ፈልግ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ ምድራችንን ከውድመት ለማዳን ቆራጥ እርምጃን መውሰድ እንደሚገባ አሳሰቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በየወሩ በሚያቀርቡት የጸሎት ሃሳባቸው ለመስከረም ወር እንዲሆን በማለት ያዘጋጁትን አዲስ የጸሎት ሃሳብ በቪዲዮ መገናኛ በኩል ይፋ አድርገዋል። በዚህ ሃሳባቸው ኑሮን በልኩ በመኖር፣ የምድራችን የተፈጥሮ ሃብት አጠቃቀምን በማስተካከል እና ሥነ-ምሕዳራዊ ደንቦችን በማክበር ሃላፊነት የተሞላበት ኑሮን መኖር እንደሚገባ እና ምድራችንን ከውድመት ለማዳን ቆራጥ እርምጃን መውሰድ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በዓለም አቀፍ የጸሎት ጥሪ አውታረ-መረብ አማካይነት ለመላው ካቶሊካዊ ምዕመናን ባስተላለፉት መልዕክት፣ ከነሐሴ 26/2013 - መስከረም 24/2014 ዓ. ም. በሚቆየው የፍጥረት መታሰቢያ ሰሞን በአደጋ ውስጥ የምትገኝ የምትገኝ የጋራ ምድራችንን ከውድመት ለማዳን የጋራ ጥረት ማድረግ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል። ወጣቶች የሚኖሩበትን አካባቢ በመንከባከብ እና በመጠበቅ፣ ማኅበራዊ ዕድገትን ለማምጣት የሚያስችሉ እቅዶችን ተግባራዊ ለማድረግ ቆራጥ ተነሳሽነት ያላቸው መሆኑን ገልጸዋል። የጋራ ምድራችንን ለጥፋት የሚዳርጉ የኑሮ ልማዶችን በማስቀረት፣ የምድራችን የተፈጥሮ ሃብትን በሃላፊነት መጠቀም እንደሚገባ አሳስበዋል። የቅዱስነታቸው የመስከረም ወር የጸሎት ሃሳብ፣ በአውሮፓ ውስጥ ለንግድ ሥራ ውህደት አጋር ድርጅቶች ከፍተኛ አማካሪ እና ባሁኑ ጊዜ በዓለም ዙሪያ ከ3,500 ሰራተኞች በላይ ካሉት ተቋም ድጋፍ ማግኘቱ ታውቋል።

ለሥነ-ምህዳር ቀውስ የሰው ልጅ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ

የማኅበራዊ ዕድገት ቀውሶችን ለመከላከል የሚደረግ አስቸኳይ ጥረት አዲስ እንዳልሆነ የሚታወቅ ሲሆን፣ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በተፈጥሮ ሃብት አያያዝ ላይ ለውጥ እንዲደረግ የሚያሳስቡ በርካታ ዓለም አቀፍ ጥሪዎች በመቅረብ ላይ መሆናቸው ይታወቃል። ባለፈው ሰኔ ወር የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ባስተላለፈው የማስጠንቀቂያ መልዕክቱ፣ የአየር ንብረት መዛባት እና ብክለት በብዝሃ ሕይወት ላይ የሚደርሰው ጥፋት በሦስት እጅ መጨመሩን ገልጾ፣ ፈጣን እርምጃ ካልተወሰድበት፣ ምድራችን ሊቀለበስ በማይችል ከፍተኛ አደጋ ላይ እንደምትወድቅ ገልጿል። በጋራ መኖሪያ ምድራችን ላይ የደረሰው አደጋ የ3.2 ቢሊዮን ሰዎች ደህንነት ማቃወሱን የተባበሩት መንግሥት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አቶ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ አስታውቀው፣ አክለውም የሰው ልጅ ላለፉት በርካታ ዓመታት የምድራችንን ደን በመጨፍጨፍ፣ ወንዞቿን እና ውቂያኖሶችቿን በመበከል፣ የግጦች መሬቶችን ለእርሻ በማዋል፣ ማህበረሰብን መሠረት ያደረጉ ሥነ-ምህዳሮችን እያበላሸን መሆኑን አስረድተዋል።

