ፈልግ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ ለአገር መሪዎች ሰላም መጸለይ እንደሚገባ አሳሰቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ እሑድ ግንቦት 14/2014 ዓ. ም. በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተገኙት ምዕመናን እና መንፈሳዊ ነጋዲያን በዕለቱ በተነበበው የቅዱስ ወንጌል ክፍል ላይ በማስተንተን ስብከታቸውን አቅርበዋል። ቅዱስነታቸው በስብከታቸው፣ በየዕለቱ ‘ጌታ ሆይ ሰላምህን ስጠኝ፤ ቅዱስ መንፈስህን አብዛልኝ’ ማለትን እንድንማር እና ይህ ጸሎታችን ለራሳችን ብቻ ሳይሆን ከጎናችን ላሉት፣ በየዕለቱ ለምናገኛቸው፣ ለጎረቤቶቻችን እና ለአገር መሪዎችም ጭምር መሆን እንደሚገባ አሳስበዋል። ክቡራት እና ክቡራን አድማጮቻችን ከዚህ ቀጥሎ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን አስተንትኖ ትርጉም ሙሉ ይዘቱን እንደሚከተለው እናቀርብላችኋለን፥

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“ውድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ፤ እንኳን ለዛሬው እሑድ አደረሳችሁ!

በዛሬው ስርዓተ አምልኮ ላይ ከዮሐ. 14: 23-29 ተወሰዶ የተነበበልን የቅዱስ ወንጌል ክፍል፣ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመጨረሻው እራት ወቅት ደቀ መዛሙርቱን ሲሰናበታቸው የተናገረውን መልዕክት ያስታውሰናል። ‘ሰላምን እተውላችኋለሁ’ አላቸው። (ዮሐ. 14፡27) በማከልም ‘ሰላሜን እሰጣችኋለሁ’ አላቸው። ኢየሱስ ክርስቶስ የተናገራቸውን እነዚህ አጫጭር ሐረጎች በዛሬው አስተንትኖአችን እንመለከታቸዋለን። 

ኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱን ‘ሰላምን እተውላችኋለሁ’ በማለት ፍቅርን እና መረጋጋትን በሚገልጹ ቃላት ተሰናበታቸው። እንዲህ ብሎ የተናገራቸውም መረጋጋት በነበረበት ወቅት ነበር። ይሁዳ አሳልፎ ሊሰጠው ሄዷል፤ ጴጥሮስም ሊክደው ተዘጋጅቷል፤ ሌሎች የተቀሩትም በሙሉ ሊተውት ደርሰዋል። ኢየሱስ ክርስቶስ ይህ እንደሚሆን ያውቅ ነበር። ነገር ግን አልገሰጻቸውም፣ ከባድ ቃላትንም አልተናገረም። ከመረበሽ ወይም የመደንገጥ ስሜት ከማሳየት ይልቅ እስከ መጨረሻው ደግነቱን ገለጠላቸው። ‘በኖርክበት አኳኋን ትሞታለህ’ የሚል ምሳሌያዊ አነጋገር አለ። የኢየሱስ ክርስቶስ ሕይወት የመጨረሻ ሰዓታት፣ የመላ ሕይወቱን ይዘት የሚገልጹ ናቸው። ፍርሃት እና ሐዘን ቢሰማውም የቁጣ፣ የተቃውሞ ወይም የምሬት ስሜት አልታየበትም። ትዕግስት ይታይበት ነበር። መታመንን ከለመደ ከየዋህ ልብ ውስጥ በሚፈልቅ ሰላም ውስጥ ይገኝ ነበር። ኢየሱስ ክርስቶስ የሰጠን የሰላም ምንጭ ይህ ነው። ማንም ሰው በውስጡ ሰላም ከሌለው ለሌሎች ሰላምን ሊሰጥ አይችልምና። ያ ሰው ራሱ ሰላም ካልሆነ በቀር ለማንም ሰላምን ሊሰጥ አይችልም።

