ፈልግ

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ የቆጵሮስ ቤተክርስቲያን ለውጥን እና ልዩነትን በትዕግስት እንድትቀበል ጥሪ አደረጉ! ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ የቆጵሮስ ቤተክርስቲያን ለውጥን እና ልዩነትን በትዕግስት እንድትቀበል ጥሪ አደረጉ! 

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ የቆጵሮስ ቤተክርስቲያን ለውጥን እና ልዩነትን በትዕግስት እንድትቀበል ጥሪ አደረጉ!

ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ በቆጵሮስ እና ግሪክ ባደረጉት የመጀመሪያ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው ጳጳሳት፣ ካህናት፣ ገዳማዊያን/ገዳማዊያት እና ለካቴኪስቶች ባደረጉት ንግግር በወንድማማችነት፣ በይቅርታ፣ በምሕረት እና በግልጽነት መንፈሳዊ አገልግሎታቸውን እንዲያከናውኑ ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን ተግባራቸውን በትዕግስት እንዲወጡ ቅዱስነታቸው አክለው ገልጸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

በቆጵሮስ ላለው እውነታ በጣም የሚስማማው ባሕሪይ “ትዕግስት” እንደ ሆነ የገለጹት ቅዱስነታቸው ቤተ ክርስቲያን “በለውጥ ምክንያት እንድትበሳጭ እና እንድትጨነቅ የማትፈቅድ መሆን አለባት፣ ነገር ግን በእርጋታ አዲስነትን የምትቀበል እና ሁኔታዎችን በወንጌል ብርሃን የምትረዳ” መሆን ይኖርባታል ብለዋል።።

ይህ የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ራዕይ እና ማበረታቻ ለካቶሊክ ቀሳውስት፣ ገዳማዊያን እና ገዳማዊያት እንዲሁም ለካቴኪስቶች በቆጵሮስ ሐዋርያዊ ጉብኝት ባደረጉበት በመጀመሪያው ቀን ላይ በኒቆሲያ በሚገኘው የጸጋ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ካቴድራል ውስጥ ባደረጉት የመጀመሪያው ንግግር ላይ ያቀረቡት ጥሪ ነው።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በቆጵሮስ ለተገኙት የሁሉም የካቶሊክ ሥርዓተ አምልኮ ተወካዮች - የላቲን ሥርዓት፣ የማሮናውያን እና የአርሜኒያ ካቶሊክ ተወካዮች ንግግር ሲያደርጉ - ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ የልዩነታቸውን ብልጽግና በመደገፍ “ሳይታክቱ ወይም ተስፋ ሳይቆርጡ” እንዲጸኑ አሳስቧቸዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በቆጵሮስ የሚያደርጉትን ጉብኝት በጀመሩበት ወቅት እርሳቸውን ለመቀበል ከመጡ ሰዎች መካከል የቆጵሮስ ማሮናዊት ሊቀ ጳጳስ ሰሊም ስፌር፣ የአንጾኪያ ማሮናዊ ፓትርያርክ ቤቻራ ቡትሮስ ራኢ እና የኢየሩሳሌም የላቲን ስርዓት ፓትርያርክ የሆኑት ፒየርባቲስታ ፒዛባላ ይገኙበታል።

ሊባኖስ

የማሮናዊት ቤተ ክርስቲያን ተወካዮች ሰላምታ ባቀረቡበት ወቅት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በአሁኑ ጊዜ ሊባኖስን እያሽመደመደው ስላለው ቀውሶች ስላሳሰባቸው እንዲህ ብለዋል፡- “የደከሙና በዓመፅና በችግር የተፈተኑ ሰዎችን ስቃይ እመለከታለሁ። ከዚች ሀገር ልብ ሊባል የሚገባውን የሰላም ፍላጎት በጸሎቴ ሁሌም አስባለሁ” ብለዋል።