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ “ውዳሴ ላንተ ይሁን” በሚለው ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳናቸው “የሥነ-ምህዳር ቀውስ ምልክቶችን ከሰው ልጅ አመጣጥ ጋር በማዛመድ ማስረዳት ጠቃሚ ይሆናል” ማለታቸው ይታወሳል። ቅዱስነታቸው በሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳናቸው፣ ድርጊታችን ምድራችንን ምን ያህል እንደሚጎዳ ለማየት በመጀመሪያ ደረጃ እኛ በምንመራው የአኗኗር ዘይቤ ላይ ማሰላሰል አስፈላጊ እንደሆነ፣ በተለይ ጤናችን አደጋ ላይ በወደቀበት ወቅቶች ፣ ማኅበራዊ እና አካባቢያዊ ቀውሶች ባጋጠሙን ወቅት ማሰላሰል አስፈላጊ እንደሆነ ተናግረዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ይህን ሁሉ በማስታወስ በላኩት የቪዲዮ መልዕክታቸው፣ ኑሮን በልኩ በመኖር፣ የምድራችን የተፈጥሮ ሃብት አጠቃቀምን በማስተካከል እና ሥነ-ምሕዳራዊ ደንቦችን በማክበር ሃላፊነት ያለበት ሕይወት መኖር እንደሚገባ አሳስበው፣ የአመጋገብ ሥርዓታችንን፣ የውሃ እና የኃይል አጠቃቀማችንን፣ ፕላስቲክ እና ሌሎች ቁሳዊ ዕቃዎችን  የምንጠቀምባቸው መንገዶች ብዙውን ጊዜ ለምድራችን ጎጂ እንደሆኑ አስረድተዋል።

በወጣቶች ጥረት በመታገዝ ዓለምን መለወጥ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ “ለውጥን እናምጣ” በሚለው መሪ ቃላቸው በወጣቶች ላይ ትኩረት በማድረግ፣ ለውጥን ለማምጣት በሚያሰብበት ጊዜ ወጣቶች በሥነ-ምሕዳር ጉዳዮች ላይ በድፍረት ተሳትፈው በአካባቢ እና ማኅበራዊ እድገት ላይ የሚያመጡ ለውጥ ከፍተኛ መሆኑን አስረድተዋል። የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የመስከረም ወር የቪዲዮ መልዕክት ቅንብርን በገንዘብ የደገፈው በአውሮፓ የንግድ ሥራ ውህደት አጋር ድርጅቶች ሊቀ መንበር ክቡር አቶ ኒኖ ሎ ቢያንኮ፣ እንደ ኩባንያ፣ ተልእኳቸው ለጋራ ምድራችን ዋጋ የሚሰጥ ዘላቂ እና ኢኮኖሚያዊ ዕድገትን ማበረታታት መሆኑን አስረድተዋል። 

ዓለም አቀፍ የጸሎት ጥሪ አውታረ-መረብ አስተባባሪ የሆኑት ክቡር አባ ፍሬደሪክ ፎርኖስ በበኩላቸው፣ የር. ሊ. ጳጳሳት ፍራንችስኮስ መልዕክት ሁላችንን በጋራ የሚመለከት መሆኑን ገልጸው፣ በሥነ-ምህዳር ላይ የደረሰው ቀውስ የአኗኗር ዘይቤያችንን መለወጥ በጋራ አስቸኳይ መፍትሄን ማግኘት እንደሚያስፈልግ ያሳስባል ብለዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ስለ ሥነ-ምህዳር ሲያናገሩ ፣ ሁሉም ነገር ከሕይወታችን ጋር እርስ በራሱ የተገናኘ መሆኑን መናገራቸውን ገልጸዋል። በመሆኑም ሥነ-ምህዳራዊ ዘላቂነት ያለውን የወደፊት ሕይወት ለማረጋገጥ ወጣቶችን በማሳተፍ ቆራጥ እርምጃ መውሰድ እንዲቻል እንጸልይ ብለዋል። ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ “ውዳሴ ላንተ ይሁን” ባሉት ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳናቸው፣ ወደ ቀላል ሕይወት በመመለስ ፣ ከፍጥረት ጋር እና የእኛ እርዳታ እና ድጋፍ ከሚያስፈልጋቸው ጋር ወንድማማችነትን መመሥረት እንደሚያስፈልግ መምከራቸውን፣ ዓለም አቀፍ የጸሎት ጥሪ አውታረ-መረብ አስተባባሪ ክቡር አባ ፍሬደሪክ ፎርኖስ አስታውሰዋል።   

06 September 2021, 16:05