ፈልግ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ “የእግዚአብሔር ፍቅር ለእኛ ቅርባችን፣ ታዳጊያችን እና ርኅሩህ ነው!”

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ትናንት እሑድ ጥር 8/2014 ዓ. ም. በቫቲካን በሚገኘው ቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተገኙ ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የአገር ጎብኚዎች በዕለቱ በተነበበው ቅዱስ ወንጌል ላይ በማስተንተን ስብከታቸውን አቅርበዋል። ቅዱስነታቸው በዚህ አስተንትኖአቸው “የእግዚአብሔር ፍቅር ለእኛ ቅርባችን፣ ታዳጊያችን እና ርኅሩህ መሆኑን አስረድተዋል።

ክቡራት እና ክቡራን አድማጮቻችን ቅዱስነታቸው በትናንትናው ዕለት ያቀረቡትን የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ ትርጉም ሙሉ ይዘት እንደሚከተለው ቀርቧል። 

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“ውድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ!

በዚህ እሁድ የተነበበው ቅዱስ ወንጌል በገሊላ ቃና ሠርግ ላይ ኢየሱስ ክርስቶስ ውሃን ወደ ወይን ጠጅ በለወጠው ጊዜ ሙሽሮች መደሰታቸውን ይናገራል። ኢየሱስ ክርስቶስ ይህን የተአምራት ሁሉ መጀመሪያ የሆነውን ተአምር በገሊላ ቃና ከተማ በመፈጸም ኃይሉን በገለጠ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ በእርሱ ያመኑበትን ታሪክ መበግልጽ ያበቃል። (ዮሐ. 2:11) ኢየሱስ ክርስቶስ አስደናቂ ሥራን ማከናወኑ ተአምር መሆኑን ወንጌላዊው ዮሐንስ በጽሑፉ እንዳልተናገረው እናስተውላለን። ነገር ግን በገሊላ ቃና ላይ ምልክት መታየቱ የደቀ መዛሙርቱን እምነት እንደቀሰቀሰው ጽፏል። በቅዱስ ወንጌል አገላለጽ “ምልክት” ማለት ምን ማለት ነው?

በቅዱስ ወንጌል አገላለጽ ምልክት ማለት ለተከናወነው ድርጊት ኃይለኛነት ትኩረት ሳይሰጥ ነገር ግን የእግዚአብሔር ፍቅር እንዲገለጥ ምክንያት መሆኑን የሚገልጽ ነው። የእግዚአብሔር ፍቅር ሁል ጊዜ ለኛ ቅርብ፣ ታዳጊያችን እና ርኅሩህ መሆኑን ያስተምረናል። የኢየሱስ ክርስቶስ የመጀመሪያው ምልክት የተፈጸመው ሁለቱ ምሽሮች በሕይወታቸው ውስጥ በጣም አስፈላጊ በሆነው ቀን ችግር ባጋጠማቸው ጊዜ ነው። ልክ በሠርጉ መሃል ለግብዣው አስፈላጊ የሆነው ወይን ጠጅ በጠፋበት ጊዜ በእንግዶች ነቀፌታ ምክንያት ሙሽሮች ደስታቸው ሊጠፋ በተቃረበበት ጊዜ ነበር። አንድ ሠርግ በውሃ ብቻ ሲደገስ አስቡት! ምን ያህል አሳፋሪ ሊሆን እንደሚችል፣ ባልና ሚስት ምን ዓይነት ስሜት ሊሰማቸው እንድሚችል አስቡት!

ክስተቱ አሳፋሪ መሆኑን በመገንዘብ ችግሩን ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ ያቀረበችው እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ናት። ኢየሱስ ክርስቶስ ሁኔታውን ተገንዝቦ የሠርጉ ታዳሚዎች በማይገነዘቡት መንገድ አስተካከለው። ኢየሱስም አገልጋዮቹን “ጋኖቹን ውሃ ሙአቸው” አላቸው። በዚህን ጊዜው ወሃው ወደ ወይን ተለወጠ። እግዚአብሔር ወደ እኛ ቀርቦ ሥራውን የሚሠራው በዚህ ዓይነት መንገድ ነው። የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት የተሠራውን ነገር ተረድተዋል። ለኢየሱስ ክርስቶስ ምስጋና ይድረሰውና የሠርጉ ግብዣ ይበልጥ ውብ ሆነ። ደቀ መዛሙርቱ ኢየሱስ ክርስቶስ በድብቅ ተአምር ያደረገበትን መንገድ ተመልክተው ነበር። ኢየሱስ በዚህ ዓይነት መንገድ በስውር የረዳናል። በዚያች ቅጽበት ጥሩ የወይን ጠጅ በመቅረቡ ምክንያት የተመሰገነው ሙሽራው ነበር። ከአገልጋዮቹ በቀር ስለወይን ጠጁ ማለቅ ያወቀ ማንም አልነበረም። የእምነት ፍሬ በውስጣቸው ማደግ የጀመረው በዚህ መንገድ ነበር። እግዚአብሔርን ያመኑት እና የእግዚአብሔር ፍቅር በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል መገለጡን የተረዱት በዚህ መንገድ ነበር።  

