ፈልግ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ የጣሊያን ሕንጻ ተቋራጭ ማኅበራት ተወካዮችን በቫቲካን በተቀበሏቸው ጊዜ ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ የጣሊያን ሕንጻ ተቋራጭ ማኅበራት ተወካዮችን በቫቲካን በተቀበሏቸው ጊዜ 

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ለአካባቢ ጥበቃ እና ለሠራተኛ ደህንነት የበለጠ ኃላፊነት እንዲሰማ አሳሰቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ጥር 12/2014 ዓ. ም. በጣሊያን ውስጥ የሚገኙ የሕንጻ ተቋራጭ ማኅበራት ተወካዮችን በቫቲካን ተቀብለው ንግግር አድርገውላቸዋል። ቅዱስነታቸው ለማኅበራቱ ተወካዮች ባደረጉት ንግግር፣ ስለ ሥራቸው አስፈላጊነት፣ ለሁሉም ሰው ደህንነቱ የተጠበቀ የሥራ ሁኔታ ማረጋገጥ አስፈላጊ መሆኑን አስረድተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ሐሙስ ጥር 12/2014 ዓ. ም. በቫቲካን ለተቀበሏቸው በጣሊያን የሚገኙ የሕንጻ ተቋራጭ ማኅበራት የሚያከብሩትን 75ኛ ዓመት የምሥረታን በዓልን ምክንያት በማድረግ ባደረጉት ንግግር፣ አጋጣሚው “ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ወደ ጣሊያን የተመለሰውን ታሪክ የሚስታወስ አጋጣሚ ነው” ብለዋል። አክለውም የግንባታ ተቋራጮች ብሔራዊ ማኅበር እ. አ. አ በ 1946 በኮንስትራክሽን ዘርፍ የተሰማሩ፣ በሁሉም ደረጃ የሚገኙትን የጣሊያን ኩባንያዎችን የሚወክል የሥራ ፈጣሪዎች ማኅበር መመስረቱን አስታውሰዋል።

ሠራተኞችን የሚያበረታቱ እሴቶች

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለግንባታ ዘርፍም ቢሆን አሁን የምንገኝበት ወቅት አስቸጋሪ ነው ብለው፣ በእነዚህ ጊዜያት ተነሳሽነትን ማሳደግ ከመሠረታዊ ምርጫዎች መካካል አንዱ በመሆኑ አስፈላጊ ነው ብለዋል።  በመቀጠልም ድርጅቶችን ከሚያበረታቱ የቅዱስ ወንጌል ትምህርቶች መካከል ፉክክርን፣ ግልጽነትን፣ ኃላፊነትን እና ዘላቂነትን የሚመለከቱ እሴቶች መኖራቸውን፣ ከእነዚህም መካከል ጥቂቶቹ ስነ-ምግባር፣ ሕጋዊነት እና ደህንነት መሆናቸውን ገልጸዋል።

ኢየሱስ ክርስቶስ በስብከቶቹ መልዕክቶችን በቀላሉ ለማስተላለፍ የግንባታ ዘይቤን መጠቀሙን ያስታወሱት ቅዱስነታቸው፣ የሉቃስ ወንጌል ከሥራ ይልቅ በወሬ ጊዜን የሚያሳልፉ ሰዎች የግብዞችን እና የሰነፍ ሰዎች ባህሪን ገሃድ ያደርጋል ብለው፣ የመሐንዲሶችን የግንባታ ጥበብ በአሸዋ ላይ ቤት ከሚገነቡ ሰዎች ጋር ያነጻጸሩት ቅዱስነታቸው፣ በእርግጥ ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ትላልቅ ሕንጻዎች ባይናግርም ነገር ግን በወንዝ ላይ የሚገነቡ ቤቶችን መጠቆሙን ተናግረው፣ ጥሩ ግንበኛ እንዲህ ዓይነት ቤት ወዲያው በጎርፍ ሊወሰድ እንደሚችል ያውቃል ማለቱንም አስታውሰዋል።

ኢየሱስ ክርስቶስ የተናገረውን ምሳሌ ያብራሩት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ የምሳሌው ሌላኛው ገጽታ ሲያስረዱ፣ “ወደ እኔ የሚመጣ እና ቃሌንም ሰምቶ የሚፈጽም ማንን እንደሚመስል ልንገራችሁ፤ እርሱ በጥልቅ ቆፍሮ ቤቱን በጽኑ አለት ላይ የመሠረተውን ሰው ይመስላል፤ ጎርፍ መጥቶ ያንን ቤት ገፋው፤ ነገር ግን በጽኑ መሠረት ላይ ስለተሠራ ሊያነቃንቀው አልቻለም።” (ሉቃ. 6:47-48) ይህ ምሳሌ የበለጠ አስደሳች የሚሆነው እንዲህ ዓይነቱ ግንበኛ ቤቱን ወደፊት ከሚመጣው የጎርፍ መጥለቅለቅ እንደሚከላከል ስናስብ መሆኑን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ተናግረዋል።

