ፈልግ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፡ ጭካኔያዊ የጦርነት ተግባር እንዲያቆም ጠየቁ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ መጋቢት 21/2014 ዓ. ም. ባቀረቡት ሳምንታዊ ጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ፍጻሜ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፣ በሩሲያ እና በዩክሬን መካከል በመካሄድ ላይ ያለው ጦርነት እንዲያቆም ጥሪያቸውን በድጋሚ አቅርበው፣ በጦርነቱ ወቅት በመፈጸም ላይ የሚገኝ ጭካኔ የተመላበት ተግባርም እንዲያቆም ጠይቀዋል። ቅዱስነታቸው በሁለት ሰብዓዊ ዕርዳታ ሰጭ ድርጅቶች እገዛ አማካይነት በዩክሬን ውስጥ ጦርነቱ ካየለባት ቼርኖቪል ከተማ ወጥተው ወደ ጣሊያን ለደረሱት ሕጻናት ሰላምታቸውን አቅርበውላቸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ቅዱስነታቸው ከዩክሬን ለመጡት ሕጻናት ሰላምታ ባቀረቡበት ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት፣ በምሥራቅ አውሮፓ እየተካሄደ ያለውን ደም ማፍሰስን በድጋሚ አውግዘው፣ ከዚህም ጋር ስለ ጦርነት በማሰብ ጭካኔ የተሞላበት አስከፊ የጦርነት ተግባርም እንዲያቆም ጸሎታችንን ደግመን እናቅርብ ብለው፣ “በዚህ የዓብይ ጾም መጨረሻ ወቅት ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል ተመልክተን፣ የእግዚአብሔርን ታላቅ የፍቅር መግለጫ በመገንዘብ ከሚሰቃዩት፣ ረዳት ከሌላቸው፣ በአመጽ ጊዜ በግፍ ከሚሰቃዩ እና ተከላካይ ከሌላቸው አቅመ ደካሞች ጋር ሁልጊዜ መሆን ያስፈልጋል” ብለዋል።

ከቼርኖቬል አደጋ ከተረፉ ሕጻናት ጋር መሆን

“ፑዬር” የተባለ ሰብዓዊ ዕርዳታ አቅራቢ ማኅበር ዋና ተልዕኮ፣ በአደገኛ ማኅበራዊ ቀውስ ውስጥ ለሚገኙ በተለይም አካለ መጠን ላልደረሱ ሕፃናት ትኩረት በመስጠት ድጋፍ የሚያደርግ በጎ አድራጊ ድርጅት መሆኑ ታውቋል። በቼርኖቬል የኑክሌር ኃይል ማመንጫ ጣቢያ ላይ እ. አ. አ ሚያዝያ 26/1986 ዓ. ም. ፍንዳታ መከሰቱ ይታወሳል። ለማኅበሩ ምስጋና ይግባውና በወቅቱ በሺዎች የሚቆጠሩ ሕፃናት በከፍተኛ ጨረር ምክንያት ጉዳት እንዳይደርስባቸው በማለት አደጋው ወደማደርስበት አካባቢ በተለይም ወደ አጎራባች አገር ቤላሩስ በማጓጓዝ የነፍስ አድን ዕርዳታን ማድረጉ ይታወሳል። በቼርኖቤል የኒውክሌር አደጋ የተጎዱትን ሕፃናት ለመርዳት በበጎ ፈቃደኞች የተመሠረተው እና “በሕይወት እንዲኖሩ እርዳቸው” የተሰኘ ሌላው ዕርዳታ ሰጭ ፋውንዴሽን ልኡካን ቡድን በቅርብ ቀናት ውስጥ ከዩክሬን ጋር በሚዋሰኑ አገራት ድንበር ላይ በመሄድ ሌሎች ሰብዓዊ ዕርዳታዎችን ጨምሮ ምግብ፣ አልባሳት፣ ብርድ ልብስ፣ ጫማ እና መድኃኒቶችን ማከፋፈሉ ታውቋል።

የምግብ እና የልብስ ዕርዳታ ብቻ አይደለም!