በዮሐ. 14፡27 ላይ እንደተጻፈው፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ለደቀ መዛሙርቱ ‘ሰላምን እተውላችኋለሁ’ ባላቸው ጊዜ፣ የዋሆች መሆን እንደሚቻል አሳይቷል። በተለይ በጣም አስቸጋሪ በሆነበት ጊዜ የዋህነትን በመልበሱ፣ የሰላሙ ወራሾች የሆንን እኛም እንደ እርሱ የዋሆች እንድንሆን ይፈልጋል። የዋሆች፣ ሌሎችን ለማዳመጥ ዝግጁ እንድንሆን፣ በግል እና በማኅበራዊ ሕይወታችን ውስጥ የሚታዩ ውጥረቶችን አርግበን በስምምነት እንድንኖር ይፈልጋል። ውጥረቶችን በማስወገድ በሰላም እና በስምምነት መኖር፣ ከሺህ ቃላት እና ስብከቶች በላይ ዋጋ ያለው ለኢየሱስ ክርስቶስ የምንሰጠው ምስክርነት ነው።  ሰላምን መመስከር! የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርት እንደ መሆናችን መጠን፣ በምንኖርበት አካባቢ ሁሉ የዚህ ዓይነት ባህሪ እንዳለን እራሳችንን እንጠይቅ። ውጥረቶችን እናበርዳለን ውስይስ ግጭቶችን እናባብሳለ? ከሰዎች ጋር ተጣልተን ሁል ጊዜ ለጥቃት ተዘጋጅተናል ወይስ በሰላማዊ መንገድ ምላሽ የሚሰጥበትን መንገድ እናውቃለን? እንዴት ነው ምላሽ የምሰጠው? ሁሉም ሰው በዚህ መንገድ እራሱን ሊጠይቅ ይገባል።

እርግጥ ነው! የዋህነት ቀላል አይደለም። በሁሉም ደረጃ ግጭቶችን ማርገብ ምንኛ ከባድ እንደሆነ እናውቃለን። ‘ሰላሜን እሰጣችኋለሁ’ የሚለው የኢየሱስ ክርስቶስ ሁለተኛ ሐረግ ይህን ያስረዳናል። ኢየሱስ ክርስቶስ እኛ በራሳችን ኃይል ሰላምን መፍጠር እንደማንችል ያውቃል። እርዳታን እንደምንፈልግ እና የሰላም ስጦታ እንደሚያስፈልገን ያውቃል። ግዴታችን የሆነው ሰላም ከሁሉ አስቀድሞ የእግዚአብሔር ስጦታ ነው። ‘ሰላሜን እተውላችኋለሁ፤ ሰላሜንም እሰጣችኋለሁ፤ እኔ የምሰጣችሁ ሰላም ዓለም እንደሚሰጠው ዓይነት አይደለም’ በማለት ኢየሱስ ተናግሯል። (ዮሐ. 14: 27) ዓለም የማያውቀው እና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሚሰጠን ይህ ሰላም የቱ ነው? ይህ ሰላም ቅዱስ የሆነው የኢየሱስ ክርስቶስ መንፈስ ነው። በእኛ ውስጥ የሚገኘው እግዚአብሔር የሰላም ኃይል ነው።

የጥላቻ ልብን በማስወገድ መረጋጋትን የሚሰጥ እሱ መንፈስ ቅዱስ ነው። ልበ ግትርነትን እና ሌሎችን የማጥቃት ፈተናዎችን የሚያስወግድ እርሱ መንፈስ ቅዱስ ነው። ከጎናችን ያሉ ወንድሞችና እህቶች እንጂ ጠላቶቻችን እንዳልሆኑ የሚያስገነዝበን እርሱ መንፈስ ቅዱስ ነው። በራሳችን ብርታት የበደሉንን ይቅር ማለት ስለማንችል፣ ጥንካሬ ሰጥቶን ሕይወትን እንደገና እንድንጀምር የሚያግዘን እርሱ መንፈስ ቅዱስ ነው። የሰላም ሰዎች የምንሆነው ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ስንሆን ነው።

ውድ ወንድሞቼ እህቶቼ! ማንኛውም ዓይነት ኃጢአት፣ ማንኛውም ዓይነት ውድቀት፣ ማንኛውም ዓይነት ቂም በቀል፣ ከመንፈስ ቅዱስ የሚገኘውን የሰላም ስጦታ ከመለመን ሊያግደን አይገባም። ልባችን ይበልጥ ሲታውክ፣ ስንጨነቅ፣ ትዕግስት ስናጣ፣ ስንቆጣ፣ የሰላምን መንፈስ እንዲሰጠን ኢየሱስ ክርስቶስን መጠየቅ ያስፈልጋል። በየዕለቱ ‘ጌታ ሆይ፣ ሰላምህን ስጠኝ፤ ቅዱስ መንፈስህን አብዛልኝ’ ማለትን እንማር። ይህ መልካም ጸሎት ነው። ‘አቤቱ ሰላምህን ስጠኝ፣ መንፈስ ቅዱስህን ስጠኝ’ በማለት አብረን እንጸልይ። እንዲህ በማለት ለራሳችን ብቻ ሳይሆን ከጎናችን ላሉት፣ በየዕለቱ ለምናገኛቸው፣ ለጎረቤቶቻችን እና ለሀገር መሪዎችም ጭምር መሆን ያስፈልጋል። የሰላም ፈጣሪዎች የሚያደርገንን የመንፈስ ቅዱስ ጸጋ በልባችን እንድንቀበል እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ትርዳን።”

23 May 2022, 16:46