ፈልግ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ ከፍርሃት ተላቀን የትንሳኤውን እውነት ልንመሰክር ይገባል አሉ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ የጎርጎሮሳዊኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ ክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ ያለፈው እሑድ በተከበረው የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ትንሳኤ ማግስት፣ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡት ምዕመናን ባቀረቡት መልዕክት፣ ከፍርሃት መቃብር ውስጥ ወጥተን፣ ነጻ ለሚያደርገን እውነት ምስክሮች እንድንሆን ከሞት የተነሳው ኢየሱስ ይፈልጋል ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ሰኞ ሚያዝያ 10/2014 ዓ. ም. በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡት ወደ ሃያ አምስት ሺህ ለሚደርሱ ምዕመናን ባቀረቡት መልዕክታቸው፣ ለታይታ የሚገልጽ እምነት ለወንጌል ምስክርንርት እንቅፋት ሊሆን እንደሚችል አስጠንቅቀው፣ መቃብሩን ሲጠብቁ የነበሩ ወታደሮች የኢየሱስ አስከሬን በደቀ መዛሙርቱ ተሰርቋል ብለው እንዲዋሹ ብዙ ገንዘብ የተከፈላቸው መሆኑን አስታውሰዋል።

የገንዘብ ፈተና

ወደ እመቤታችን የቀረበ የመማጸኛ ጸሎት
ወደ እመቤታችን የቀረበ የመማጸኛ ጸሎት

ውሸት እውነትን ማወጅ እንደሚቃወም የገለጹት ቅዱስነታቸው፣ የሞትን ኃይል አሸንፎ በተነሳው የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ኃይል በተቃራኒ፣ እውነቱን ለመደበቅ የሚሞክር የገንዘብ ኃይልም መኖሩን አስታውሰው፣ ይህ ኃይል የድነትን ዕድል የሚዘጋ መሆኑን አስረድተዋል።  ከብዙሃን መገናኛዎች የምናገኛቸው መረጃዎች ውሸት ሲነግሩን በትክክል እንደምንቆጣ የገለጹ ቅዱስነታቸው፣ ነገር ግን በውስጣችን ያለውን ውሸት መደበቅ ስንፈልግ፣ ከሞት የተነሳው ኢየሱስ ክርስቶስ የተደበቁ ነገሮችን ወደ ብርሃን ሊያወጣ፣ የወንጌልን ደስታ እንድንመሰክር፣ ነጻ የሚያወጣንን የእውነት ምስክሮች ሊያደርገን እንደሚፈልግ አስረድተዋል።

ከፍርሃት መቃብር ልንወጣ ይገባል!

ፍርሃት ሁል ጊዜ በልባችን ውስጥ እንዳለ ቅዱስነታቸው በመግለጽ፣ በኢየሱስ ክርስቶስ የምናምን ከሆነ ፍርሃት ሊይዘን እንደማይገባ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ የሞተው ለድነታችን እንደሆነ እና ከሞት የተነሳው ፍርሃትን ከእኛ በማስወገድ እና ለዘለዓም አብሮን ሊኖር በመሆኑ ከፍርሃት መቃብር ውስጥ ልንወጣ ይገባል ብለዋል።

 

19 April 2022, 16:55