ፈልግ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ ከባዮ ሜዲሲን ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል ልኡካን ጋር በቫቲካን ሲገናኙ ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ ከባዮ ሜዲሲን ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል ልኡካን ጋር በቫቲካን ሲገናኙ 

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ የሕሙማን ሰብዓዊ ክብር በቅድሚያ ሊታይ ይገባል አሉ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በሮም ከተማ የሚገኝ የባዮ ሜዲሲን ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል ልኡካንን በቫቲካን ተቀብለው ንግግር አድርገውላቸዋል። ቅዱስነታቸው ለልኡካኑ ባሰሙት ንግግር ማዕከሉ በጤና እንክብካቤው ክርስቲያናዊ መርህን ተከትሎ ለሚያቀርበው አገልግሎት አድናቆታቸውን ገልጸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ቅዱስነታቸው ሰኞ ጥቅምት 8/2014 ዓ. ም. በቫቲካን ለተቀበሏቸው ካቶሊካዊ የጤና ተቋም ሠራተኞች ባሰሙት ንግግር፣ ክቡር የሆነው የሰው ልጅ ሕይወት ለገንዘብ ትርፍ ቅድሚያን የሰጡ ሰዎች ሰለባ ሊሆን አይገባም ብለው፣ የተቋሙ ሠራተኞችም ይህን መርህ በተግባር መመስከር እንዳለባቸው አሳስበዋል። እያንዳንዱ የጤና እንክብካቤ መስጫ ተቋም ፣ በተለይም ክርስቲያናዊ የጤና አገልግሎት መስጫ መሣሪያዎች ለሰው ልጅ የጤና እንክብካቤ የሚሰጥበት ሊሆን ይገባል ብለው፣ የጤና አገልግሎት መስጫ ማዕከላት ሐኪሞች እና ሕሙማን ብቻ የሚታዩበት ሳይሆን ለሰዎች መልካም አቀባበል የሚደረግበት እና ሰዎች የሚረዳዱበት ቦታ ሊሆን ይገባል ብልዋል። አክለውም የሕክምና አገልግሎት መስጫ ተቋማት የሰውን ልጅ ሰብዓዊ ክብር ለማስጠበቅ ጥረት የሚደረጉበት መሆን እንዳለባቸው ለልኡካን ቡድኑ ባሰሙት ንግግር ገልጸዋል።

በሮም ከተማ ውስጥ የሚገኝ የባዮ-ሜዲሲን ዩኒቨርሲቲ ካቶሊካዊ የጤና ተቋም የስፔን ጳጳስ በሆኑት በብጹዕ አቡነ አልቫሮ ደል ፖርቲሎ እ. አ. አ በ1993 ዓ. ም. የተመሠረተ መሆኑ ይታወሳል። ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ለልኡካኑ ባሰሙት ንግግር፣ ብጹዕ አቡነ አልቫሮ ደል ፖርቲሎ፣ በማዕከሉ ውስጥ የሚሠሩ የጤና ባለሞያዎች ለታካሚዎቹ በሚሰጡት የእንክብካቤ አገልግሎት መካከል ከሕመማቸው ይልቅ ለሰብዓዊ ክብራቸው ቅድሚያን እንዲሰጡ ማበረታታቸውን አስታውሰው፣ በእያንዳንዱ የሕክምና መስክ መሠረታዊው እና አስፈላጊው ለሰው ልጅ የሚሰጥ ጠቅላላ የሕክምና አገልግሎት መሆኑን አስረድተዋል።    

ሳይንስ እና ምርምር

በጤና አገልግሎት ዘርፍ ውስጥ የሳይንስ እና የምርምር አስፈላጊነትን ያስታወሱት ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ “የጤና እንክብካቤን የላገናዘበ ሳይንሳዊ ምርምር ዋጋ እንደማይኖረው ሁሉ በሳይንስ ያልታገዘ የጤና እንክብካቤ ከንቱ ነው” ብለዋል። ሳይንስ እና ምርምር አብረው ፣ አዕምሮን እና ልብን፣ ዕውቀትን እና ርህራሄን ከሙያዊ ብቃት ጋር በማጣመር የሕክምና ዘርፍ ሥነ-ጥበብን እንደሚያፈራ ቅዱስነታቸው አስረድተዋል። በዚህ ረገድ የባዮ-ሜዲሲን ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል ልዑካን ሰብአዊ ዕድገትን ለማምጣት ብለው ለሚያደርጉት የምርምር ጥረት ምስጋናን እና ሞገስን አቅርበውላቸዋል።

