ፈልግ

በጳውሎስ 6ኛ አዳራሽ ውስጥ ሳምንታዊ የጠቅላላ ትምህርት ክርስቶስ አስተምህሮ በቀረበበት ወቅት በጳውሎስ 6ኛ አዳራሽ ውስጥ ሳምንታዊ የጠቅላላ ትምህርት ክርስቶስ አስተምህሮ በቀረበበት ወቅት  

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ “የካቶሊክ ዩኒቨርሲቲዎች በእምነት እና በሳይንስ መካከል ያለውን ትስስር ይገልጻሉ።”

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በጣሊያን ለሚገኝ የልበ ኢየሱስ ካቶሊካዊ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መጽሐፍ የመግቢያ ገጽ ጽሑፍ አበርክተዋል። ቅዱስነታቸው ለመጽሐፉ የመግቢያ ገጽ ባበረከቱት ጽሑፍ፣ ቤተክርስቲያኒቱ በትምህርት ዘርፍ የምታበረክታቸው ሥራዎች አስፈላጊነትን በማብራራት፣ የካቶሊክ ዩኒቨርሲቲዎች በእምነት እና በሳይንስ መካከል ያለውን ትስስር የሚያሳዩ መሆናቸውንም አስረድተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ኅዳር 15/2014 ዓ. ም በቫቲካን በሚገኘው በጳውሎስ 6ኛ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ለተገኙት በርካታ ምዕመናን ሳምንታዊውን የጠቅላላ ትምህርት ክርስቶስ አስተምህሮን ባቀረቡበት ወቅት፣ ከብጹዕ አቡነ ክላውዲዮ ጁሊዮዶሪ እና ከዩኒቨርሲቲው አስተዳዳሪ ከአቶ ፍራንኮ አኔሊ እጅ የመጽሐፉ የመጀመሪያ እትም ተበርክቶላቸዋል። ዩኒቨርሲቲው ያሳተመው መጽሐፍ አርዕስት፣ “ለልበ ኢየሱስ ካቶሊክ ዩኒቨርሲቲ የሚሆን የቤተክርስቲያን ሐዋርያዊ አስተምሮ” የሚል መሆኑ ታውቋል። አባ አጎስቲኖ ጄሜሊ፣ በሮም እ. አ. አ. ታህሳስ 7/1921 ዓ. ም. ያቋቋሙት ዩኒቨርሲቲ ያሳተመው የታሪክ መጽሐፍ በውስጡ ር. ሊ. ጳጳሳት እና የጣሊያን ካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳት ዩኒቨርሲቲውን በማስመልከት ያስተላለፉትን ሐዋርያዊ አስተምህሮች እና መልዕክቶችን ያካተተ መሆኑ ታውቋል። 

ከቤተክርስቲያን በኩል የሚደረግ ሙሉ እንክብካቤ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ለመጽሐፉት መግቢያ ባበረከቱት ጽሑፍ፣ የዩኒቨርሲቲው መቶኛ ዓመት ክብረ በዓል፣ በእያንዳንዱ አዲስ ትውልድ እየታስደሰ የመጣውን የቤተክርስቲያን ጠቃሚ የትምህርት አገልግሎትን ለማድነቅ እድል መስጠቱን ገልጸዋል። ቅዱስነታቸው አክለውም፣ ዩኒቨርሲቲው የሚያቀርበው የትምህርት ብዛት እና ጥራት የቤተክርስቲያኒቱን የማስተማር ተልእኮ አስፈላጊነትን በማሳየት፣ በተለይም ለላቀ ሳይንሳዊ እና ሙያዊ እድገት በሁሉም የእውቀት ዘርፎች እና በሰዎች ጥረት ውስጥ ያላትን ትጋት፣ የትምህርት ዓይነቶችንም በመጥቀስ “ወጣቶች ተሰጥኦአቸው ፍሬ እንዲያፈራ እና ለጋራ ጥቅም እንዲውል የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱ ያደርጋል” ብለዋል።  

ሙያዊ ስልጠናን እና ቅድስናን ማሳደግ

በሮም በሚገኝ የልበ ኢየሱስ ካቶሊካዊ ዩኒቨርሲቲ የሚሰጡ ጳጳሳዊ አስተምህሮች “ጣሊያን ከተዋሄደች በኋላ በተደረጉ የቤተክርስቲያን እና የማኅበረሰብ ውስብስብ ግንኙነቶች” ተጽዕኖ የተደረጉባቸው መሆኑን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጠቁመዋል። የልበ ኢየሱስ ካቶሊክ ዩኒቨርሲቲ፣ ለባሕል ፍለጋ፣ ለክርስቲያናዊ ተሃንጾ እና የቅድስና ጎዳናዎችን ለመገባት እውነተኛ ማዕከል ሆኖ መቆየቱን ቅዱስነታቸው አስታውሰዋል። “‘ካቶሊካ’ በመባል የሚታወቅ የዩኒቨርሲቲው የታሪክ መጽሐፉ፣ በእምነት እና በሳይንስ፣ በሥነ-መለኮት እና በጥበብ፣ እንዲሁም በመንፈሳዊነት እና በምክንያታዊ ልኬቶች መካከል ያለው ጥምረት ምን ያህል ውጤታማ እና ፍሬያማ እንደሆነ የሚያሳይ ብሩህ ምሳሌ ነው" ብለዋል።

የልዕኮአዊ ትምህርት

ቅዱስነታቸው በመቀጠል ሁሉም የካቶሊክ ዩኒቨርሲቲዎች የቤተክርስቲያኗን የወደፊት ተልእኮ መመልከት እንዳለባቸው፣ ይህም አካዳሚያዊ ተቋማትን እንደሚመለከት አሳስበዋል። የካቶሊክ ትምህርት ቤቶች እምነትን የመመስከር ልምድ በማሳደግ፣ በየደረጃው ያሉ የውይይት መድረኮች፣ የእርስ በርስ ጥናት፣ የምርምር፣ የግንኙነት እና የትስስር ባህልን በማሳደግ፣ ቤተክርስትያን ለድሆች የምታቀርበውን አማራጮች የመረዳት ተልእኮ አለባቸው ብለዋል።

የተደበቁ የጥበብ እና የእውቀት ሀብቶች

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለመጽሐፉ መቅድም ያበረከቱትን ጽሑፍ ሲያጠቃልሉ፣ ተቋሙ ትኩረቱን “የተደበቀ የጥበብና የእውቀት ውድ ሀብት ሁሉ” ወደሚገኝበት ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ልብ እንዲመልስ ጥሪያቸውን አቅርበዋል። ዩኒቨርሲቲው እንዲያድግ ከቤተክርስቲያን በኩል የሚደረገውን እንክብካቤ እና የአስተምህሮ ዕርዳታዎችን በማስታወስ፣ ወቅታዊ ፈተናዎችን በአዲስ ጉልበት እንዲጋፈጥ በማለት ለትምህርት ተቋሙ ብርታትን ተመኝተውለታል።

25 November 2021, 16:22