ፈልግ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ ቅዱስ ዮሴፍ የማኅበራዊ ሕይወት ምሳሌ መሆኑን ገለጹ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ረቡዕ ኅዳር 15/2014 ዓ. ም. ሳምንታዊውን የጠቅላላ ትምሕርተ ክርስቶስ አስተምህሮአቸውን አቅርበዋል። ቅዱስነታቸው በዛሬ ዕለት ባቀረቡት የጠቅላላ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮአቸው፣ ቅዱስ ዮሴፍ ትርጉም ላለው የማኅበራዊ ሕይወት ዋና ምሳሌ መሆኑን ገልጸዋል።

ክብራትና ክቡራን የዝግጅታችን ተከታታዮች፣ ቅዱስነታቸውን በዛሬው ዕለት ያቀረቡት የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ትርጉም ሙሉ ይዘቱን እንደሚከተለው አቅርበናል።  

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“ውድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ!

ባለፈ ሳምንት በቀረበው የረቡዕ ዕለት ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ፣ የቅዱስ ዮሴፍን ሕይወት ማየት መጀመራችን ይታወሳል። በዛሬው ዕለት የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮአችንም ቅዱስ ዮሴፍ በሰው ልጅ የምሕረት ታሪክ ውስጥ ያለውን ሚና እንመለከታለን።

በሉቃ. 3፡23 ፣ 4፡22 እና በዮሐ. 1፡45 ፣ 6፡42 ላይ ኢየሱስ ክርስቶስ የዮሴፍ ልጅ እንደሆነ ተጠቅሷል። በማቴ. 13፡55 እና በማር. 6፡3 ላይ ደግሞ የአናጽው ልጅ እንደሆነ ተጠቅሷል። ሁለቱ ወንጌላውያን፣ ወንጌላዊው ቅዱስ ማቴዎስ እና ወንጌላው ቅዱስ ሉቃስ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ የሕጻንነት ሕይወት ሲተርኩ፣ በዚህ መካከል የዮሴፍንም ሚና ጠቅሰዋል። ሁለቱም ወንጌላውያን የኢየሱስን ታሪክ ለማጉላት በመፈለግ የትውልድ ሐረጉን መመልከት መርጠዋል። በተለይ ወንጌላው ማቴዎስ የአይሁድ መሠረት ካላቸው ክርስቲያኖች ጋር በማዛመድ፣ ከአብርሃም ጀምሮ እስከ ዮሴፍ ያለውን የዘር ሐረግ በመቁጠር፣ ዮሴፍ የኢየሱስ ክርስቶስ እናት የማርያም እጮኛ እንደሆነ ይናገራል። (ማቴ. 1፡16) ወንጌላው ሉቃስ በሌላ ወገን፣ እስከ አዳም ድረስ ያለውን የዘር ሐረግ ቆጥሮ ከጨረሰ በኋላ ለሕዝቡ ሲናገር ‘ኢየሱስ ክርስቶስ የዮሴፍ ልጅ ይመስላቸው ነበር’ በማለት ይጀምራል። (ሉቃ. 3፡23) ስለዚህ ሁለቱም ወንጌላዊያን ዮሴፍን የሚመለከቱት የኢየሱስ ክርስቶስ የስጋ አባት እንደሆነ ሳይሆን ነገር ግን ምንም ቢሆን የኢየሱስ ክርስቶስ አባት እንደ ሆነ ይቆጥሩታል። በዮሴፍ በኩል፣ በእግዚአብሔር እና በሰው መካከል ያለው የቃል ኪዳን እና የድነት ታሪክ በኢየሱስ ክርስቶስ መፈጸሙን ይመሰክራሉ። ለወንጌላዊው ማቴዎስ ይህ ታሪክ የሚጀምረው ከአብርሃም ሲሆን፣ ለሉቃስም የሰው ልጅ ከተገኘበት ጊዜ አንስቶ ነው።

ወንጌላዊው ማቴዎስ ዮሴፍን ገለልተኛ ቢያስመስልም በስተጀርባው ዮሴፍ በእውነት በድነት ታሪክ ውስጥ ዋና ተዋናይ መሆኑን እንድንረዳ አግዞናል። ዮሴፍም ቢሆን እንደምንመለከተው ሕይወቱን የኖረው ቀዳሚ ሥፍራን ለመያዝ ፈልጎ እንዳልሆነ እንገነዘባለን። ሕይወታችንም የተገናኘ፣ በተራ ሰዎች የሚደገፍ መሆኑን ለመረዳት ሰዎች ችላ ይላሉ። በጋዜጦች፣ በመጽሔቶች እና በተለያዩ ማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ ስማቸው የማይጠቀስ ብዙ ሰዎች አሉ። ልጆቻችን የዕለት ተዕለት ሕይወታቸውን እንዴት መኖር እንደሚገባ የሚመክሩ፣ የሚያጋጥማቸውን ፈተና እንዴት መቋቋም እንዳለባቸው ምክራቸውን የሚያካፍሉ እና ወደ ፊት እንዲመለከቱ የሚያደርጉ እና በጸሎት እንዲበረታቱ በማድረግ የሚረዱ ስንት አባቶች፣ እናቶች፣ አያቶች እና አስተማሪዎች አሉ። ለጋራ ደህንነት ብለው ዘወትር የሚጸልዩ እና የሚመልዱ፣ መስዋዕትን በመክፈል ላይ የሚገኙ ብዙ ሰዎች አሉ።’ (Apostolic Letter Patris corde, 1) ስለዚህ ሰዎች ባይገነዘቡትም ስለ ዮሴፍ ሕይወት በስፋት ባይነገርም፣ እርሱ አስተዋይ፣ አማላጅ፣ አጋዥ እና የችግር ጊዜ ደራሽ እንደነበረ ከሕይወቱ መረዳት ይቻላል። ዮሴፍ፣ ተደበቀው የሚገኙ ሰዎች በመዳን ታሪክ ውስጥ ወደር የለሽ ሚና ያላቸው መሆኑን ያስታውሰናል። ዛሬ ዓለምም እነዚህን የመሳሰሉ ሰዎች፣ ወንዶች እና ሴቶች ያስፈልጉታል።

