ፈልግ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፥ “ብጹዓን ወደ ቅድስና እና ወደ ደስታ ጎዳና ይመሩናል!

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በላቲን ሥርዓተ አምልኮ የቀን አቆጣጠር መሠረት ጥቅምት 22/2014 ዓ. ም. ተከብሮ በዋለው የመላው ቅዱሳን መታሰቢያ ዕለት ባቀረቡት ስብከት፣ ብጹዓን ወደ እግዚአብሔር መንግሥት እና ወደ ደስታ ጎዳና የሚመሩን ናቸው ብለዋል። በቫቲካን በሚገኘው ቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ከተሰበሰቡት ምዕመናን ጋር የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት ባቀረቡበት ወቅት ባሰሙት ስብከት፣ ቅድስና የደስታ ጎዳናን መጓዝ እና በሕይወታችን ውስጥ ትንቢት የተገለጠበት መሆኑን አስረድተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ዓመታዊውን የቅዱሳን መታሰቢያ ቀን ምክንያት በማድረግ ሰኞ ጥቅምት 22/2014 ዓ. ም. የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት ለተካፈሉት በርካታ ነጋዲያን ባሰሙት ስብከት፣ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት እና ወደ ደስታ የሚወስደው ቅዱሳን የሚከተሉት መንገድ፣ ትህትናን፣ ርህራሄን፣ ገርነትን፣ ፍትህን እና ሰላምን የሚያካትት ነው ብለዋል። የዚህ ሕይወት ገጽታዎችም ደስታ እና ትንቢት መሆናቸውን አስረድተዋል።

ያለ ደስታ ቅድስና የለም

ኢየሱስ ክርስቶስ የተራራ ላይ ስብከቱን “የተባረኩ ናቸው!” በማለት መጀመሩን ያስታወሱ ቅዱስነታቸው፣ ይህም ማለት ታላቅ ደስታ ማለት እንደሆነ አስረድተው፣ የእግዚአብሔር ተወዳጅ ልጆች መሆንን ማወቅ፣ እግዚአብሔር በሕይወታችን ውስጥ እንዲኖር ስንፈቅድ የምንቀበለው የመባረክ ስጦታ ነው ብለዋል። የክርስቲያን ደስታ የሚያልፍ ደስታ ወይም ከንቱ ተስፋ ሳይሆን በእግዚአብሔር የፍቅር እይታው ስር የሚገኙት ሁሉ በሕይወት መካከል የሚያጋጥሙ ፈተናዎችን ለማለፍ በእርግጠኝነት በመተማመን ፣ ድፍረት እና ጥንካሬ የሚገኝበት ነው ብለዋል። ለዚህ እውነት ቅዱሳን ታላቅ ምስክሮች ናቸው ያሉት ቅዱስነታቸው፣ በብዙ መከራዎች ውስጥ የኖሩ ቢሆኑም ነገር ግን ሁልጊዜ በእግዚአብሔር የመወደድን እና የመደገፍን ደስታ የሚመሰክሩ ናቸው ብለዋል። ደስታ የሌለበት እምነት “ጨቋኝ” የመሆን አደጋ ሊያጋጥመው እንደሚችል ጠቁመው፣ ሕይወታችንም ደስታ የሚታይበት እንደሆነ ራሳችንን መጠየቅ እንዳለብን አሳስበው፣ "ያለ ደስታ ቅድስና የለም" ብለዋል።

የሕይወታችን ትንቢታዊ ምስክርነት

የደስታ ሕይወት ሁለተኛው ገጽታ ትንቢት መሆኑን የገለጹት ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ ብፁዓን ለድሆች፣ ስደት ለደረሰባቸው እና ፍትህ ለሚሹ ሰዎች የሕይወት ምስክርነትን በተግባር መግለጻቸውን አስታውሰው፣ የብጹዓን ሕይወት በሀብት፣ በስልጣን እና በዝና ላይ በማትኮር ዓለማዊ ደስታን ለማግኘት የሚፈልግ ሕይወት የሚጻረር መሆኑን አስረድተዋል። ኢየሱስ "ሙሉ ሕይወት የሚገኘው እርሱን በመከተል ቃሉን በተግባር በማዋል ነው" ማለቱን ቅዱስነታቸው ገልጸው፣ ይህም ያለ እግዚአብሔር ምንም ማድረግ እንደማንችል በማወቅ፣ በሕይወታችን ውስጥ እውነተኛ ደስታን ለማግኘት ከፈለግን ለእግዚአብሔር ቦታ መስጠት እንዳለብን ይጠይቃል ብለዋል።

የአዲስ ሰውነት ትንቢት

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ዓመታዊውን የቅዱሳን መታሰቢያ ቀን ምክንያት በማድረግ ያቀረቡትን ስብከት ሲያጠቃልሉ፣ በሕይወታችን ውስጥ መለወጥ እና የአዲስ ሕይወት ጎዳናን መጓዝ የምንችለው ማንነታችንን ዝቅ በማድረግ፣ ሙሉ በሙሉ በእግዚአብሔር በመታመን እንደሆን አስረድተዋል። እነዚህ በሙሉ፣ ብፁዓን የሕይወት ምስክርነት እንደሰጡ ሁሉ፣ ከገናናነት ይልቅ የዋህነትን፣ ከራስ ወዳድነት ይልቅ ምሕረት ለማድረግ፣ ፍትህ እና እኩልነት ከማጉደል ይልቅ ለፍትህ እና ለሰላም ለመሥራት መጠራትን ያካትታል ብለዋል። ቅድስና ማለት፣ በእግዚአብሔር ዕርዳታ "ይህን ዓለም የሚለውጥ ትንቢት" መቀበል እና መፈጸም እንደሆነ አስረድተው፣ ኢየሱስ የተናገረውን ትንቢት ለመመስከር ምን ያህል እንደጣርን፣ ካልሆነ የሕይወት ምቾት እና ዓለማዊ መንገዶችን ብቻ የምንከተል እንደሆነ ራሳችንን መጠየቅ አለብን ብለዋል። የቅዱሳን መንገድ የሆነውን የብጽዕና ጎዳናን እንድንከተል፣ የተባረከች፣ ነፍስዋ በደስታ ጌታን ያከበረች የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ዕርዳታን በጸሎት በመለመን ስብከታቸውን ደምድመዋል።  

02 November 2021, 15:54