ፈልግ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በቫቲካን በጥር 20/2014 ዓ.ም ከዓለም አቀፉ የካቶሊክ ሚዲያ ማሕበር አባላት ጋር በተገናኙበት ወቅት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በቫቲካን በጥር 20/2014 ዓ.ም ከዓለም አቀፉ የካቶሊክ ሚዲያ ማሕበር አባላት ጋር በተገናኙበት ወቅት  (Vatican Media)

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ ለካቶሊክ ሚዲያ አባላት እውነታዎችን ፈትሹ፣ ሁልጊዜ ሰዎችን አክብሩ ማለታቸው ተገለጸ!

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በጥር 20/2014 ዓ.ም ከዓለም አቀፉ የካቶሊክ ሚዲያ ማሕበር አባላት ጋር ተገናኝተው በተወያዩበት ወቅት ቅዱስነታቸው በወቅቱ ባደርጉት ንግግር ጋዜጠኞች ሁል ጊዜ እውነታዎችን በማጣራት እና ግለሰቦችን በማክበር ለእውነት ታማኝ እንዲሆኑ አሳስበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

የኮቪድ-19 ወረርሽኝን በተመለከተ የተሳሳቱ መረጃዎች እየተሰራጩ በመጡበት በአሁኑ ወቅት፣ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ጋዜጠኞች በተለይም የካቶሊክ ሚዲያ ባለሙያዎች የሀሰት ዜናን ለሚያዘጋጁ እና ለሚያሰራጩ ሰዎች አክብሮት በተሞላው መልኩ እውነታውን እንዲረዱ ማደረግ ያስፈልጋል፣ የሚዘግቡትን እውነታ እንዲያረጋግጡ መምከር ተገቢ ነው ብለዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ከዓለም አቀፉ የካቶሊክ ሚዲያ ማሕበር አባላት ጋር አርብ ጥር 20/2014 ዓ.ም በተገናኙበት ወቅት የግንኙነት እና የእውነት ጭብጥ ላይ ተንተርሰው ንግግር አድርገዋል።

በአሌቴያ እና አይ ሚዲያ የተሰኙ ሁለት የዜና ድህረ ገፆች እና ቬሪፊካት፣ የእውነታ አረጋጋጭ ኤጀንሲ የሚተዳደሩት ማሕበራት እ.አ.አ በ2021 ዓ.ም መጀመሪያ ላይ “የካቶሊክ ፋክት ቼኪንግ” ድህረ ገጽን አቋቁመዋል።

የሐሰት ዜናን ማጋለጥ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ስለ ኮቪ -19 ክትባቶች እና ከነሱ ጋር የተያያዙ የስነምግባር ጥያቄዎች ላይ “የውሸት ዜና እና ከፊል ወይም አሳሳች መረጃን” ለመዋጋት እነዚህ ድርጅቶች እያደረጉ የሚገኙትን ጥረት አድንቀዋል።

የማሕበሩ አባላት በኤፒዲሚዮሎጂ “epidemiology” (ሰለ በሽታ ወረርሽኝ መነሻ ምክንያትና ቁጥጥር የሚያጠና የህክምና ትምህርት ዘርፍ ነው)፣ ቴዎሎጂ “theology” (የነገረ መለኮት አስትምህሮ) ባዮ ሄቲክስ “bioethics” (የስነ ሕይወት ሳይንስ ስነ ምግባር) ባለሙያዎችን በስሩ ያካተተ ሳይንሳዊ ኮሚቴዎችን ያካትታል።

ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በሰዎች ላይ የመገናኛ ብዙኃን ተጽዕኖ እየጨመሩ መምጣቱን እና ስለዚህ ጋዜጠኞች ጥብቅ ዘዴን መጠቀም አለባቸው ብለዋል ።

