ፈልግ

በፖቱጋል የአርጋቬ ሀገረ ስብከት ወጣቶች ዓመታዊ በዓላቸውን ሲያከብሩ በፖቱጋል የአርጋቬ ሀገረ ስብከት ወጣቶች ዓመታዊ በዓላቸውን ሲያከብሩ 

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ “ወጣቶች ሕይወታቸው በኢየሱስ የታገዘ በመሆኑ ፍርሃት ሊሰማቸው አይገባም!”

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ ኅዳር 12/2014 ዓ. ም. በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ውስጥ በመሩት መስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ-ሥርዓት ዓመታዊው የክርስቶስ ንጉሥ በዓል መከበሩ ታውቋል። በላቲን ሥርዓተ አምልኮ የቀን አቆጣጠር መሠረት ከተከበረው የክርስቶስ ንጉሥ በዓል ጋር፣ በየዓመቱ በሀገረ ስብከት ደረጃ የሚዘጋጅ 36ኛው ዓለም አቀፍ የወጣቶች ቀንም ተከብሮ መዋሉ ታውቋል። ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በመስዋዕት ቅዳሴው ወቅት ባቀረቡት ስብከት፣ ወጣቶች ሕይወታቸውን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር በመጓዝ፣ ኢየሱስን በልባቸውም እንዲይዙት አሳስበው፣ ወጣቶች ሕይወታቸው በኢየሱስ የታገዘ በመሆኑ ፍርሃት ሊሰማቸው አይገባም ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ቅዱስነታቸው በስብከታቸው፣ የዛሬዎቹ ወጣቶች፣ ሁሉም ነገር እየፈራረሰ ባለበት ጊዜ ጸንተው እንዲቆሙ አሳስበው፣ መከራ በአቋራጭ መንገድ ማለፍ ሳይሆን በድፍረት እና በእርግጠኝነት እንዲቋቋሙት አሳስበዋል።  ከዮሐንስ ራእይ እና ከትንቢተ ዳንኤል መጽሐፍት ተወስዶ በተነበቡት የዕለቱ ንባባት ላይ በማስተንተን ስብከታቸውን ያቀረቡት ቅዱስነታቸው፣ ኢየሱስ ክርስቶስ በደመና እንደሚመጣ መጠቀሱን አስታውሰው፣ የኢየሱስ ክርስቶስ ሁለተኛው ምልክት፣ በቅዱስ ወንጌል የተጠቀስው እና በጲላጦስ ፊት ቆሞ “እኔ ንጉሥ ነኝ” ያለው መሆኑን አስታውሰዋል።

በእነዚህ ሁለት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ላይ በማስተንተን ስብከታቸውን ያቀረቡት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ወጣቶች ቆም ብለው እነዚህን ሁለቱ የኢየሱስ ክርስቶስ ገጽታዎች በማሰብ፣ በፖርቱጋል ዋና ከተባ ሊዝቦን በ2015 ዓ. ም. የሚከበረውን ዓለም የወጣቶች ፌስቲባል በማሰብ ብርታትን እንዲያገኙ ተመኝተዋል። በዕለቱ በቀረቡት ንባባት ኢየሱስ ክርስቶስ የሚታይበትን የመጀመሪያውን ገጽታ ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ኢየሱስ ክርቶስ በዘመናት ፍጻሜ ላይ በደመና ተገልጦ በክብር በመምጣት፣ በሕይወታችን ላይ የመጨረሻውን የፍርድ ቃል የሚሰጥ እርሱ እንደሆነ ያስገነዝበናል ብለዋል። ኢየሱስ ክርስቶስ ከደመና ውስጥ በመገለጥ “ሕይወታችሁ በአውሎ ነፋስ እንዲመታ ብቻችሁን አልተዋችሁም! ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ! ወደ ዓለም የመጣሁትም ወደ ብሩህ ሰማይ ልወስዳችሁ ነው!” ማለቱን አስታውሰዋል።

ነቢዩ ዳንኤል በትንቢቱ፣ እግዚአብሔር በደመና ሲመጣ በራእይ እንዳየው የተናገረውን ያስታወሱት ቅዱስነታቸው፣ ዛሬ ወጣቶች ሕይወታቸው የጨለመባቸው መስሎ ቢታያቸውም፣ ከጨለማ ወጥተው ወደ ብርሃን ለመድረስ ጥረታቸውን እንዳያቋርጡ እና ብርሃን በዙሪያቸው እንዳለ መዘንጋት እንደሌለባቸው አሳስበዋል።

ኢየሱስን የሕይወት መሠረት ማድረግ

ወጣቶች፣ አስደሳች ነገር ግን ደግሞ ፈታኝ ተግዳሮት ውስጥ እንደሚገኙ የተነገሩት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በዙሪያችን ያለው ነገር ሁሉ የፈረሰ መስሎ ቢታየንም በጽናት በመቆም፣ በጨለማ ውስጥ ብርሃንን ለማየት የተዘጋጀን፣ የፈራረሰውን መገንባት የምንችል እና ይህን ለማድረግ የምናስብ መሆን አለብን ብለዋል። አክለውም፣ ወጣቶች ኢየሱስ ክርስቶስን የሕይወታቸው መሠረት ሲያደርጉት እና በደስታ ሲቀበሉት የሚመሰገኑ መሆናቸውን ገልጸው፣ “ይህ ለሁላችንም መልካም ነው" ብለዋል።

ቅዱስነታቸው በዕለቱ ያቀውረቡትን ስብከት ሲያጠቃልሉ፣ ወጣቶች በዕድሜ እየገፉም ቢሄዱም ህልማቸውን እንዲቀጥሉበት አሳስበው፣ በሚኖሩበት ኅብረተሰብ መካከል ነጻ እና ትክክለኛ ሕሊና እንዲኖራቸው አደራ ብለዋል። በመሆኑም ወጣቶች እውነት ወዳዶች፣ “ሕይወቴ በዓለማዊ አስተሳሰብ ያልተማረከ እና ነጻ ነው” ማለት እንዲችሉ፣ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ሆነው ፍትህን፣ ፍቅርን እና ሰላምን ለማንገሥ የቆሙ መሆናቸውን እንዲመሰክሩ አሳስበዋል።

22 November 2021, 14:38