የቅዱስ በርናባስ ትዕግስት

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳቱ ወደ መልእክታቸው ዋና ክፍል በገቡበት ወቅት የቆጵሮስን ደጋፊ ቅዱስ በርናባስን ውርስ ላይ ያሰላሰሉ ሲሆን እርሱም የእምነት እና የጥበብ ሰው ነበር፣ አመለካከቱም እጅግ በጣም በትዕግስት የተሞላ “ወደ ፊት ለመቀጠል ያለውን ትዕግስት፤ እስካሁን ድረስ ወደማይታወቁ ሰዎች ሕይወት ውስጥ ለመግባት ትዕግስት፣ ለፍርድ ሳይቸኩሉ አዲስ የሆነውን ለመቀበል ትዕግስት ያደርግ ነበር” ይህንን ከእርሱ መማር ይኖርብናል ብለዋል።

ቅዱስነታቸው መልእክታቸውን ሲቀጥሉ ቅዱስ በርርናባስ የማስተዋል ትዕግስትን፣ ሌሎች ባህሎችንና ወጎችን "ለማጥናት" የአብሮነት ትዕግስት አስፈላጊ መሆኑን አስተምሮናል ያሉ ሲሆን አዲስ መጤዎችን እጃቸውን በመያዝ ከእነርሱ ጋር በመነጋገር እና በመደጋገፍ እንዴት መርዳት እንደ ምንችል አሳይቷል ማለታቸው ተገልጿል።

የቆጵሮስ ቤተ ክርስቲያን ክፍት ክንዶች

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በቅዱስ ወንጌል ብርሃን አዲስነትን እና አስተዋይ ሁኔታዎችን በመቀበል በዚሁ መንገድ እንዲቀጥሉ ለተሳታፊዎች የገለጹ ሲሆን በዚህ መንገድ እንዲቀጥሉ አበረታተዋል።

በደሴቲቱ ላይ የሚኖሩ ሰዎች “ከዓለም ዳርቻዎች የመጡ አዳዲስ ወንድሞችንና እህቶችን” በደስታ ተቀብለው በፍቅር በማቀፍ እንክብካቤ በማድረግ ላይ ስለሚገኙ አመሰግናለሁ ብለዋል። በዚህ መንገድ የምታከናውኑትን ተግባራት እደግፋለሁ በማለት አክለው ገልጸዋል።

በመላው አውሮፓ ለሚገኝ ቤተክርስቲያን መልእክት

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ መልእክታቸውን ሲቀጥሉ “ይህ በመላው አውሮፓ ለምትገኘው ቤተክርስቲያን በእምነት ቀውስ ውስጥ የምትገኝ ጠቃሚ መልእክት ነው። ግልፍተኛ እና ማዕበል፣ ያለፈውን ጊዜ መናፈቅ ወይም ጠበኛ መሆን ብዙም አይጠቅምም። ይልቁንም የዘመኑን ምልክቶችና የቀውሱን ምልክቶች እያነበብን ወደፊት መራመድ አለብን” ብሏል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ አያይዘውም ካህናት ለትውልድ ወንጌልን በማወጅ በትዕግስት እንዲጸኑ፣ ጳጳሳትም ከካህናቶቻቸው ጋር በመቀራረብና ከሌሎች ወንድሞችና እህቶች ጋር በመገናኘት በትዕግስት ሁሉንም ነገር እንዲያሳልፉ አደራ ብለዋል።

የይቅርታና የምሕረት ባህልን እንዲያሳድጉና ለተለያዩ መንፈሳዊ ስሜቶች፣ የተለያዩ እምነቶችን የመግለጫ መንገዶችን፣ የተለያዩ ባህሎችን ለመረዳት የሚያስችል ጆሮና ልብ እንዲኖራቸው የጠየቁ ሲሆን ቤተክርስቲያን፣ “ሁሉንም ነገር ወደ ወጥነት መቀነስ አትፈልግም፣ ነገር ግን በትዕግስት ለሁሉም አዎንታዊ ለሆኑ ባሕሎች ራሳችንን ክፍት ማደረግ አለብን” ብሏል።