ቅዱስ ሉቃስ በጻፈው ወንጌል ውስጥ ዮሴፍ የኢየሱስ ክርስቶስ እና የማርያም ጠባቂ ሆኖ ተገልጿል። በዚህም ምክንያት እርሱ "የቤተክርስቲያንም ጠባቂ ነው። ምክንያቱም በታሪክ ውስጥ ቤተክርስቲያን የክርስቶስ አካል ናትና። ማርያምም የቤተክርስቲያት እናት እንደሆነች የተገለጸው በዚህ ምክንያት ነው። ዮሴፍ ሕፃኑን ኢየሱስ ክርስቶስን እና እናቱን ማርያምን ከአደጋ የጠበቀ በመሆኑ የቤተክርስቲያንም ጥባቂ ሆኖ ቀጥሏል። ይህ የዮሴፍ ጥባቂነት ሚና ለኦሪት ዘፍጥረት ታሪክም ታላቅ መልስ ሆኖ እናገኛለን። እግዚአብሔር ቃየልን ‘ወንድምህ አቤል ወዴት ነው?’ ብሎት በጠየቀው ጊዜ ቃየልም “የወንድሜ ጠባቂው እኔ ነኝን?” ብሎ መለሰ። (ዘፍጥ. 4፡9) ከዮሴፍ ሕይወት ልንማር የሚገባን ነገር እንዳለ ይገባናል። እኛም የተጠራነው የወንድሞቻችን እና የእህቶቻችን ጠባቂዎች እንድንሆን፣ ዕርዳታችንን ፈልገው የሚቀርቡትን ተቀብለን በርኅራሄ እና በትህትና እንድናስተናግዳቸው፣ እግዚአብሔር በሁኔታዎች ሁሉ አደራ የሰጠን መሆናችን እንዲሰማን ሊነግረን የፈለገ ይመስላል።

በቀላሉ እንደሚጎዳ የተገለጸው የዛሬው ማኅበረሰባችን፣ በዮሴፍ ታሪክ ውስጥ የተገለጸው የሰዎች ኅብረት እና ትስስር እንደሚያስፈልገው ግልጽ ነው። በእርግጥም በቅዱስ ወንጌል ውስጥ የተገለጸው የኢየሱስ ክርስቶስ የዘር ሐረግ፣ ሥነ-መለኮታዊ ገጽታን ለማስየት ብቻ ሳይሆን የእያንዳንዳችን ሕይወት ከሌሎች ሰዎች ሕይወት ጋር የተገናኘ መሆኑን ለማስታወስ ጭምር ነው። የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስም ወደዚህ ዓለም የመጣው ይህን ዓይነት ትስስር በመምረጥ ነው

ውድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ፣ በሕይወታቸው ውስጥ ትርጉም ያለውን ትስስር ለማግኘት የሚከብዳቸው ብዙ ሰዎች እንዳሉ አስባለሁ። በብቸኝነታቸው ምክንያት የሕይወት ትግል እንደሚያጋጥማቸው፣ ብቸኝነትም እንደሚሰማቸው አስባለሁ።  ነገር ግን ሕይወታቸውን ለመቀጠል ጥንካሬ እና ድፍረት ይጎድላቸዋል። ስለዚህ እነዚህ ሰዎች እና እኛ ሁላችንም የቅዱስ ዮሴፍን አጋርነት፣ ወዳጅነት እና ድጋፍ ማግኘት እንድንችል በዚህ ጸሎት የዛሬውን ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ማጠቃለል እፈልጋለሁ።

ቅዱስ ዮሴፍ ሆይ!

ከማርያምና ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ያለህን ግንኙነት ጠብቀሃል።

እኛም በሕይወታችን ውስጥ ከሌሎች ሰዎች ጋር ያለንን ግንኙነት ጠብቀን

እንድንኖር እርዳን። ማናችንም በብቸኝነት ስሜት ውስጥ እንዳይወድቅ ጥብቀን።

እያንዳንዳችን ከራሳችን እና ከእኛ በፊት ከነበሩትም ጋር እንድንታረቅ እርዳን።

በፈጸምናቸው ስህተቶች ክፉ መንፈስ ዕድል ሳያገኝ፣

የእግዚአብሔር የምሕረት ጸጋ የበዛልን መሆኑን እንድናውቅ እርዳን።

በመከራ ውስጥ ለሚገኙት በሙሉ የቅርብ ረዳታቸው እንደሆንክ አሳያቸው።

ቅድስት ማርያምን እና ኢየሱስ ክርስቶስን በአስቸጋሪ ጊዜያት እንደረዳሃቸው ሁሉ

እኛንም በአስቸጋሪው የሕይወት ጉዟችንም ላይ ደግፈን።  አሜን።”

24 November 2021, 16:29