ፈልግ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ በእግር ኳስ ውድድር አማካይነት ማግለልን መዋጋት እንደሚያስፈልግ አሳሰቡ

በጣሊያን ውስጥ ላሲዮ ክፍለ ሀገር የሚገኝ የስፖርት ማኅበር “ዎርልድ ሮም” እና “ሁላችንም ወንድማማቾች ነን” የእግር ኳስ ቡድኖች መካከል የወንማማችነት ጨዋታን ማዘጋጀቱ ታውቋል። በሁለቱ የእግር ኳስ ቡድኖች መካከል የተካሄድው ይህ የወንድማማችነት ጨዋታ፣ ጥላቻን አስወግዶ ወዳጅነትን ለማሳደግ እና ያሉትን ልዩነቶች በማክበር በጓደኝነት ጊዜን በደስታ ለማሳለፍ ትምህርት እንዲሆን የተደረገ ውድድር እንደነበር ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በሁለቱም ቡድኖች በኩል ሰባት ግቦችን በማስቆጠር በእኩል ግብ የተጠናቀቀው የወዳጅነት ጨዋታ የታካሄደው እሑድ ኅዳር 12/2014 ዓ. ም. ሲሆን ግጥሚያውን ያስተባበረው በላሲዮ ክፍለ ሀገር የሚገኝ የፎርሜሎ ከተማ ስፖርት ማኅበር መሆኑ ታውቋል። የውድድሩ ዓላማ በስፖርት ጨዋታዎች አማካይነት መገለልን፣ ዘረኝነትን እና ድህነትን መዋጋት እንደሚገባ ለማሳሰብ እንደነበር ታውቋል። “ሁላችንም ወንድማማቾች ነን” ቡድንን በመወከል ግጥሚያውን የተካፈሉት ተጫዋቾች፣ ከቫቲካን ዘብ ጠባቂዎች ልጆች፣ በቫቲካን ውስጥ ከሚገኙ ካኅናት፣ ከቫቲካን ተቀጣሪዎች ልጆች እና ከቅዱስ ኤጂዲዮ ማኅበር የተወጣጡ ልጆች መሆናቸው ታውቋል።

“ሁላችንም ወንድማማቾች ነን” የተሰኘው የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ቡድን የመጀመሪያውን ግማሽ የጨዋታ ጊዜን በተፎካካሪው የክሮዋሺያ ቡድን ቴክኒክ እና ጨዋታ ብቃት ተበልጦ 5 ለ 1 ያጠናቀቀ ሲሆን፣ ተፎካካሪው የክሮዋሺያ ቡድን በሁለተኛው አጋማሽ የጨዋታ ጊዜ በአካል ጥንካሬ ቀንሶ በመገኘቱ ከ"ፍራቴሊ ቱቲ" ወይም “ሁላችንም ወድማማቾች ነን” ቡድን ጋር አቻ ለአቻ ውጤት ማጠናቀቁ ታውቋል።

ጫዋታው የ “አንድነት” እንጂ የ “ልዩነት” አልነበረም

በሁለቱ ተጋጣሚዎች መካከል የተካሄደው የወዳጅነት ጨዋታ፣ የ “ሁላችንም ወንድማማቾች ነን” የጨዋታ ሕጎችን የተከተለ እንደነበር የቫቲካን አትሌቲክስ ማኅበር ፕሬዚደንት የሆኑት አቶ ጃምፓውሎ ማቴዪ ገልጸዋል። ጨዋታው አንድነት እና ወዳጅነት የታየበት እንደነበር ገልጸው፣ ማን ብዙ እንዳስቆጠረ ወይም ማን በጫወታው በልጦ እንደተገኘ ለማሳየት ሳይሆን፣ በሁለቱ ተጋጣሚዎች መካከል ያለውን ወዳጅነት ለማሳየት የተደረገ ጨዋታ እንደነበር አስረድተዋል። “በጨዋታው መካከል ስህተት ተፈጽሞ ቅጣት እንኳን እንዳልነበረ አምናለሁ” ያሉት አቶ ጃምፓውሎ፣ የስፖርት ጨዋታዎችን፣ በሌሎች ላይ ጉዳትን ሳያስከትሉ በወዳጅነት እና በወንድማማችነት መንፈስ እንዲካሄዱ ለማድረግ የሚቻል መሆኑን ገልጸዋል።

