ፈልግ

የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤነዲክቶስ 15ኛ በጽሕፈት ቤታቸው ሆነው የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤነዲክቶስ 15ኛ በጽሕፈት ቤታቸው ሆነው 

ሰላም የሚረጋገጠው በፍትሃዊነት ጥላቻንና ቂምን ሲያስወግድ መሆኑ ተገለጸ

በዩክሬን ውስጥ ከፍተኛ ድንጋጤን ያስከተለ ጦርነት እየተካሄደ ባለበት በዚህ ወቅት፣ የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤነዲክቶስ 15ኛ በ1912 ዓ. ም. “ሰላም ፣ እጅግ ውብ የሆነ የእግዚአብሔር ስጦታ ነው!” በማለት ይፋ ያደረጉትን ሐዋርያዊ ሰነድ እናስታውሳለን።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

1912 ዓ. ም. አውሮፓ ታላቁ ጦርነት በፈጠረባት ቁስሎች እና በአንዳንድ ያልተፈቱ ጉዳዮች ምክንያት በሁለተኛው የዓለም ጦርነት እየተሰቃየች የምትገኝበት ጊዜ ነበር። የቬርሳይ ውል ጦርነት በይፋ እንዲቆም ያደረገ ቢሆንም፤ ነገር ግን ጦርነቱ እንዲቀጣጠል ላደረጉት ምክንያቶች ምንም ዓይነት ትክክለኛ መፍትሄ አላገኘለትም ነበር። ነገሮች አስፈሪ በሆኑበት እና ጦርነቱም ከመጀመሩ ሦስት ዓመታት አስቀድመው፣ የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤኔዲክቶስ 15ኛ “ጦርነት እልቂትን የሚያስከትል ዋጋ ቢስ ነው” በማለት “ሰላም ፣ እጅግ ውብ የሆነ የእግዚአብሔር ስጦታ ነው!” የሚለውን ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን ይፋ አደረጉ። በጴንጠቆስጤ ዕለት፣ እሑድ ግንቦት 15/1912 ዓ. ም. ይፋ ባደረጉት በዚህ ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳናቸው፣ “ጥላቻንና ንዴትን የሚያበርድ”፣ “ፍትሃዊ እና ዘላቂ” ሰላም ካልወረደ፣ ሰላም ሊረጋገጥ አይችልም በማለት ጽፈዋል።

ጥላቻን አስወግዶ የሚሰቃዩትን መርዳት

ዛሬ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመልዕክታቸው ከሚሰቃዩት ጋር እንድንሆን ዘወትር አበክረው እንደሚጠይቁን ሁሉ፣ የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤነዲክቶስ 15ኛ በጊዜው ለነበረው ክርስቲያን ማኅበረሰብ ባስተላለፉት መልዕክት፥ “ምዕመናን በአደራ የተሠጣችሁ ጥላቻን እና ጥፋት እንዲያስወግዱ ለማድረግ ብቻ ሳይሆን ክርስቲያናዊ በጎ አድራጎት አገልግሎታችሁን በስፋት ለማዳረስ የቻላችሁትን በሙሉ እንድታደርጉም ጭምር ነው። የተቸገሩትን መርዳት፣ ማፅናናት፣ ደካሞችን ከጉዳት ለመከላከል እና በጦርነቱ ምክንያት ከፍተኛ ጉዳት ለደረሰባቸው በሙሉ በአጭር ጊዜ ውስጥ ዕርዳታን በማቅረብ ምቹ ሁኔታን እንድትፈጥሩላቸው፣ የኢየሱስ ክርስቶስ የቸርነት ተግባር እድትፈጽሙ እንለምናችኋለን።” በማለት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል። 

