ፈልግ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ በታላቁ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ባዚሊካ ውስጥ ጸሎት ሲያቀርቡ ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ በታላቁ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ባዚሊካ ውስጥ ጸሎት ሲያቀርቡ 

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ ለቆጵሮስ እና ለግሪክ ጉብኝታቸው የማርያምን እርዳታ ለመኑ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ ከኅዳር 23 – 27/2014 ዓ. ም. ድረስ በቆጵሮስ እና በግሪክ የሚያደርጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝት ከመጀመራቸው በፊት ረቡዕ ኅዳር 22/2014 ዓ. ም. ከሰዓት በኋላ ሮም ከተማ ውስጥ ወደሚገኝ ታላቁ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ባዚሊካ ደርሰው ጸሎታቸውን አቅርበዋል። በሁለቱ አገራት በሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት ወቅት የእመቤታችን ጥበቃ እና እርዳታ መለመናቸውን እና በእመቤታችን ማርያም ቅዱስ ምስል ሥር የአበባ ጉንጉን ማስቀመጣቸውን የቅድስት መንበር ጋዜጣዊ መግለጫ ክፍሉ አስታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ከአብያተ ክርስቲያናት ጋር ያለው ግንኙነቶች

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሐሙስ ኅዳር 23/2014 ዓ. ም. በጀመሩት ሐዋርያዊ ጉብኝት ወቅት አስቀድመው ለሦስት ቀናት ቆጵሮስን ከጎበኙ በኋላ ከቅዳሜ ኅዳር 25 - 27/2014 ዓ. ም. በግሪክ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን እንደሚያካሂዱ የጉዞአቸው መርሃ-ግብር አመልክቷል። ቅዳሜ ዕለት የቆጵሮስ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያም መሪ ከሆኑት ከሊቀ ጳጳስ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ክሪሶስቶሞስ ዳግማዊ እና ከቤተክርስቲያኒቱ ቅዱስ ሲኖዶስ ጋር እንደሚገናኙ ታውቋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በግሪክ በሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት ወቅት በዋና ከተማዋ አቴንስ ከሚገኙ ከብጹዕ ወቅዱስ ኢሮኒሞስ ዳግማዊ 2ኛ ጋር እንደሚገናኙ ታውቋል። ቅዱስነታቸው በሚጎበኟቸው ሁለቱም አገራት ክርስቲያን ምዕመናን መካከል አብዛኞቹ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች መሆናቸው ታውቋል።

ለስደተኞች ትኩረት መስጠት

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በቆጵሮስ የሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት፣ ሁለተኛው የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ጉብኝት ሲሆን፣ ከዚህ በፊት የቀድሞ ር. ሊ. ጳ በነዲክቶስ 16ኛ እ. አ. አ በ2010 በቆጵሮስ ሐዋርያዊ ጉብኝት ማድረጋቸው ይታወሳል። ቅዱስነታቸው በግሪክ በሚያደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት ወቅት በሌስቦ ደሴት የሚገኙ ስደተኞችን እና ጥገኝነት ጠያቂዎችንም እንደሚጎበኙ ታውቋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በግሪክ ሐዋርያዊ ጉብኝት ሲያደርጉ ይህ ለሁለተኛ ጊዜ ሲሆን የመጀመሪያን እ. አ. አ በ2016 ዓ. ም. ማድረጋቸው የሚታወስ ነው። በግሪክ ባደረጉት የመጀመሪያ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው ወቅት ከቁንስጥንጥንያው ፓትሪያርክ ከብጹዕ ወቅዱስ በርቶሎሜዎስ ቀዳማዊ ጋር መገናኘታቸው ሲታወስ፣ በወቅቱ በግሪክ ያደረጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝት ፈጽመው ወደ ቫቲካን ሲመለሱ በመጠለያው ከነበሩ ስደተኞች መካከል ለሦስት የሶርያ ስደተኛ ቤተሰቦች የጥገኝነት ፍቃድ በመስጠት ይዘዋአቸው መመለሳቸው ይታወሳል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቆጵሮስ እና በግሪክ በሚያደርጓቸው ሐዋርያዊ ጉብኝት ወቅት ከሚያነሷቸው የመወያያ ርዕሦች መካከል አንዱ ስደትን የሚመለከት ሲሆን፣ አጋጣሚው ለስደተኞች ያላቸውን አጋርነት እና ቅርበት ለመግልጽ እድል የሚሰጣቸው መሆኑ ታውቋል።  

02 December 2021, 08:40