ፈልግ

በአፍጋኒስታን ውስጥ የሚታይ የሕጻናት የሥራ ክፍፍል በአፍጋኒስታን ውስጥ የሚታይ የሕጻናት የሥራ ክፍፍል  (AFP or licensors)

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ በዓለማችን በርካታ ሕጻናት መብታቸውን መነፈጋቸውን አስታወቁ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በደቡብ አፍሪካ፣ ደርባን ከተማ በመካሄድን ላይ ለሚገኝ የዓለም የሥራ ድርጅት ጉባኤ መልዕክት ልከዋል። ጉባኤው በሕጻናት ላይ የሚፈጸም የጉልበት ብዝበዛን ለማስቀረት እና መብታቸውንም ለማስከበር የጋራ በሆነ ወሳኝ እና ቆራጥነት መንገድ ክስተቱን ለመታገል ያለመ መሆኑ ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ድህነት ለሁሉ ዓይነት ብዝበዛ ዋና ምክኛት እንደሆነ የገለጸው ጉባኤው፣ ሰብዓዊ መብቶችን ካለመጠበቅ ጋር ተያይዞ የሚመጣው ሰቆቃ በየዓመቱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ፣ እራሳቸውን መከላከል የማይችሉ ወንድ እና ሴት ሕጻናት በእርሻ ሥራ እና በማዕድን ቁፋሮ ሥራ ተሠማርተው እንደሚገኙ ጉባኤው አስታውሶ ሕጻናቱ ውሃ ለመቅዳት ረጅም መንገድ እንደሚጓዙ፣ ትምህርታቸውን እንዳይከታተሉ  በሚከለክሉ ሥራዎች ላይ እና በሴትኛ አዳሪነት ወንጀል እንዲሰማሩ መገደዳቸውን አስታውሷል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስም ከዚህ በፊት ለዓለም የሥራ ድርጅት (አይኤልኦ) ባስተላለፉት መልዕክት፣ በዓለማችን በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሕጻናት በኢኮኖሚያዊ እና ባሕላዊ የድህነት ሕይወት ውስጥ እንደሚገኙ መናገራቸው ይታወሳል።

መንስኤዎችን ማስወገድ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ከእሁድ ግንቦት 7 - 12/2014 ዓ. ም. በደቡብ አፍሪካ ደርባን ከተማ ለተጀመረው አምስተኛው ዓለም አቀፍ የህጻናት ጉልበት ብዝበዛን ለማስወገድ ለተዘጋጀው ጉባኤ መልዕክት ልከዋል። በትናንትናው እለት የር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስን መልዕክት ለስብሰባው ታዳሚዎች ያቀረቡት፣ በደቡብ አፍሪካ የቅድስት መንበር እንደራሴ የሆኑት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ፒተር ብራያን ዌልስ ሲሆኑ፣ ቅዱስነታቸው በዚህ መልዕክታቸው፣ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እየተባባሰ የመጣውን ዓለም አቀፉ የጤና ቀውስ እና የድህነት አስከፊነት አስታውሰዋል። ቅዱስነታቸው ይህን ሁኔታ ለጉባኤው ተካፋዮች አስታውሰው፣  ሕጻናት ማንም ሊያከናውን የማይገባውን የሥራ ዓይነት ለመሥራት መገደዳቸውን ገልጸው፣ ብቃት ያላቸው ዓለም አቀፍ እና ብሔራዊ አካላት፣ የዓለም አቀፍ ድህነት መዋቅራዊ መንስኤዎችን እና አሁንም ድረስ ያለውን አሳፋሪ የእኩልነት ማጣት ለማስቀረት ከፍተኛ ቁርጠኝነትን እንዲያሳዩ ጠይቀዋል።

"በቆራጥነት እንዲከናወን!"

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በማከልም፣ ብዙውን ጊዜ ወደ ከፋ ጥቃት ከሚመራው የጉልበት ብዝበዛ ጋር በአንድነት በዓለማችን በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሕፃናት ከእግዚአብሔር የተሰጣቸው የሕጻንነት ጊዜ ደስታ እና ክብር ተነፍገው እንደሚገኙ ገልጸዋል። በመሆኑም ዓለም አቀፍ የሥራ ድርጅት ያዘጋጀውን ጉባኤ በመካፈል ላይ የሚገኙት አባላት በሙሉ ለጉዳዩ ትኩረትን በመስጠት፣ የልጆችን ክብር እና መብት ለማስጠበቅ የሚያስችሉ ተገቢ እና ውጤታማ መንገዶችን ለማግኘት፣በተለይም የማኅበራዊ ጥበቃ ስርዓቶችን በማስተዋወቅ፣ ለሁሉም የትምህርት ተደራሽነት እንዲኖር ለማድረግ ግንዛቤን የማስያዝ ሥራ በስፋት እንዲሰራ በጥብቅ አሳስበዋል። ቅዱስነታቸው አክለውም፣ ቅድስት መንበር እና መላዋ ቤተ ክርስቲያን ክስተቱን በቆራጥነት ለመታገል በጋራ መሥራት እንደሚያስፈልግ በድጋሚ ገልጸው፣ ሰብዓዊ ክብር የሚለካው፣ የሕጻናት መሠረታዊ መብቶች ሲከበሩ በሚታዩ የጎልማነት ሕይወት እና ወደ ፊት እንዲታይ በምንፈልገው የማኅበረሰብ ዓይነት እንደሆነ አስረድተዋል።

17 May 2022, 16:49