የእግር ኳስን እና የስፖርት ስነ-ምግባርን የሚያጎለብት ውጤት

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ቅዳሜ ኅዳር 11/2014 ዓ. ም. ሁለቱን የእግር ኳስ ቡድኖች በቫቲካን በተቀበሏቸው ጊዜ ያስተላላፉትን መልዕክት ያስታወሱት አቶ ጃምፓውሎ፣ የ “ሁላችን ወንድማማቾች ነን” የጨዋታ ሕጎች፣ እግር ኳስ ሊኖረው የሚገባውን የደስታ ስሜት፣ የነጻ ጨዋታን እና አንድነትን ጨምሮ ሁሉም እሴቶች የያዘ እንደሆነ ገልጸዋል። አንዳንድ ጊዜ፣ በተለይም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ብዙ ባይታዩም፣ ትህትናን እና ወንድማማችነትን የተላበሱ ግጥሚያዎች ሞዴል በመሆን ለሌሎች ጥሩ ምሳሌ ሊሆኑ እንደሚችሉ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

“በ ‘ዎርልድ ሮም’ እና ‘ሁላችንም ወንድማማቾች ነን’ ቡድኖች መካከል የተካሄደው ጨዋታ የወንማማችነት ጨዋታ እንደነበር ተረድቻለሁ” ያሉት የቫቲካን አትሌቲክስ ማኅበር ፕሬዚደንት አቶ ጃምፓውሎ፣ ይህን የመሰለ የጨዋታ ባሕል፣ በእግር ኳስ ዓለም ውስጥ ለሚያድጉ ህጻናት አስፈላጊ ትምህርት እንደሆነ ገልጸው፣ በሌላ መንገድም የእግር ኳስ ጨዋታን ያለ ግፊያን እና የስድብ ቃላት ስይሰነዝሩ መጫወት የሚቻል መሆኑን ገልጸዋል። በሁለቱ ቡድኖች ውስጥ በተሰልፉት ተጫዋቾች መከከል ስደተኞች እና የአእምሮ ዝግምተኛ ልጆች መኖራቸውን ማየት ትልቅ ተሞክሮ እንደሆናቸው ገልጸው፣ በሰዎች መካከል መገለል እንዳይታይ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ስላደረጉት ጥረት ምስጋናቸውን አቅርበውላቸዋል።

የተለያየ ታሪክ ያላቸው ሃያ ሁለት ተጫዋቾች

በሜዳው ለውድድር የቀረቡ ሃያ ሁለቱ ተጫዋቾች፣ እያንዳንዳቸው የግል ታሪክ እንዳላቸው ሲነገር በዕለቱ ባካሄዱት ጨዋታም ጥሩ የእግር ኳስ ትርዒት ​​ማሳየታቸው ተመልክቷል። የእግር ኳስ ጨዋታ ብዙውን ጊዜ የሕይወት ገጠመኞችን ለማቅረብ እንደሚያገለግል የገለጹት አቶ ጃምፓውሎ፣ በተጨዋቾች መካከል ግሪክ ውስጥ ከሚገኝ የሌስቦ ስደተኞች መጠለያ አቋርጦ የመጣ ካሜሩናዊ ልጅ መኖሩ ታውቋል። በውድድሩ ላይ የ “ፍራቴሊ ቱቲ” ወይም “ሁላችን ወንድማማቾች ነን” ማለያን ለብሶ የተሰለፈው ይህ ወጣት ለቡድኑ እንግዳ ሆኖ ሳይሆን ከቡድኑ ተጫዋቾች መካከል አንዱ ሆኖ መቅረቡ ክብርን ያጎናጸፈው መሆኑ ታውቋል።

ጨዋታው ሌላ ምስክርነት የታየበት ነበር

የቴክኒክ እና ሎጂስቲክስ እርዳታን በማቅረብ ይህን የመሰለ የወንድማማችነት ግጥሚያ እንዲካሄድ እድሉን ላመቻቸው፣ የላሲዮ ክፍለ ሀገር ስፖርት ማኅበር አቶ ጃምፓውሎ ማቴዪ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

22 November 2021, 14:15