ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፣ በኢዮቤልዩ ዓመት የምሕረት በር ሲከፍቱ የሚያሳይ (ከማኅደር ምስል) ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፣ በኢዮቤልዩ ዓመት የምሕረት በር ሲከፍቱ የሚያሳይ (ከማኅደር ምስል) 

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ እ. አ. አ 2025 ለሚከበረው የኢዮቤልዩ ዓመት በጸሎት እንድንዘጋጅ አሳሰቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እ. አ. አ በ2025 ዓ. ም. ለሚከበረው የኢዮቤልዩ ዓመት መላው ምዕመናን በጸሎት እንዲዘጋጁ፣ በቅድስት መንበር የስብከተ ወንጌል አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ፕሬዚዳንት ለሆኑት ለብጹዕ ሞንሲኞር ሪኖ ፊዚኬላ በላኩት መልዕክት አሳስበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን  

ቅዱስነታቸው በመልዕክታቸው፣ የኢዮቤልዩ ዓመት ወይም በዓል ምንጊዜም በቤተክርስቲያን ሕይወት ውስጥ ታላቅ መንፈሳዊ እና ማኅበራዊ ጠቀሜታ ያለው መሆኑን አስረድተዋል። የመጀመርያው ቅዱስ ዓመት ከተከበረበት፣ እ. አ. አ ከ1300 ዓ. ም ጀምሮ “የእግዚአብሔር ቅዱስ እና ታማኝ ሕዝብ፣ ልዩ የጸጋ ስጦታ የሆነው ሙሉ የኃጢአት ይቅርታ የሚገኝበት የእግዚአብሔር ምሕረት መግለጫ መሆኑንም አስታውሰዋል።

የመጀመሪያዎቹ 25 ዓመታት

በ2000 ዓ. ም የተከበረው ታላቁ የኢዮቤልዩ ዓመት ቤተክርስትያንን ወደ ሦስተኛው ሺህ ዓመት ያሸጋገራት መሆኑን ቅዱስነታቸው አስታውሰዋል። የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ፣ ሁሉም የክርስትና እምነት ተከታዮች ታሪካዊ ልዩነታቸውን ወደ ጎን አድርገው የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሁለት ሺህ ኛ የልደት ዓመትን በኅብረት እንዲያከብሩት በማሰብ በጉጉት የጠበቁት እንደ ነበር አስታውሰዋል። “የአዲሱ ክፍለ ዘመን የመጀመሪያዎቹ ሃያ አምስት ዓመታት እየተቃረቡ ሲመጡ ሕዝበ ክርስቲያኑ ቅዱሱን ዓመት በሐዋርያዊ በረከቶች በመሞላት እንድንለማመደው እና እንድንኖረው የሚያስችል ዝግጅት ለማድረግ ተጠርተናል” ብለዋል።

ለአደጋ ተጋላጭ የሆኑትን ማስታወስ

በቅርብ ዓመታት ውስጥ በዓለማችን የተከሰተው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በእያንዳንዱ አገር ላይ ጉዳት ማስከተሉን በማስታወስ በጻፉት መልዕክታቸው፣ “የተስፋ ነጋዲያን” የሚል መሪ ሃሳብ ለኢዮቤልዩ ዓመት መምረጣቸው ታውቋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከዚህም ጋር በማያያዝ፣ በዓለም አቀፍ የወንድማማችነት ስሜት፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ወንዶችን እና ሴቶችን፣ ወጣቶችን እና ሕጻናትን ለአደጋ የዳረጋቸውን ድህነት ማየት ካልተቻለ ሰብዓዊ ክብርም አደጋ ላይ መውደቁን አስታውሰዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ይህን መነሻ በማድረግ፣ “በተለይ ትውልድ አገራቸውን ጥለው እንዲሰደዱ የተደረጉት በርካታ ስደተኞችን አስታውሰዋል። በመሆኑም በዚህ የኢዮቤልዩ ዝግጅት ወቅት የድሆች ድምፅ ሊደመጥ እንደሚገባ እና ምድራችን የምታቀርብልን ፍሬ ለሁሉም ሰው ተደራሽ እንዲሆን ማድረግ ያስፈልጋል ሲሉ አስረድተዋል።

በኅብረተሰብ ውስጥ የሚንጸባረቁ ሃሳቦች

የኢዮቤልዩን መንፈሳዊ ገጽታ አስፈላጊነት የተናገሩት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ የኢዮቤልዩ በዓል "መለወጥን የሚጠይቅ" እና የማኅበረሰባችንን መሠረታዊ ገጽታዎች እንደ አንድ ሙሉ አካል የያዘ መሆኑን አስረድተው፣ ለጋራ መኖሪያ ምድራችን እንክብካቤ እና ልዩ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ገልጸው፣ ወጣቶችን እና ሕፃናትን ጨምሮ በቁጥር በርካታ የሆኑ ወንዶች እና ሴቶች ፍጥረትን መንከባከብ የእምነታቸው ዋነኛ መግለጫ መሆኑን በመገንዘብ ለእግዚአብሔር እና ለፈቃዱ መታዘዛቸውን ገልጸዋል።

በአደራ የተሰጠ ኃላፊነት

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ በቅድስት መንበር የስብከተ ወንጌል አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ፕሬዚዳንት ለሆኑት ለብጹዕ ሞንሲኞር ሪኖ ፊዚኬላ በላኩት መልዕክት፣ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤቱ ቅዱስ የኢዮቤልዩ ዓመትን በጥልቅ እምነት፣ ሕያው ተስፋ እና በጎ አድራጎት የሚከበርበትን ተስማሚ መንገዶች የማፈላለግ ኃላፊነት እንዳለበት በአደራ አሳስበዋል።  

ቅዱስነታቸው በመቀጠል፣ ወደ ኢዮቤልዩ ዓመት የሚደረገው መንፈሳዊ ጉዞ ቤተክርስቲያን የተጠራችበትን የጋራ ጉዞ በመግለጽ እና በማረጋገጥ፣ በልዩነት መካከል የአንድነት ምልክት እና መሣሪያ ለመሆን እንደሆነ አስረድተዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ መልዕክታቸውን ሲያጠቃልሉ እንደገለጹት፣ የኢዮቤልዩ ዝግጅት ወቅትን በጸሎት ለማሳለፍ ፍላጎት ያላቸው መሆኑን ገልጸው፣ በእግዚአብሔር ፊት ቀርበን እርሱን ለማድመጥ እና ልንሰግድለት ያለንን ፍላጎት እንድናድስ አደራ ብለዋል።

12 February 2022, 14:17