“ኮሙዩኒኬተሮች እውነታዎችን በጥንቃቄ መመልከት፣ ትክክለኛነታቸውን ማረጋገጥ፣ የመረጃ ምንጮቻቸው ላይ ወሳኝ ግምገማ ማድረግ እና በመጨረሻም ውጤቶቻቸውን ማስተላለፍ አለባቸው። የኃላፊነት ሸክሙ የበለጠ የሚከብደው፣ እንደተለመደው፣ ዘጋቢው የሚያስፈልገው የአንድን ጉዳይ ቀላል መረጃ እንዲያቀርብ ብቻ ሳይሆን፣ አንድምታውን እንዲያብራራ አስተያየትና ለፍትሃዊ ግምገማ የሚያስፈልጉትን ነገሮች ለማቅረብ  ጭምር ነው። (ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ጳውሎስ ስድስተኛ የስብሰባ አዳራሽ ውስጥ እ.ኤ.አ. በ1972 ዓ.ም ለዓለም የኮሙንኬሽን ቀን ያስተላለፉት መልእክት)

በአንድነት መቆም 

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በመቀጠል የካቶሊክ ሚድያ ማሕበር አባላት “ለእውነት አንድ ላይ” የመቆም ግብ ላይ አንጽኖት ሰጥተው ተናግረዋል።

የማሕበሩ የመጀመሪያው መሪ ቃል “በአንድነት” መቆም የሚለውን በተመለከተ ቅዱስነታቸው ሲናገሩ እርስ በርስ የሚገናኙ እና እውቀትን የሚካፈሉ ክርስቲያን አውታረ መረብ መፍጠር እንደሚገባ የገለጹ ሲሆን በዚህ ዝግባብ “የመጀመሪያ ምስክርነት” እየሰጡ ነው ብሏል።

ዓለማችንን ከወረርሽኙ ጋር እያስጨነቀ ያለውን “ኢንፎደሚክ” (ኢንፎደሚክ በጣም ብዙ መረጃዎችን ያቀፈ የመረጃ ፍሰት ሲሆን በሽታ ወይም አንድ ወረርሽኝ በሚከሰትበት ጊዜ በዲጂታል እና በተለያዩ የዜና ማሰራጫ አውታሮች፣ እንዲሁም በአካል እና በቃላት የውሸት ወይም አሳሳች መረጃን ማሰራጨት ማለት ነው። ጤናን ሊጎዱ የሚችሉ ግራ መጋባት እና አደገኛ ባህሪያትን ያስከትላል። በጤና ጉዳዮች ላይ በሚሰሩ ባለስልጣናት ላይ አለመተማመንን ያስከትላል እና የህዝብ ጤና ምላሽን ያዳክማል) በተመለከተ ቅዱስነታቸው በግንኙነቱ ወቅት በቁጭት የተናገሩ ሲሆን “በፍርሀት ላይ የተመሰረተ የእውነታ መዛባት፣ ይህም በአለም አቀፍ ማህበረሰባችን ውስጥ ያልተከሰቱ ነገሮችን እንደተከሰቱ አድርጎ በማቅረብ የተጭበረበረ አስተያየት እንዲፈጠር ምክንያት ሆኗል” በማለት ተናግሯል።

"በተገቢ ሁኔታ መረጃ ማግኘት፣ ሁኔታዎችን በሳይንሳዊ መረጃ ላይ ተመስርተው እና በውሸት ዜና ተንተርሶ ሳይሆን እውነታውን ለመረዳት መሞከር ሰብአዊ መብት ነው። ትክክለኛ መረጃ ከምንም በላይ መሳሪያ ለሌላቸው፣ ለደካሞች እና ለአደጋ ተጋላጭ ለሆኑት ሰዎች ሁሉ መረጋገጥ አለበት” ሲሉ በጽኖት ገልጸዋል።ለመቃወም ሳይሆን