የጦርነት ጭካኔያዊ ምልክቶች ያለባቸው ሕዝቦች

የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤነዲክቶስ 15ኛ፣ “ሰላም ፣ እጅግ ውብ የሆነ የእግዚአብሔር ስጦታ ነው!” በሚለው ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን ውስጥ የገለጹት የጦርነት አስከፊነት፣ ዛሬ በዩክሬን እና ግጭቶች በሚታዩባቸው ሌሎች አገሮች ውስጥ ከምናያቸው እውነታዎች ጋር ተመሳሳይነት አለው። “ጦርነቱ የተካሄደባቸውን አካባቢዎች ዙሪያቸውን ብንመለከት፣ ያልታረሱ እና የተተዉ እጅግ የተራቆቱ ክልሎችን እናገኛለን።  “የተጨቆነ የሰው ልጅ ከስቃይ ብዛት የተነሳ ዕርዳታን የሚጠይቅበት የመከራ ምስል ከፊት ለፊታችን ተጋርጦብናል፡- “የዕለት እንጀራ፣ ልብስ እና መጠለያ የሌላቸው በርካታ ሰዎች አሉ። ብዙ እናቶች እና ወላጅ አልባ ሕፃናት ዕርዳታን በመጠባበቅ ላይ ይገኛሉ። እጅግ የተቸገሩ ብዙ ሰዎች በተለይም ሕፃናት፣ ሰውነታቸው በጦርነት መጎዳቱን ይመሰክራል። ሁላችንም በከባድ ጭንቀት ውስጥ በምንገኝበት ወቅት በጎ ሥራችንን የምናበረክትባቸው ቀናት እንዲጨምሩ እና ድንበሮችም ከአሁኑ በበለጠ መስፋት ይኖርባቸዋል።” በማለት የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤነዲክቶስ 15ኛ ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳናቸውን አቅረበዋል።  

የሰላም ዋስትናን የሚሰጥ ክፍል ሊኖር ይገባል

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤነዲክቶስ 15ኛ፣ ወደፊት ሰላምን የሚያረጋግጥ አንድ ክፍል እንደሚፈጠር ተስፋ ባደረጉበት መልዕክታቸው፡- “ሁሉም ክልሎች አንዱ በሌላው ላይ ያለውን ጥርጣሬ አስወግዶ፣ በአንድ ማኅበረሰብ ውስጥ፣ ይልቁንም በሕዝባዊ ቤተሰብ ውስጥ ማለት ይቻላል፣ የእያንዳንዱን ሰው፣ የዜጎችን ነፃነት የሚያረጋገጥ እና የሚያስጠብቅ ማኅበራዊ ጥምረት ሊኖር ይገባል። ይህን ማኅበረሰብ በሕዝቦች መካከል መመስረቱ፣ ከሌሎች በርካታ ጉዳዮች በተጨማሪ ለወታደራዊ ኃይል ግንባታ የሚውለውን ግዙፍ ወጪ በማስቀረት ሕዝብን ከጦርነት አደጋ መከላከል ያስፈልጋል። ወደፊትም በዚህ መልኩ ነፍስ ገዳይ የሆኑ አስከፊ ጦርነቶችን በማስወገድ እያንዳንዱ ሕዝብ የግዛቱን ነፃነት በታማኝነት ማረጋገጥ ይችላል።” በማለት ተናግረዋል።

ሰላም ልግስና ያስፈልገዋል

በዚህ አሳዛኝ እና ታሪካዊ ወቅት፣ የሰውን ልጅ ከዚህ በፊት ያጋጠሙት አስጨናቂ ገጽታዎች በድጋሚ ተንጸባርቀዋል። “ሰላም ፣ እጅግ ውብ የሆነ የእግዚአብሔር ስጦታ ነው!” የሚለው ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳንም፣  ሰላም፣ ድንገተኛ ስምምነቶችን ሳይሆን ዘላቂ መፍትሄዎችን የያዘ ሊሆን እንደሚገባ ያስገነዝባል። የሰላም ዘር ስር ሊሰድ የሚችለው ቂሞች ተለውጠው በበጎ ተግባራት ላይ በመመስረት እርቅን ካላመጡ ሰላም ሊገኝ እንደማይችል የቀድሞ ር. ሊ. ጳ ቤኔዲክቶስ 15ኛ አሳስበዋል።  ይህ “የልግስና ሥርዓት” ኢየሱስ ክርስቶስ “ጠላቶቻችሁን ውደዱ፤ ለሚጠሉአችሁ መልካም አድርጉ፣ ለሚያሳድዱአችሁ እና ለሚሰድቡአችሁ ጸልዩላቸው” ባለው ላይ ያስተነተነ ነው። "ይህን ሕግ መታዘዝ ከባድ ነው" ነገር ግን ክርስቲያኖች ከሁሉም በፊት፣ "አባት ሆይ የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው" ያለውን ኢየሱስ ክርስቶስን እንዲመስሉ ተጠርተዋል። እነዚህ ቃላት ከጸሎት እና ከበጎ አድራጎት ሥራ ጋር መያያዝ አለባቸው” በማለት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤነዲክቶስ 15ኛ የእውነተኛ ሰላም መልዕክታቸውን ማስተላለፋቸው ይታወሳል።

10 March 2022, 15:58