ፈልግ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ከሩሲያ ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ፓትሪያርክ ከብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ኪሪል ጋር  ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ከሩሲያ ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ፓትሪያርክ ከብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ኪሪል ጋር  

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ለዩክሬን ሰላም ከፓትሪያርክ ኪሪል ጋር ለመሥራት እንደሚፈልጉ ገለጹ

የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ትንሳኤ በዓል እሑድ ሚያዝያ 16/2014 ዓ. ም. ላከበሩት የሞስኮ ፓትርያርክ ብጹዕ ወቅዱስ ኪሪል ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የመልካም ምኞት መግለጫ መልዕክታቸውን ልከዋል። ቅዱስነታቸው ከመልዕክታቸው በተጨማሪ የጦርነት ጨለማ ጊዜ አብቅቶ አዲስ የሰላም ጎህ እንዲቀድ የሚናፍቀውን የዩክሬን ሕዝብ በጸሎታቸው አስታውሰዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ “ወንድሜ ሆይ!” ላሏቸው የሩሲያ ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ፓትሪያርክ ለብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ኪሪል በላኩት የትንሳኤው በዓል መልካም ምኞት መልዕክታቸው፣ በጦርነት ለተመሰቃቀለች ዩክሬን፣ ታላቁ የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ትንሳኤ በዓል ከሞት ወደ አዲስ ሕይወት መሻገርን፣ ሕዝቡም በጦርነት የተዋጠ የጨለማ ጊዜ አብቅቶ አዲስ የሰላም ጎህ የሚቀድበት ጊዜን እውን ለማድረግ መንፈስ ቅዱስ ልባችንን ለውጦ እውነተኛ የሰላም ፈጣሪዎች እንዲያደርገን” በማለት ምኞታቸውን ገልጸውላቸዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ይህን መልዕክታቸውን፣ በምስራቅ ቤተ ክርስቲያን የአምልኮ ሥርዓት እና የቀን አቆጣጠር መሠረት የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ትንሳኤ በዓልን እሑድ ሚያዝያ 16/2014 ዓ. ም. ላከበረች የሩሲያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ለብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ኪሪል ልከዋል። ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ከሩሲያው ፓትሪያርክ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ኪሪል በተጨማሪም ለሌሎች የምስራቅ አብያት ክርስቲያናት ፓትሪያርኮች የላኩትን የትንሳኤው በዓል መልካም ምኞት መግለጫ መልዕክቶችን የሞስኮ ፓትርያርክ ጽሕፈት ቤት በማኅበራዊ ድረ-ገጹ ላይ ይፋ ማድረጉ ታውቋል።

ለሰዎች ስቃይ ግምት መስጠት

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመልዕክታቸው በአሁኑ ጊዜ የሰው ልጅ በዓመፅ፣ በጦርነት እና በብዙ የፍትሕ መጓደል ሰብዓዊ ቤተሰባችን በስቃይ ላይ መሆኑን ጠቁመው፣ “ምንም እንኳን እነዚህ መከራዎች ቢኖሩም፣ የዓለማችንን ክፋት እና ስቃይ ለተቀበለው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ምስጋናችንን እናቀርብለታለን” ብለዋል። የኢየሱስ ክርስቶስ ሞት የአዲስ ሕይወት መጀመሪያ እና ከኃጢአት እስራት ነጻ በማውጣት ደስታ የተገኘበት አጋጣሚ እንደሆነ ገልጸው፣ ከጨለማ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ብርሃን የተሸጋገርንበት መንገድ ነው" ብለዋል። ቅዱስነታቸው ከዚህም በተጨማሪም የምስራቅ አብያተ ክርስቲያናት ፓትርያርኮች በጸሎት እንዲደጋገፉ፣ ከሞት ስለተነሳው ኢየሱስ ክርስቶስ እና ስለ ቤተክርስቲያን የወንጌል አገልግሎት ታማኝነት ምስክርነትን እንዲሰጡ አደራ ብለው፣ በዚህ መንገድ “ሁሉም ወደ ፍትሕ፣ ሰላም እና በመንፈስ ቅዱስ ወደሚገኝ የደስታ መንግሥት መግባት እንችላለን” ብለዋል።

አስቀድሞ የተላከው የቪዲዮ ጥሪ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በዩክሬን እየተካሄደ ያለውን ጦርነት በማስመልከት ከሞስኮ ፓትሪያርክ ከብጹዕ ወቅዱስ ኪሪል ጋር መጋቢት 7/2014 ዓ. ም. መወያየታቸውን፣ የቫቲካን ጋዜጣዊ መግለጫ ክፍል ዳይሬክተር ክቡር አቶ ማቴዮ ብሩኒ መግጻቸው ይታወሳል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከብጹዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ኪሪል ጋር ባደረጉት የቪዲዮ ውይይት፣ “የሕዝቦች መንፈሳዊ መጋቢዎች እንደ መሆናችን፣ ለሰላም በሚደረግ ጥረት አንድ መሆን አለብን” ማለታቸው ይታወሳል። የቅድስት መንበር ጋዜጣዊ መግለጫ ክፍል ዳይሬክተር አቶ ማትዮ ብሩኒ በውቅቱ በሰጡት መግለጫ እንደገለጹት፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የሩስያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብጹዕ ወቅዱስ ኪሪል በዩክሬን የተነሳውን የጦርነት እሳት ለማጥፋት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ፣ በጦርነቱ  ምክንያት የሚሞቱት እና ከፍተኛ ዋጋን የሚከፍሉት ወታደሮች እና ሰላማዊው ዜጎች እንደሆኑ መናገራቸውን ገልጸው እንደነበር ይታወሳል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በዚያን ወቅት ከሞስኮ ፓትሪያርክ ከብጹዕ ወቅዱስ ኪሪል ጋር ባደረጉት የቪዲዮ መልዕክት ልውውጥ “ቤተ ክርስቲያን የኢየሱስ ክርስቶስን የሰላም ቋንቋ እንጂ የፖለቲካ ቋንቋ መጠቀም የለባትም” ማለታቸውም ይታወሳል።

ቅዱስነታቸው ከፓትሪያርኩ ጋር ለመገናኘት የነበራቸ ዕቅድ መሰረዙ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ያለፈው ዓርብ ሚያዝያ 14/2014 ዓ. ም. ከአርጀንቲና ጋዜጣ ላ ናሲዮን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፣ በሰኔ ወር ኢየሩሳሌም ከተማ ከሞስኮ ፓትርያርክ ከብጹዕ ወቅዱስ ኪሪል ጋር ለመገናኘት ቀጠሮ ተይዞ የነበረ ቢሆንም መሰረዙን ገልጸው፣ በሁለቱ አብያተ ክርስቲያናት መካከል ያለው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እ. አ. አ በ2016 ዓ. ም. በኩባ ዋና ከተማ ሃቫና ተገናኝተው ያወጡት የጋራ መግለጫ እንዳለ መናገራቸውን ላ ናሲዮን የተባለ የአርጄንቲና ብሔራዊ ጋዜጣ ገልጿል።  

26 April 2022, 15:34