የወንድማማች ቤተ ክርስቲያን አስፈላጊነት

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በመቀጠል ቅዱስ ባርናባስ ከጳውሎስ ጋር የተገናኘበትን አስፈላጊነት አጉልተው ገልጸዋል፣ “የጓደኝነት እና የህይወት መጋራት አቀራረብ” እንደ ነበራቸው የገለጹት ቅዱስነታቸው በቦታው የተገኙት ሰዎች የሌሎችን ታሪክ እንዲወስዱ አሳስቧቸዋል “የሰዎችን ባሕል እና ይኑሮ ዘዴ አስቀድመን በተሳሳተ ሁኔታ ተረድተን እነርሱን ከማንቋሸሽ ይልቅ ጊዜ ወስደን ስለእነርሱ ባሕል እና ወግ በትዕግስት በማጥናት የደከሙትን እና በተለያዩ ነገሮች የቆሰሉትን ሰዎች እንደ ደጉ ሳምራዊ ተሸክመን ልንረዳቸው ይገባል፣ ይህ ወንድማማችነት ነው፣ ከትዕግስት ቀጥሎ የሚመጣ ሁለተኛው ቃላችን ነው ብለዋል።

የሜዲትራኒያንን ምሥራቃዊ አካባቢ ለመስበክ አብረው የተጓዙት ሁለቱ ሐዋርያት አለመግባባታቸውና የየራሳቸውን መንገድ የሄዱበትን ጊዜ አስታውሷል።

ነገር ግን አሉ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ንግግራቸውን ሲቀጥሉ ምንም እንኳን የተለያየ ሐሳብ ቢኖራቸውም፣ በመካከላቸው ምንም ዓይነት ሽኩቻ እንዳልነበረው ገልጸው “በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ወንድማማችነት ማለት ይህ ነው፡ ስለ ራእዮች፣ ግንዛቤዎች እና የተለያዩ ሀሳቦች መሟገት እንችላለን” ነገር ግን የወንድማማችነት መንፈስ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል።

“በዓለማችን የወንድማማችነት ወኪል የሆነች አንዲት በወንድማማችነት መንፈስ የተሞላች ቤተ ክርስቲያን ለማየት እንፈልጋለን” በማለት ልዩነት የማንነት ጠንቅ እንዳይሆን ጥሪ አቅርበዋል።

ሁላችንም ወንድማማቾች እና እህተማማቾች ነን!

እኛ ሁላችን በአንድ አባት የምንወደድ ወንድሞች እና እህቶች ነን ያሉት ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ የቆጵሮስ ቤተክርስቲያን በሜዲትራኒያን ባህር አከባቢ መገኘቷን በመጥቀስ “በታሪክ የበለፀገ ባህር ፣ የበርካታ ስልጣኔዎች መፍለቂያ የነበረ ባህር የነበር ሲሆን ዛሬም ቢሆን ከየትኛውም የዓለም ክፍል የተውጣጡ ብዙ ግለሰቦች፣ ሕዝቦችና ባህሎች አሁንም በደሴቲቷ ላይ በመስፈር ላይ እንደሆኑ አክለው ገልጸዋል።

በማጠቃለያም ሁሉም ሰው እና አውሮፓ በአጠቃላይ “ለወደፊት ለሰው ልጅ የሚስማማ ሁኔታዎችን ለመገንባት፣ መለያየትን ለማስወገድ፣ ግንቦችን ለማፍረስ፣ ለአንድነት ማለም እና መስራት እንዳለብን ለዚህም በጋራ መረባረብ አለብን” በማለት አሳስበዋል። እርስ በርሳችን መስማማት፣ መተሳሰር እና እንደ ወንድም እና እህት ሁላችንም እንድንቀራረብ ካሳሰቡ በኋላ ቅዱስነታቸው ንግግራቸውን አጠቃለዋል።

03 December 2021, 16:31