ፈልግ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በበረራ ላይ እያሉ ከጋዜጠኛ ጋር ቃለ ምልልስ አድርገዋል ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በበረራ ላይ እያሉ ከጋዜጠኛ ጋር ቃለ ምልልስ አድርገዋል 

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ ይቅርታን በማድረግ በክርስቲያኖች ውስጥ አንድነት እንዲያድግ አሳሰቡ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ ከኅዳር 23-27/2014 ዓ. ም. ድረስ በቆጵሮስ እና በግሪክ ያደረጉትን 35ኛ ዓለም አቀፍ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን ፈጸመው ወደ ቫቲካን መመለሳቸውን የቅድስት መንበር ጋዜጣዊ መግለጫ ክፍሉ አስታውቋል። ቅዱስነታቸው ወደ ሮም ባደረጉት ጉዞ ወቅት በሁለቱ አገራት ያካሄዱትን ሐዋርያዊ ጉብኝት ጨምሮ በልዩ ልዩ ርዕሠ ጉዳዮች ላይ ከጋዜጠኞች ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች መልስ ሰጥተዋል። ከጥያቄዎች መካከል፣ ስደትን፣ የአውሮፖ ኅብረት የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ልደት በዓል በማስመልከት ባወጣው አዲስ ሰነድ፣ በዓለም ዙሪያ በምትገኝ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ዘንድ በመካሄድ ላይ ስለሚገኝ ሐዋርያዊ ሲኖዶስ እና በሁለቱ አገራት ማለትም በቆጵሮስ እና በግሪክ ባደረጓቸው ሐዋርያዊ ጉብኝቶች ወቅት ከቤተክርስቲያን አባቶች ጋር ያደረጓቸውን ውይይቶች የሚመለከቱ ጥያቄዎች ቀርበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የሐዋርያዊ ጉብኝታቸው ሁለተኛ አገር ከሆነችው ግሪክ ወደ ሮም ሲመለሱ፣ በጉብኝታቸው ወቅት ስደተኞችን እና ከኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን ጋር ያለውን የወንድማማችነት ግንኙነት አስመልክተው ማብራሪያ ሰጥተዋል። ቅዱስነታቸው የአቴንስ እና የመላው ግሪክ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ከብጹዕ አቡነ ኢሮኒሞስ ዳግማዊ ጋር አቴንስ በሚገኘው የቅድስት መንበር ቋሚ ጽሕፈት ቤት ውስጥ ተገናኝተው ተወያይተዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በክርስቲያኖች መካከል ለተፈጠረው መከፋፈል ሁሉ በተለይም ከካቶሊክ ቤተክርስቲያን ጋር ለተፈጠረው ልዩነት ይቅርታ መጠይቃቸውን ገልጸዋል።

“እግዚአብሔር ይቅርታን ለማድረግ በፍጹም አይታክትም” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ እግዚአብሔርን ይቅርታ የማንጠይቅ ከሆነ፣ ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን ይቅርታ መጠየቅ ይጨንቀናል ብለዋል። አሁን በምንኖርበት ዓለም ውስጥ ይቅርታን እንደ ውርደት የሚቆጥሩ ብዙ ሰዎች መኖራቸውን ያስታወሱት ቅዱስነታቸው፣ ይህን ስሜት አስወግደን ይቅርታን የማድረግም ሆነ የመጠየቅ ፍላጎት ሊኖረን ያስፈልገናል ብለዋል። በዓለም ዙሪያ ብዙ ነገሮች እየተከሰቱ ባሉበት፣ የብዙ ሰው ሕይወት እየጠፋ ባለበት፣ ብዙ ጦርነቶች እየተካሄዱ ባሉበት ዘመን እንዴት ይቅርታ አንጠይቅም? ብለዋል።

የክርስቲያኖችን አንድነት በማስመልከት ሃሳባቸውን የገለጹት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ “እኛ ሁላችን የአንድ እግዚአብሔር ልጆች ነን” ብለው፣ ቤተክህነት እና ምዕመናን በማለት በአገልግሎት እና በጥሪ ዘርፍ ልዩነት ቢኖርም በእግዚአብሔር መንጋዎች መካከል ሁል ጊዜ አንድነት አለ ብለዋል። የቤተክርስቲያንን ሲኖዶሳዊነት ስንገልጽ ክርስቲያኖች በሙሉ እርስ በእርስ በመደማመጥ፣ በአንድ ጎዳና በኅብረት የሚጓዙበት አካሄድ እንደሆነ ቅዱስነታቸው ስረድተው፣ ይህ የክርስቲያኖች ኅብረት ጉዞ በምስራቅ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያናት መካከል ከረጅም ዘመናት ጀምሮ ተጠብቆ የኖረ ባሕል እንደሆነ አስረድተዋል። በሌላ በኩል የላቲን ሥርዓተ አምልኮን በምትከተል ካቶሊዊት ቤተ ክርስቲያን ዘንድ የቤተክርስቲያን ሲኖዶሳዊነት ተረስቶ የነበረ ቢሆንም ከ54 ወይም ከ56 ዓመታት በፊት የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ጳውሎስ ስድስተኛ ባደረጉት ጥረት ብርታትን በማግኘት የቤተክርስቲያን ሲኖዶሳዊነት ለመለማመድ እና በአንድነት ለመራመድ ጉዞ የተጀመረ መሆኑን አስረድተዋል።