የሥራ ፉክክር እና ግልጽነት

በመቀጠል ቀደም ሲል የጠቀሷቸውን “የሥራ ፉክክር እና ግልጽነት” በሚሉት እሴቶች ላይ ተወያይተዋል። አንዱ ሌላውን በፉክክር ያሸንፋል ብሎ ስለሚያስብ ወይም የሌላው ሽንፈት በኢኮኖሚ አፈጻጸሙ ላይ እንዲካተት ስለሚያደርግ “ፉክክር ብቻውን በቂ አይደለም” ብለዋል። ይህ በሚሆንበት ጊዜ የሥራ ገበያው በሚገባ እንዲሠራ የሚያስችል ማኅበራዊ እምነት እንደሚጎዳ ገልጸው፣ ፉክክር የበላይነት እና የመገለል ፍላጎት ከመሆን ይልቅ ሥራን በአግባቡ ለመሥራት እና ለማሻሻል የሚያበረታታ መሆን አለበት ብለዋል። በውሳኔ አሰጣጥ ሂደቶች እና በኢኮኖሚያዊ ምርጫዎች ላይ ግልጽነት አስፈላጊ የሚሆነው ለዚህ እንደሆነ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አስረድተዋል። አክለውም ግልጽነት ኢ-ፍትሃዊ ፉክክርን ለማስቀረት እንደሚያግዝ እና ይህም በኢኮኖሚ እና በሠራተኛው ጉልበት መስክ ሥራ ማጣት ፣ ሕገወጥ ሥራ እንዲስፋፋ ያለ ክፍያ መሥራትን እንደሚያበረታታ አስረድተዋል።

ኃላፊነት እና ዘላቂነት እንዲኖር

ስለ "ኃላፊነት እና ዘላቂነት" የተናገሩት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ከዚህ በፊት ስለ ዘላቂ አካባቢያዊ እና ሰብዓዊ ደህንነት ብዙ ሲወራ አይሰማም ብለው፣ እያንዳንዱን ስነ-ምህዳር መልሶ የማልማት አቅም እንደሚያካትት አብራርተዋል። በሕንጻውም ዘርፍ ለሰዎች ደህንነት የሚያገለግሉ ቁሳቁሶችን መጠቀም አስፈላጊ እንደሆነ፣ ሆኖም ግን በኅብረት አካባቢን ከብዝበዛ መከላከል ያስፈልጋል ብለዋል።

ስነ-ምግባር፣ ህጋዊነት እና ደህንነት

በመጨረሻም ሥነ ምግባርን፣ ሕጋዊነትን እና ደህንነትን አስመልክተው ባደረጉት ንግግር፣ ያለፈው ዓመት በርካታ ሰዎች በሥራ መስክ ለሞት አደጋ መዳረጋቸውን አስታውሰው፣ የእነዚህን ሰዎች ቁጥር መጥቀስ ብቻ ሳይሆን ውድ የሰው ነፍሳት መሆናቸውን ማወቅ ያስፈልጋል ብለዋል። “በሕንጻ ሥራዎች አካባቢም እንዲሁ ቸል የማንችላቸው አሳዛኝ ክስተቶች ተመልክተናል" ያሉት ቅዱስነታቸው፣ በሚያሳዝን ሁኔታ በሥራ መስክ ለሠራተኛ የሚደረገውን የደህንነት ማረጋገጫ እንደ ገንዘብ ወጪ አድርጎ መመልከት ስህተት መሆኑን አስረድተዋል። ሰዎች እውነተኛ ሀብት እንደሆኑ እና ያለ ሰው የሠራተኛ ኃይል፣ የንግድ እና የኤኮኖሚ እንቅስቃሴ ሊኖር እንደማይችል አስረድተዋል።

በአስተማማኝ ሁኔታ መሥራት ሁሉም ሰው የዕለት እንጀራውን እንዲያገኝ ያስችላቸዋል ብለው፣ የሥራን ክብር ከተጠበቀ ጥራቱ እና ውበቱ እንደሚጨምር እርግጠኞች መሆን እንደሚቻል አስረድተዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ለጣሊያን የሕንጻ ተቋራጭ ማኅበራት ተወካዮች ያደረጉትን ንግግር ከማጠናቀቃቸው በፊት፣ የሠራተኞች ጠባቂ ወደ ሆነው ቅዱስ ዮሴፍ ባቀረቡት ጸሎት እገዛውን ጠይቀው፣ የማኅበራቱ ተወካዮች በጸሎታቸው እንዲያስታውሷቸው አደራ ብለዋል።

21 January 2022, 08:57