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ወደ ሁለተኛው ቃል ዘወር ሲሉ ክርስቲያኖች ምንጊዜም “ግፍንና ውሸትን የሚቃወሙ ነገር ግን ሁልጊዜ ለሰዎች ተቆርቋሪ” እንደሆኑ አስታውሰዋል።

የሀሰት መረጃን በሚዋጉበት ጊዜም የካቶሊክ ሚዲያ ህብረት አባላት “በመረጃ እና በሰዎች መካከል ያለውን መሠረታዊ ልዩነት” በጭራሽ አዛብተው እንዳይመለከቱ አሳስቧቸዋል።

"የሐሰት ዜና ውድቅ መሆን አለበት፣ ነገር ግን ግለሰቦች ሁል ጊዜ መከበር አለባቸው፣ ምክንያቱም ያለ ሙሉ ግንዛቤ ወይም ሃላፊነት ብዙ ጊዜ ያምናሉና" ብለዋል።

ይህ አካሄድ ክርስቲያን ጋዜጠኞች “በአጻጻፍ ዘይቤ ወንጌላውያን፣ ድልድይ ሠሪዎች፣ ሰላም ፈጣሪዎች፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ እውነትን ፍለጋ” ላይ አተኩረው እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል። ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በተጨማሪም “ለችግሮች መፍትሄ ለማምጣት” በሂደት ላይ ላለው ከሳይንስ ጋር ግጭት መፍጠር እና ፊደዝም “fideism” (እምነት ከምክንያታዊነት የጸዳ ነው፣ ወይም ምክንያት እና እምነት እርስበርስ ጠላት እንደሆኑ እና እምነት ወደ ተለየ እውነቶች ለመድረስ እምነት የላቀ መሆኑን የሚያረጋግጥ ንድፈ ሀሳብ ነው። ፊዴዝም የሚለው ቃል ከላቲን የእምነት ቃል የመጣ ሲሆን በጥሬ ትርጉሙም "እምነት" ማለት ነው” ለይተን መመልከት ይኖርብናል ሲሉ ተናግረዋል።

"እውነታው ሁልጊዜ ከምናስበው በላይ ውስብስብ ነው እናም ሰዎች የሚያነሷቸውን ጥርጣሬዎች፣ ጭንቀቶች እና ጥያቄዎች ማክበር አለብን” ብለዋል ቅዱስነታቸው።

ስለዚህ ክርስቲያን ጋዜጠኞች “ሰላምና ምክንያታዊ በሆነ መንገድ” መልስ በመስጠት ሰዎችን አጅበው እንዲሄዱ አሳስቧል።

በእውነት ወደ ሕብረት መጓዝ

ከዚያ በኋላ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ የቡድኑን ዓላማ የማጣራት ዓላማን ለማበረታታት የመጨረሻውን  “እውነት” የሚለውን የማሕበሩን መሪ ቃል የወሰዱ ሲሆን ለጥቅም ወይም ለንግድ ትርፍ እንዳንሰጥ አስጠንቅቀዋል። “የማንኛውም የውሸት መድሀኒት ራሳችንን በእውነት ማንጻት ነው። ለክርስቲያኖች፣ እውነት በነገሮች ላይ ከመፍረድ ጋር የተያያዘ ፅንሰ-ሀሳብ በጭራሽ አይደለም። እውነት ሕይወትን በአጠቃላይ ይመለከታል” ሲሉ ተናግረዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በወረርሽኙ የተጎዱትን በማስታወስ እና ለድርጅቱ አባላት ማበረታቻ በመስጠት ለካቶሊክ ሚዲያ ማሕበር አባላት ያደረጉትን ንግግር አጠናቀዋል። “ለእውነት ማገልገል ማለት ኅብረትን የሚያበረታቱና የሁሉንም ጥቅም የሚያጎናጽፉ ነገሮችን መፈለግ እንጂ የሚያገሉ፣ የሚከፋፍሉ እና የሚቃወሙ አይደሉም” ብሏል።

28 January 2022, 13:03