ኢየሱስ ክርስቶስ የፈጸመው የመጀመሪያ ምልክት በኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ ውስጥ በአስደናቂ የፈውስ ተግባር ሳይሆን ተራ ሰዎች ለሚያስፈልጋቸው ተጨባጭ ነገር ምላሽ የሰጠበት እርምጃ መሆኑ እንዴት የሚያስደስት ነገር ነው። በጥንቃቄ እና በፀጥታ የተደረገ ተአምር ነበር ልንለው እንችላለን። ኢየሱስ ክርስቶስ እኛን ለመርዳት ዘወትር ዝግጁ ነው። ለእነዚህ “ምልክቶች” ትኩረት የምንሰጥ ከሆነ፣ በፍቅሩ በመሸነፍ ደቀ መዛሙርቱ እንሆናለን።

በገሊላ ቃና የነበረውን ሠርግ ልዩ የሚያደርግ ሌላ ባህሪ አለ። ዛሬም ቢሆን በአጠቃላይ በበዓል መጨረሻ ላይ የሚቀርብ የመጠጥ ጥራት ጥሩ አይሆንም። ይህ በሚሆንበት ጊዜ የበዓሉ ታዳሚዎች የሚቀርብላቸው መጠጥ ጥሩ ይሁን ወይም በመጠኑም ቢሆን የተበረዘ መሆኑን ለይተው ማወቅ ይከብዳቸዋል። ኢየሱስ ክርስቶስ የበዓሉ ፍጻሜ ይበልጥ በተሻለ የወይን ጠጅ እንዲጠናቀቅ አድርጎታል። ይህ በምሳሌያዊ አነጋገር፣ እግዚአብሔር ለእኛ የተሻለ ነገር እንደሚያደርግልን እና ደስተኞች እንድንሆን እንደሚፈልግ ይነግረናል። እርሱ ለደግነቱ ገደብ የለውም፤ ለሥራው የአገልግሎት ክፍያ አይጠይቀንም። በሙሽሮቹ ላይ የታሰበ ድብቅ ዓላማ ወይም የቀረበላቸው ጥያቄ የለም። ኢየሱስ ክርስቶስ በምሽሮቹ ልብ ውስጥ እንዲቀመጥ ያደረገው ደስታ ፍጹም እና ያልተበረዘ ነበር።

ስለዚህ ጠቃሚ የሚሆነን አንድ ልምድ ልጠቁማችሁ እፈልጋለሁ። ዛሬ፣ ጌታ በሕይወታችን ያከናወናቸውን ምልክቶች በመፈልግ ትዝ የሚሉንን ለመግለጽ እንሞክር። “እግዚአብሔር በሕይወታችን ውስጥ የፈጸማቸው ምልክቶች የትኞቹ እንደሆኑ እራሳችንን እንጠይቅ። እርሱ አብሮ እንደሆነ የሚገልጹ ፍንጮች የትኞቹ ናቸው? እንደሚወደን ለማሳየት ብሎ ያደረጋቸው ምልክቶችስ የትኞቹ ናቸው? እግዚአብሔር ፍቅሩን እንድንለማመድበት ስለፈቀደን ስለ እነዚያ አስቸጋሪ ወቅቶች እናስብ። ርህራሄው እንዲሰማን የፈቀደን ልዩ የፍቅር ምልክቶች የትኞቹ እንደሆኑ እራሳችንን እንጠይቅ። እግዚአብሔር ከእኔ ጋር እንደሆነ የገባኝ መቼ ነው? ጥበቃው እና ርኅራሄው ብዙ እንደሆነ የተረዳሁት መቼ ነው? እያንዳንዳችን በግል የሕይወት ታሪካችን ውስጥ እነዚህ ጊዜያት እንዳሉን እናውቃለን። እነዚህን ምልክቶች እንፈልግ፣ እናስታውሳቸው። የእርሱን ቅርብነት እንዴት አገኘሁት? ልቤን በታላቅ ደስታ እንዴት ሞላው? እግዚአብሔር ከእኛ ጋር መሆኑን እና የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን አማላጅነት የተለማመድንባቸውን ጊዜያት እናስታውስ። በገሊላ ቃና ሠርግ ላይ በትኩረት ስትከታተል የነበረች እናታችን ቅድስት ድንግል ማርያም፣ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር መሆኑን የሚገልጹ ምልክቶችን በሕይወታችን ውስጥ አክብረን እንድንይዝ ዘወትር ትረዳን።”

17 January 2022, 16:14