ፈልግ

በብራዚል ውስጥ ኃይለኛ ዝናብ ካስከተለው የጎርፍ አደጋዎች መካከል አንዱ በብራዚል ውስጥ ኃይለኛ ዝናብ ካስከተለው የጎርፍ አደጋዎች መካከል አንዱ   (Washington Alves/Light Press)

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በጎርፍ አደጋ የተጎዱ የብራዚል ሕዝቦችን በጸሎታቸው አስታወሱ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ በብራዚል ውስጥ ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ ሲወርድ የቆየው ኃይለኛ ዝናብ ባስከተለው የጎርፍ አደጋ ጉዳት የደረሰባቸውን ሕዝቦች በጸሎታቸው አስታውሰዋል። በትናንትናው ዕለት በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ከተሰበሰቡት ምዕመናን ጋር ያቀረቡትን የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት ከማጠቃለላቸው በፊት፣ በብራዚል ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች በጎርፍ አደጋ የተጎዱ ሰዎችን በጸሎታቸው አስታውሰዋል። በተለይም የአደጋው ለተጎጂዎች እና ቤተሰቦቻቸው እንዲሁም ቤት ንብረታቸው የወደመባቸውን በሙሉ በጸሎታቸው አስታውሰዋል። በእነዚህ አካባቢዎች ሰብዓዊ ዕርዳታን በማድረስ ላይ ለሚገኙ ድርጅቶች እና ግለሰቦች የእግዚአብሔርን ድጋፍ ለምነዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በብራዚል ባይያ እና ሚናስ ግሬይስ ግዛቶች በሚገኙ በበርካታ ከተሞች ላይ ላለፉት ሁለት ወራት የጣለው ኃይለኛ ዝናብ ለበርካታ የሰው ሕይወት መጥፋት እና በሽዎች ለሚቆጠሩት መፈናቀል ምክንያት መሆኑ ታውቋል። የአፈር መደርመስ እና የወንዞች ሙላት ከፍተኛ ጉዳቶችን ማስከተሉ ሲነገር የድንገተኛ አደጋ መከላከያ እና መቆጣጠሪያ ሠራተኞች የውሃ ግድቦችን ለመቆጣጠር ጥረት በማድረግ ላይ መሆናቸው እና በአደጋው ለተጎዱት አካባቢዎች የዕርዳታ ቁሳቁሶችን በማድረስ ላይ መሆናቸው ታውቋል።

ባለፉት ጥቂት ቀናት ብቻ በአደጋው 25 ሰዎች ሕይወታቸውን ማጣታቸው የተነገረ ሲሆን፣ በርካታ መኖሪያ ቤቶች፣ ትምህርት ቤቶችን ጨመሮ በርካታ የአገልግሎት መስጫ ተቋማትም መፍረሳቸው ታውቋል። በብራዚል ውስጥ ቡራሚኞ በተባለ አካባቢ እ. አ. አ ጥር 25/2019 ዓ. ም. በጣለው ኃይለኛ ዝናብ ግድብ ሞልቶ በመደርመሱ ምክንያት 270 ሰዎች ሕይወታቸውን ማጣታቸው ይታወሳል።

ዕርዳታን የማቅረብ ጥረት

በብራዚል ውስጥ አደጋው በተከሰቱባቸው አካባቢዎች ለሚገኙ ሰዎች ዓለም አቀፍ የዕርዳታ ድርጅቶች ዕርዳታን ለማቅረብ መጀመራቸው ታውቋል። ካሪታስ ኢንተናሲዮናሊስ የተሰኘ ካቶሊካዊ ዕርዳታ አቅራቢ ድርጅትም ከብራዚሉ አቻ ድርጅት ጋር በመተባበር ሰብዓዊ ዕርዳታን ማቅረብ መጀመሩ ታውቋል። ከዚህ በተጨማሪ ሰሜን አሜሪካ እና የአውሮፓ ኅብረትም የመጀመሪያ ዕርዳታዎቻቸውን መላካቸው ታውቋል። በብራስልስ የሚገኝ የአውሮፓ ኅብረት ጽሕፈት ቤት ለአስቸኳይ ዕርዳታ ካስቀመጠው ገንዘብ አንድ ሚሊዮን ዩሮ መለገሱ ታውቋል። የአውሮፓ ኅብረት ኮሚሽን ዕርዳታውን ባቀረበበት ወቅት እንዳስገነዘበው፣ የገንዘብ ዕርዳታው በአደጋው ለተጎዱት አካባቢዎች የምግብ፣ የንፁህ ውሃ፣ የመጠለያ እና የቤት እቃዎችን በማቅረብ አስቸኳይ ፍላጎቶችን ለመሸፈን ያለመ መሆኑን አስታውቋል። ሌሎች ሰብአዊ ዕርዳታቸውን የሚያቀርቡ አጋር ድርጅቶችም በአካባቢዎቹ ሊከሰት የሚችል የወረርሽኝ ስጋት ለመቅረፍ ህዝቡን በጤና አገልግሎት የሚደግፉ መሆኑን አክሎ አስታውቋል።               

17 January 2022, 16:24