ፈልግ

የዛይድ ሽልማት አሰጣጥ-ሥነ ሥርዓት የዛይድ ሽልማት አሰጣጥ-ሥነ ሥርዓት  (@Alto Commitato per la Fratellanza Umana)

የዛይድ ሽልማት፣ ለዓለም አንድነት እና ሰላም ድጋፍ መሆኑ ተገለጸ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ እ. አ. አ 2020 የተካሄደውን የሰብዓዊ ወንድማማችነት ሽልማት ሥነ- ሥርዓት አስመልክተው ባስተላለፉት የቪዲዮ መልዕክት፣ የዓመቱ አሸናፊዎች የሆኑትን የዮርዳኖስ ባለ ሥልጣናት ስደተኞችን በወንድማዊነት ስሜት ተቀብለው በማስተናገዳቸው፣ እንዲሁም በሄይቲ የሚገኝ የፎካል ፋውንዴሽንን አመስግነው፣ ለአገሪቱ የተሻለ የወደፊት ተስፋን ለመስጠት ፍላጎት እና ጥረት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“የዛይድ ዓለም አቀፍ ሽልማት በሕዝቦች መካከል ወንድማማችነትን ለማሳደግ ለምናደርገው የጋራ ጉዞ ድጋፍ እንደሚሆን፣ በዓለማችን ሰላምን እና አንድነትን ለማምጣት የሚደረግ የጋራ ጥረትም ቀጣይነት እንዲኖረው የሚያደርግ መሆኑን ቅዱስነታቸው አስረድተዋል። እ. አ. አ በ2020 ለዮርዳኖሱ ንጉሥ አብዱላህ ዳግማዊ፣ ለንግሥት ራኒያ እና በሄይቲ ለሚገኝ ፎካል ለተሰኘ የዕውቀት እና የነፃነት ፋውንዴሽን የተበረከተው የዛይድ ሰብዓዊ ወንድማማችነት ሽልማት ዋና ዓላማ ይህ መሆኑ ታውቋል። ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ የዩክሬኑ ጦርነት ከመጀመሩ አስቀድመው ይፋ ባደረጉት የቪዲዮ መልዕክታቸው፣

የአቡ ዳቢ አልጋ ወራሽ የሆኑትን ሼክ ሞሃመድ ቢን ዛይድ አል ናህያንን አመስግነው፣ የሰብዓዊ ወንድማማችነት ሰነድ ይዘት በማስተዋወቅ እና ለሼክ ዛይድ ቢን ሱልጣን አል ናህያን ክብር የሰጠውን የሰብአዊ ወንድማማችነት ከፍተኛ ኮሚቴን አመስግነዋል። እ. አ. አ. በ 1971 የተባበሩት አረብ ኢምሬቶች ምሥረታ ዋና ዓላማ “ሰብዓዊነትን፣ እድገትን እና በሰላም አብሮ መኖርን ለማስፋፋት ቁርጠኛ ለሆኑት ግለሰቦች እና ተቋማት እውቅና እና ሽልማት” ለመስጠት መሆኑ ይታወሳል።

የፍቅር እና የመቻቻል እሴቶችን ማሳደግ

ሽልማቱ "ለፍትህ፣ ለአብሮነት እና ለወንድማማችነት የሚጥሩትን ሁሉ ለመደገፍ እና ለማመስገን" መሆኑን ያስታወሱት ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ በአረብ ኤምሬቶች፣ አቡ ዳቢ ከተማ እ. አ. አ. የካቲት 4/2019 ዓ. ም. የጸደቀው የሰብዓዊ ወንድማማችነት ሰነድ "ከፍቅር የሚገኙ የመቻቻል እና የወንድማማችነት እሴቶችን" በተግባር ለመግለጽ ጥረት የሚያደርጉትን በሙሉ ለመደገፍ እና ለማመስገን መሆኑን አስረድተዋል። ቅዱስነታቸው በማከልም ሽልማቱ "በሰላም አብሮ መኖርን የሚያበረታታ እና በልዩ ልዩ ሃይማኖቶች መካከል የጋራ ውይይቶች እንዲካሄዱ ለማድረግ እና በማኅበራዊ አገልግሎት ውስጥ ፍሬያማ የሆኑ የትብብር ምልክት እና ሌሎች እርምጃዎችም እንዲወስዱ የሚያበረታታ" መሆኑን አስረድተዋል።

ዮርዳኖስ የመቻቻል እና የአብሮነት ምሳሌ አገር ናት

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ እ. አ. አ ለ2022 ዓ. ም. የዛይድ ሽልማት አሸናፊዎች፣ በተለይም የዮርዳኖስ ንጉሣዊ ቤተሰብ ያሳየውን ቁርጠኝነትን አስታውሰው፣ "ብዙ ቁጥር ያላቸው ስደተኞችን በመቀበል፣ አብሮ የመኖር እሴቶችን በማስተዋወቅ፣ በልዩ ልዩ ሃይማኖታዊ ወጎች መካከል በሚደረግ ውይይት፣ መድልዎ በመዋጋት፣ ወጣቶችን እና ሴቶች ነፃ ለማውጣት" ያደረገውን ጥረት አስታውሰው፣ ዮርዳኖስ የመቻቻል እና አብሮ የመኖር ምሳሌ አገር መሆኗን ገልጸው፣ ሽልማቱ የዮርዳኖስ ሕዝብ ምንም እንኳን በብዙ ችግሮች ውስጥ የሚገኝ ቢሆንም በቆራጥነት እና በድፍረት ዓመጽን በመቃወም የሰላም መንገድን ለመከተል ላደረገው ጥረት ማበረታቻ መሆኑን አስረድተዋል።

መልካም ለሆነው የሄይቲ ሕዝብ መጸለይ

በሄይቲ ለሚገኝ ፎካል የተሰኘ የዕውቀት እና የነፃነት ፋውንዴሽን የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክታቸውን የላኩት ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ የሄይቲን ሕዝብ በጸሎታቸው እንደሚያስታውሱት ገልጸዋል። ለፋውንዴሽኑ መስራች ለሆኑት ለክቡር አቶ ሚቸል ፒየር-ሉዊስ በላኩት የምስጋና መልዕክታቸው፣ ለሰብዓዊ መብቶች ጥበቃ በተለይም ለአዲሱ ትውልድ ትምህርትን እና ስልጠናን ለማዳረስ ላደረጉት ቁርጠኝነት አመስግነዋል።

ለሄይቲ የተሻለ የወደፊት ተስፋን ለመስጠት በሕዝቦቿ መካከል ወዳጅነት እና ጥረት እንደሚያስፈልግ የገለጹት ቅዱስነታቸው፣ የሄይቲ ሕዝብ በብዙ የተፈጥሮ አደጋዎች የተጎዳ እና በማኅበራዊ ችግሮች ምክንያት መከራ የደረሰበት መሆኑንም አስታውሰዋል። መልካም፣ ትጉ እና ሃይማኖተኛ የሆነውን የሄይቲ ሕዝብ በጸሎት መርዳት እንደሚያስፈልግ አደራ ብለዋል።

01 March 2022, 16:23