብረት

ትውልዶች ለረጅም ዘመናት አብረው የሚኖሩትን ባሕል ያስታወሱት ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ ሁላችንም በዘመናዊው ማኅበረሰብ ውስጥ ሁኔታዎችን በማመቻቸት ማኅበራዊ ሕይወት ፍቅር የሚገለጽበት የበለጠ ሰብዓዊ እና ፍትሃዊ እንዲሆን ለማድረግ ጥረት ይደረግ እንደሆን ጠይቀው፣ የአያቶች ጥሪ ዋናው አካል ሕጻናትን በጥበብ ማሳደግ እና መደገፍ እንደሆነ ገልጸው፣ ሕጻናት የትህትናን፣ የአክብሮትን፣ የርኅራሄ እና የጋራ ሕይወት ሥነ ምግባሮችን የሚማሩት በዚህ መንገድ እንደሆነ እና አያቶችም የማይተኩ የሕይወት ልምዶችን ለሕጻናት በማካፈል ከፍተኛ አስተዋጽኦን ማበርከት የሚችሉ መሆናቸውን አስረድተዋል። አያቶችም በበኩላቸው ርኅራሄን ማስተማር እና አቅመ ደካማነት የውድቀት ምልክቶች እንዳልሆነ፣ ነገር ግን ወጣቶች በወደ ፊት ሕይወታቸው ሰብዓዊነትን የሚማሩበት እርምጃ መሆኑን አስረድተዋል።

የዮዲት ምሳሌ እና የአረጋውያን ተሰጥኦ ውበቶች

በሳምንታዊ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮአቸው የዮዲትን ምሳሌ ያስታወሱት ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ ዮዲት መበለት በመሆን ልጅ ባይኖራትም፣ ነገር ግን እንደ ዕድሜ ባለ ጸጋ ሴት እግዚአብሔር የሰጣትን ተልዕኮ በመገንዘቧ፣ የተሟላ እና የተረጋጋ ሕይወት መኖር መቻሏን ተናግረዋል። ዮዲት የጥበብን እና የርህራሄ ስጦታዎችን ለቤተሰብ እና ለማኅበረሰብ አውርሳ ማለፏን ቅዱስነታቸው አስታውሰው፣ ውርሱ የንብረት ብቻ ሳይሆን የመልካም ሥነ-ምግባርም መሆኑን ገልጸዋል። ስለ ውርስ ሲነሳ ብዙ ጊዜ ስለ ንብረት፣ ስለ ቤት፣ ስለ መሬት እና በአጠቃላይ ስለ ሃብት እንደሚታሰብ ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ አስታውሰው፣ ከሁሉ የተሻለ ውርስ በእርጅና ዘመን የተዘራ መልካም ሥነ-ምግባር እንደሆነ አስረድተዋል። ዮዲትም በእርጅናዋ ዘመን ለምትወዳት አገልጋዩዋ በነፃ ያወረሰቻት እና ቅርቧ ለነበሩት ሰዎች የሰጠቻቸው ትኩረት እና ያሳየቻቸው መልካምነት እንደነበር ገልጸዋል።

በእርጅና ዘመን የሚቀርቡ የልገሳ ሃብቶች

አዛውንት በለጋስነታቸው ያላቸውን እንደሚለግሱ የተናገሩት ቅዱስነታቸው፣ የአዛውንት ልገሳ ማስተማር፣ መገሰጽ፣ መልካም ማኅበረሰብን መገንባት፣ መተሳሰብ እና መደማመጥ ሊሆን እንደሚችል ገልጸው፣ በእርጅና ምክንያት የተቸገሩትን እና የማገናዘብ ችሎታ ለሚያንሳቸው ወይም ያለ ረዳት ለቀሩት አረጋውያን ድጋፍ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ቅዱስነታቸው አደራ ብለዋል።

የጥበብ ውርስ

ወደ ዮዲት ምሳሌ እንደገና መመለስን የወደዱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ዮዲት የሚያሳዝን የጡረታ ሕይወት የምትኖር ሳትሆን እግዚአብሔር በስጦታ የሰጣትን ዕድሜ በሙላት የኖረች ደፋር እና ቆራጥ ሴት እንደነበረች አስታውሰው፣ አያቶች ለልጆቻቸው እና ለልጅ ልጆቻቸው የሚያወርሱት ቁሳዊ ሃብትን እና ንብረት ሳይሆን፣ ጉብዝናን እና ጥበብን ሊሆን እንደሚገባ ተናግረው፣ ምዕመናን በብሉይ ኪዳን መጽሐፍ ውስጥ የሚገኘውን መጽሐፈ ዮዲትን በድጋሚ እንዲያነቡት በማሳሰብ፣ ረቡዕ ግንቦት 3/2014 ዓ. ም. ያቀረቡትን የጠቅላላ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮአቸውን ደምድመዋል። 

12 May 2022, 16:29