ፈልግ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በቆጵሮስ የሚያደረጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝት መፈጸማቸው ተገለጸ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከኅዳር 23 እስከ 27/2014 ዓ. ም ድረስ በቆጵሮስ እና በግሪክ ሐዋርያዊ ጉብኝት በማካሄድ ላይ መሆናቸው ይታወቃል። ቅዱስነታቸው የጉብኝታቸው መጀመሪያ አገር በሆነችው ቆጵሮስ ያደረጉትን የሁለት ቀናት ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን ፈጽመው በዛሬው ዕለት ወደ ግሪክ ገብተዋል። በቆጵሮስ በነበራቸው ቆይታ ከአገሪቱ ከፍተኛ የመንግሥት መሪዎች፣ የሐይማኖት አባቶች እና ክርስቲያን ማኅበረሰብ ጋር ተገናኝተው መልዕክታቸውን ማስተላለፋቸው ታውቋል። ትናንት አርብ ኅዳር 24/2014 ዓ. ም በኒቆስያ የቆጵሮስ ኦርቶዶክስ ሊቀ ጳጳስ ከሆኑት ከብፁዕ አቡነ ክሪሶስቶሞስ 2ኛ ጋር ከተገናኙ በኋላ ከቅዱስ ሲኖዶስ ጋርም በኒቆስያ በሚገኝ የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ካቴድራል መገናኘታቸውን መዘገባችን ይታወሳል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ለኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ባስተላለፉት መልዕክት፣ በካቶሊክ እና በኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት መካከል ያለው የጋራ ትስስር የቅዱስ በርናባስን አርአያነት የተከተለ ጥልቅ ውይይት ለማድረግ ፍላጎት እንዳላቸው ገልጸዋል። በቆጵሮስ መገኘታቸውም “የጋራ ሐዋርያዊ ተልዕኮ” እንዳለ ያስታውሰኛል ያሉት ቅዱስነታቸው፣ ሐዋርያው ጳውሎስ ቆጵሮስን አልፎ ወደ ሮም መጓዙን አስታውሰው “እኛም የዚያው ሐዋርያዊ ቅንዓት ወራሾች ነን” ብለው፣ “የቅዱስ ወንጌል መንገድ በሆነው በዛው ጎዳና የምንራመድ ከሆነ የበለጠ ወንድማማችነትን እና ሙሉ አንድነትን እየፈለግን እንጓዛለን” ብለዋል።

በቆጵሮስ ባደረጉት ሁለት የሐዋርያዊ ጉብኝት ቀናት፣ በርካታ ምዕመናን የተገኙበትን የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ማሳረጋቸውም የተገለጸ ሲሆን በሥነ-ሥርዓቱ ወቅት ባሰሙት ስብከት፣ የቆጵሮስ ሰዎች ብዙን ጊዜ ከምንገኝበት ተመሳሳይ ጨለማ ነፃ ለመውጣት ሦስት እርምጃዎችን እንዲከተሉ በማለት ከማርቆስ ወንጌል የተወሰደውን የሁለቱ ዓይነ ስውራን ምሳሌ በመጥቀስ ከጨለማ መውጣት የምንችለው በጋራ ስንቆም ብቻ እንደ አስረድተው፣ እነርሱም

አንደኛ፣ “በታሪክውስጥ የልብንና የዓለምን ጨለማ የሚያበራ ብርሃን ኢየሱስ በመሆኑ ልባችንን እንዲፈውስ እድል በመስጠት ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ መቅረብ እንደሚያስፈልግ፣ ሁለተኛ፣ የውስጣችን ዓይነ ስውርነት ብቻችን ልንሸከመአው ስለማንችል እርስ በርሳችን መደጋገፍ፣ ህመማችንን መጋራት እና በጉዞአችን የሚያጋጥመንን ፈተና በጋራ መጋፈጥ እንደሚያስፈልግ፣ ሦስተኛ፣ ከማርቆስ ወንጌል በተነበበው በዕለቱ ንባብ ሁለቱ ዓይነ ስውሮች በኢየሱስ ክርስቶስ ከተፈወሱ በኋላ “ምሥራቹን ለአካባቢው ሰዎች ማዳረስ” መጀመራቸውን ቅዱስነታቸው አስታውሰው፣ እኛም ኢየሱስ ክርስቶስን ካገኘን በኋላ፣ ለምናገኛቸው በሙሉ ያለ ፍርሃት የኢየሱስ ምስክሮች እንድንሆን ያስፈልጋል" ብለዋል።

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በቆጵሮስ ያደረጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝት ፈጽመው የጉብኝታቸው ሁለተኛ አገር ወደ ሆነችው ግሪክ ከመጓዛቸው አስቀድመው ለቆጵሮስ ፕሬዚደንት ለክቡር አቶ ኒቆስ አናስታዲያደስ የቴለግራም መልዕክት ልከዋል። ቅዱስነታቸው በዚህ መልዕክታቸው ከመላው የቆጵሮስ ሕዝብ እና ከአገሪቱ ፕሬዚደንት ለተደረገላቸው መልካም አቀባበል ምስጋናቸውን ገልጸው፣ ለአገሪቱ ሰላም እና ብልጽግና ጸሎት እንደሚያደርጉ ገልጸው፣ ለመላው የቆጵሮስ ሕዝብ መልካምን ተመኝተው የሁሉን ቻይ እግዚአብሔር ቡራኬን ልከውላቸዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ቅዳሜ ኅዳር 25/2014 ዓ. ም. ማለዳ ላይ በቆጵሮስ ከሚገኘው ላርናካ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ተነስተው ወደ ግሪክ አቴንስ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ መድረሳቸው ታውቋል። ቅዱስነታቸው በውጭ ሀገራት በሚያደርጉት 35ኛ ዓለም አቀፍ ሐዋርያዊ ጉብኝት ላይ መሆናቸው ይታወቃል።  ቅዱስነታቸው ቆጵሮስን ከመሰናበታቸው አስቀድመው በዚያች አገር ለሚገኝ የቅድስት መንበር እንደራሴ ጽሕፈት ቤት የቅዱስ ዮሴፍ ምስል፣ ወደ ቆጵሮስ ያደረጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝት የሚያስታውስ ሜዳሊያ እና የሐዋርያዊ ስልጣናቸው አርማ ያለበት ምስል በስጦታ ማቅረባቸው ታውቋል።

ተስፋ የሞላበት ሐዋርያዊ ጉብኝት

ቆጵሮሳዊት ተወላጅ ኢሌኒ፣ ቅዱስነታቸው በቆጵሮስ ያደረጉትን የሁለት ቀናት ሐዋርያዊ ጉብኝት በማስታወስ ለቫቲካን የዜና አገልግሎት በሰጠችው አስታያየት፣ የቅዱስነታቸው ሐዋርያዊ ጉብኝት ለአገሪቱ ታላቅ ክብር ከመሆኑ በተጨማሪ መልዕክታቸውን ተስፋ ያለበት መሆኑን ገልጻለች። “ይህ የተስፋ፣ የትሕትና፣ የሰላምና የአንድነት መልዕክት ብርታት ይሆነናል” ስትል ተናግራለች፣ በመሆኑም የአገሪቱ የመንግሥት ባለስልጣናትም ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ባስተላለፉት መልዕክት ላይ ማሰላሰል እንደሚቀጥሉ ያላትን እምነት ገልጻለች።

04 December 2021, 17:36