ቅዱስነታቸው ይህን ካሉ በኋላ፣ አዳዲስ በሽታዎች እየተስፋፉ በመጡበት እና ምቾት እያነሰ በመጣበት ባሁኑ ጊዜ ማዕከሉ በጤና እንክብካቤ አሰጣጥ ሂደቱ በበሽተኞች እና ዕድሜ በገፉ አቅመ ደካሞች ላይ የሚያሳየውን የገንዘብ ትርፍ ለማግኘት በሚያደርገው ሙከራ ላይ የተሰማቸውን ቅሬታ ገልጸዋል። በሌላ በኩል ካምፓሱ የዩኒቨርሲቲ ወጪዎችን ለመሸፈን የገንዘብ አቅም ለሌላቸው ሰዎች የሚያደርገውን ዕርዳታ በማስታወስ ምስጋናቸውን አቅርበዋል። በተጨማሪም ሆስፒታሉ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከላከያ ማዕከልን እና ለድንገተኛ የሕክምና አገልግሎት መስጫን በማመቻቸት ሆስፒሉ ያሳያቸውን ጥረቶችን አስታውሰዋል።  

የተቀናጀ የአውታረ መረብ አገልግሎት

እነዚህ በርካታ አገልግሎቶች ከሌሎች ጋር በመተባበር በጋራ የሚሰሩ መሆናቸውን የገለጹት ቅዱስነታቸው፣ ዓለምን ክፉኛ ያጠቃው ኮቪድ-19 ወረርሽኝ፣ የጋራ ችግሮችን በጋራ መፍታት ይቻል ዘንድ መተባበር አስፈላጊ እንደሆነ ማስተማሩን ገልጸዋል። በተለይ ካቶሊካዊ የጤና አገልግሎት መስጫ ተቋማት መተባበር እንዳለባቸው የገለጹት ቅዱስነታቸው፣ የበጎ አድራጎት ሥራ ስጦታን እንደሚጠይቅ ሁሉ፣ በጤና ባለሞያዎች መካከል የዕውቀት፣ የብቃት እና የሳይንሳዊ ምርምሮች በቀባበል ሊኖር ይገባል ብለዋል።

ሥር የሰደዱ መንስኤዎችን መፍታት

የሳይንስ ምርምር ውጤቶች እና ዘመናዊ የሕክምና መገልገያ አቅርቦት ብቻውን በቂ እንዳልሆነ የገለጹት ቅዱስነታቸው፣ በሰው ልጅ ጤና ላይ የሚደርሱ ጉዳቶችን ለጊዜው ሊያስታግሱ ይችሉ ይሆናል እንጂ ሙሉ መፈውስን ለማምጣት አይረዱም ብለዋል። ቅዱስነታቸው በምሳሌ ሲጠቅሱ ፣ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ክትባት ፣ በማደግ ላይ ያሉ አገሮችን በአስቸኳይ ለመርዳት ያለመ እንደሆነ ገልጸው፣ የረጅም ጊዜ ዕይታን መሠረት ባደረገ እና ደህንነቱ በጠበቀ መልኩ የሚከናወን እንጂ በሀብታም አገሮች ፍላጎት በመነሳሳት በፍጥነት የሚከናወን መሆን የለበትም ብለው፣ መድኃኒቶች በክብር የሚከፋፈሉ እንጂ እንደ ወረቀት የትም መዝረክረክ የለባቸውም ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመጨረሻም ለባዮ-ሜዲሲን ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል ልኡካን ያደረጉትን ንግግር ሲያጠቃልሉ፣ የጤና ባለሞያዎቹ መንፈስ ቅዱስ ለሚሰጣቸው ተነሳሽነት እና አስገራሚ ነገሮች ልባቸውን ክፍት እንዲያደርጉ አደራ ብለው፣ ለታመሙት ቅርበትን እና ርህራሄን ሳያጎድሉባቸው አገልግሎታቸውን በፍሬያማነት እንዲያከናውኑ አሳስበዋል።  

19 October 2021, 16:48