ፈልግ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ የጦርነት እና የአመጽ ሰለባዎችን በጸሎታቸው አስታወሱ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በላቲን የአምልኮ ሥርዓት የቀን አቆጣጠር መሠረት ጥቅምት 23/2014 ዓ. ም. የተከበረው የሙታን መታሰቢያ ዕለት፣ በጦርነት እና በአመጽ ሕይወታቸውን ያጡትን በጸሎት የምናስታውስበት የተለየ ቀን መሆኑን ገልጸው፣ የጦርነት እና የአመጽ ሰለባ የሆኑትን በሙሉ በጸሎታቸው አስታውሰዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ቅዱስነታቸው የመላው ሙታን መታሰቢያ ቀን በሆነው በዛሬው ዕለት በሮም ከተማ ውስጥ በሚገኝ የፈረንሳይ የጦርነት ሰለባዎች መካነ መቃብር ሥፍራ በመገኘት የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት አሳርገዋል።  ትናንት ጥቅምት 22/2014 ዓ. ም. ተከብሮ በዋለው የመላው ቅዱሳን መታሰቢያ ዕለት፣ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ከተሰበሰቡት ምዕመናን ጋር ሆነው የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት ባቀረቡበት ወቅት እንደገለጹት፣ የሙታን መታሰቢያ ቀን በእነዚህ ቀናት ውስጥ ወደ መካነ መቃብር ሥፍራ ሄደው ጸሎታቸውን ከሚያቀርቡ በዓለም ዙሪያ ከሚገኙ ምዕመናን ጋር በመንፈስ የምንተባበርበት መልካም አጋጣሚ መሆኑን ተናግረዋል። በሮም ከተማ በሚገኝ መካነ መቃብር ተገኝተው ያሳረጉት የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት በተለይም በጦርነት እና በዓመፅ ምክንያት ያረፉትን ሁሉ በጸሎት ለማስታወስ ያገዛቸው መሆኑን ገልጸዋል።

በሮም ከተማ የሚገኝ የፈረንሳይ ወታደራዊ መካነ መቃብር ወደ 1900 የሚጠጉ ሰዎች የተቀበሩበት ሥፍራ መሆኑ ታውቋል። በዚህ መካነ መቃብር ሥፍራ ከተቀበሩት መካከል አብዛኛዎቹ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ጊዜ የተሰው የሞሮኮ እና የአልጄርያ ወታደሮች መሆናቸው ታውቋል። በርካታ ቁጥር ያላቸው የእስልምና እምነት ተከታዮች የተቀበሩ ሲሆን ክርስቲያኖችም እንደሚገኙበት ታውቋል። 

የጣሊያን መንግሥት በሮም ከተማ ያስገነባው የመቃብር ሥፍራ እ. አ. አ. ከ1943 እስከ 1944 ዓ. ም. በናዚዎች ጦርነት ለተሳተፉት የፈረንሳይ ወታደሮች ክብር ለመስጠት የተገነባ መሆኑ ታውቋል። መካነ መቃብሩ ባለፉት እና በቅርብ ዓመታት ውስጥ በተካሄዱ ጦርነቶች ላይ ሕይወታቸውን ላጡት በየዓመቱ ኅዳር 2 ቀን የመታሰቢያ ሥነ ሥርዓት የሚፈጸምበት ሥፍራ መሆኑ ታውቋል። 

በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ባለፈው ዓመት ጥቅምት 23/2013 ዓ. ም. ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዕለቱን ያስታወሱት በቫቲካን ውስጥ በሚገኝ መካነ መቃብር ውስጥ ምዕመናን ባልተገኙበት የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ሥነ-ሥርዓት መሆኑ ይታወሳል።

02 November 2021, 16:02