በዘመናት ውስጥ አምባ ገነናዊነትን የሚያንጸባርቁ ብዙ አስተሳሰቦች መስተናገዳቸውን ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳስዳት ፍራንችስኮስ፣ እነዚህ አስተሳሰቦች ሙሉ በሙሉ ያልተወገዱ በመሆናቸው በታሪክ ውስጥ በማንኛውም ጊዜ   ሊንጸባረቁ እንደሚችሉ አስገንዝበዋል። የአውሮፓ ኅብረት የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ልደት በዓልን በማስመልከት በዓሉ እንዳይከበር የሚገልጽ ሃሳብ የያዘው ሰነድን በማስመልከት ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ ቅዱስነታቸው ሲመልሱ፣ እርሳቸው እንደሚያምኑት ሃሳቡ የቅኝ ግዛት ርዕዮተ ዓለም አካሄድ እንደሆነ አስረድተው፣ የአውሮፓ ኅብረትም በኅብረቱ ውስጥ የተካተቱ የእያንዳንዱን አገር ሉዓላዊነት እና የአስዳደር ሥርዓቶችን ማክበር ይኖርበታል ብለዋል። የአውሮፓ ኅብረት፣ በወንድማማችነት የእያንዳንዱን አገር ማንነት የሚያከብር አንድነት እንዳለው የገለጹት ቅዱስነታቸው፣ ዛሬ ላይ በታየው የርዕዮተ ዓለም ቅኝ ግዛት አዙሪት ሰለባ እንዳይሆን አስጠንቅቀው፣ የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ልደት በዓልን በማስመልከት ይፋ ያደረገው ሰነድም የርዕዮተ ዓለም ቅኝ ግዛትን የሚያንጸባርቅ አስተሳሰብን የያዘ መሆኑን ገልጸዋል።

ዴሞክራሲ የስልጣኔ ውጤት እና ሃብት በመሆኑ ሊጠበቅ እንደሚገባ ያሳሰቡት ቅዱስነታቸው፣ ዴሞክራሲን መጠበቅ ብቻ ሳይሆን ዴሞክርሲን በመለማመድ ላይ ያሉ አገራት ሊከበሩ እና ሌሎችንም ሊያከብሩ እንደሚገባ አሳስበዋል። ዴሞክራሲ ሁለት አደጋዎች የተደቀኑበት መሆኑን የገለጹት ቅዱስነታቸው፣ የመጀመሪያው ሕዝባዊነት ሲሆን ባለፈው ክፍለ ዘመን ሕዝባዊነት በናዚ ሥርዓትም ሲሰበክ እንደነበር አስታውሰው፣ ሥርዓቱ ሕዝባዊ ከመሆኑ ፈንታ ከሕዝባዊነት ጋር ምንም ግንኙነት በሌላቸው አምባ ገነናዊ አስተሳሰቦች ይመራ እንደነበር አስረድተው፣ የዛሬዎቹ መንግሥታት ከሕዝብ ጋር ምንም ግንኙነት የሌለውን ጎዳና እንዳይከተሉ አስጠንቅቀዋል።

ሰደትን በተመለከት ለቀረበላቸው ጥያቄ መልስ የሰጡት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ አገራት ድንበሮቻቸውን በማጠር ስደተኞች እንዳይገቡ ማድረግ የየተለመደ መጥቷል ብለው፣ በአውሮፓ ውስጥ ከረጅም ዓመታት በፊት የነበረውን የስደት ሁኔታ አስታውሰው፣ የአውሮፓ አገራት ዛሬ ያንን ሁሉ ዘንግተው ድንበሮቻቸውን  ለመዝጋት መነሳታቸው ታሪካቸውን መዘንጋታቸውን ያመላክታል ብለዋል። እያንዳንዱ መንግሥት በግዛቱ መቀበል የሚችለውን የስደተኛ ቁጥር በመወሰን ወደ ድንበሩ ደርሰው በር የሚያንኳኩ ስደተኞችን በክብር ተቀብሎ የማስተናገድ፣ ደህንነቱን የመጠበቅ፣ ዓላማውን የማሳደግ እና ከሚኖርበት ማኅበረሰብ ጋር ተቀላቅሎ የሚኖርበትን መንገድ ማመቻቸት ይኖርበታል ብለዋል። ወደ ቆጵሮስ፣ ወደ ግሪክ እና ወደ ጣሊያን ግዛቶች የሚደርሱ ስደተኞችን ተቀብሎ ለማስተናገድ በአገሮች መካከል መልካም ፍላጎት እንደማይታይ ገልጸዋል።

07 December 2021, 15:37