“ፑዬር” የተባለ ሰብዓዊ ዕርዳታ አቅራቢ ማኅበር ፕሬዚደንት ክቡር አቶ ሴርጆ ዴ ቺኮ ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የላኩትን ልባዊ ሰላምታ በዩክሬን የሚገኙ ሕጻናት እና እናቶቻቸው በታላቅ ስሜት መቀበላቸውን ገልጸው፣ "በተለይም ቅዱስነታቸው የሀገራቸውን ስም ሲጠሩ ያፈሰሱት እንባ ልብ የሚነካ ነበር” ብለዋል። ማኅበራቸው ለሕጻናት ሰብዓዊ ዕርዳታን ማቅረብ ከጀመረ ሰላሳ ዓመታትን ማስቆጠሩን የገለጹት አቶ ሴርጆ፣ ሰብዓዊ ዕርዳታቸውን ከዚህ በፊት የዩክሬን ጎረቤት አገር በሆነች ቤላሩስ ለሚገኙ ሕጻናት ሲያቀርቡ መቆየታቸውን ገልጸው፣ በዩክሬን ጦርነቱ ከተነሳ ወዲህ በተቻለ መጠን ሕጻናት ያሏቸው እናቶችን እንደሚቀበሉ ተናግረዋል። ትምህርት ቤቶችን በማመቻቸት ሕጻናት እንዲገናኙ እና ከትምህርት ሥርዓት ጋር እንዲተዋወቁ ማኅበራቸው ትልቅ ድጋፍ እየሰጠ መሆኑን አስረድተዋል።  

ልጅነት ተክዷል

በዩክሬን ውስጥ ጦርነት ከተቀሰቀሰበት ማለትም ከየካቲት 17/2014 ዓ. ም. ወዲህ ቢያንስ 144 ህጻናት መሞታቸው ታውቋል። በዩክሬን ያሉት ምንጮች ይፋ እንዳደረጉት ከሰለባዎቹ መካከል ግማሽ ያህሉ የዋና ከተማዋ ኪዬቭ ነዋሪዎች እንደነበሩ አስታውቀዋል። በተባበሩት መንግሥታት የሕጻናት መርጃ ድርጅት “ዩኒሴፍ” ባወጣው መረጃ መሠረት ቢያንስ ከ4 ሚሊዮን 300 ሺህ ተፈናቃዮች መካከል ከ1.8 ሚሊዮን በላይ ሕጻናት ወደ ጎረቤት አገራት መሰደዳቸውን እና 2.5 ሚሊዮን ሕጻናት በአገር ውስጥ መፈናቀላቸውን አስታውቋል። የዩኒሴፍ ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ካትሪን ራስል "ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ በሕፃናት ላይ ከደረሰው ፈጣን መፈናቀል መካከል አንዱ መሆኑን ገልጸው፣ ይህም ለትውልድ የሚዘልቅ መዘዝን ያስከተለ አሳዛኝ ውጤት ነው ብለዋል።

ያለ ሕክምና ዕርዳታ እና የትምህርት ዕድል ባዶ መቅረት

በዩክሬን እየተካሄደ ያለው ጦርነት በመሠረተ ልማቶች ላይም ከፍተኛ አደጋን ማስከተሉ ተነግሯል።  ሆስፒታሎች እና ትምህርት ቤቶች ወድመዋል። የዩክሬን የትምህርት እና የሳይንስ ሚኒስቴር ከ500 በላይ የትምህርት ተቋማት ጉዳት እንደደረሰባቸው አስታውቋል። በዩክሬን ውስጥ ቢያንስ 1.4 ሚሊዮን ሰዎች ንጹህ የመጠጥ ውሃ እንደሌላቸው ተገምቷል። የሕጻናት መርጃ ድርጅት “ዩኒሴፍ” በተጨማሪ እንዳስታወቀው በምሥራቅ አውሮፓ አገር ዩክሬን፣ ኩፍኝ እና ፖሊዮን ጨምሮ ለህፃናት የሚሰጡ ክትባቶች ሽፋን መቀነሱን አስታውቋል። ይህም በክትባት ሊከላከሉ የሚችሉ በሽታዎች በፍጥነት እንዲስፋፉ ሊያደርግ እንደሚችል፣ በተለይም በተጨናነቁ አካባቢዎች፣ ከወረራ እና አየር ድብደባ ለመከላከል በተጠለሉበት አካባቢ የከፋ ሊሆን እንደሚችል ድርጅቱ አስታውቋል። 35ኛ ቀኑን የያዘው የዩክሬን ጦርነት አሰቃቂ እና ከፍተኛ ውድመትን እያስከተለ ሲሆን በተለይም ሰላም እና ጥበቃ የሚያስፈልገውን አዲሱን ትውልድ ለሞት እየዳረገው መሆኑ ታውቋል። 

31 March 2022, 15:47