ፈልግ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ ቤተክርስቲያን ነፃነትን እና የጋራ ውይይትን የምትፈልግ መሆኗን ገለጹ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በስሎቫኪያ መዲና ብራቲስላቫ በሚገኝ ቅዱስ ማርቲን ካቴድራል ውስጥ ከካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት፣ ካኅናት፣ ገዳማዊያን እና ገዳማዊያት ጋር ተገናኝተው መልዕክት አስተላለፈዋል። ቅዱስነታቸው በመልዕክታቸው በአገሪቱ የምትገኝ ቤተክርስቲያን አንድነትን ለማሳደግ፣ ወንጌልን ለመስበክ፣ እምነትን በተግባር ለማካሄድ እና የጋራ ውይይቶችን ለማካሄድ የሚያስችላት ነጻነት ሊኖራት ያስፈልጋል ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በስሎቫኪያ ውስጥ በማድረግ ላይ በሚገኙት የሐዋርያዊ ጉብኝታቸው ሁለተኛ ቀን፣ በብራቲስላቫ ከተማ በሚገኝ የቅዱስ ማርቲን ካቴድራል ውስጥ ከብጹዓን ጳጳሳት፣ ከካኅናት፣ ከገዳማዊያን እና ገዳማዊያት፣ የዘርዓ ክህነት ተማሪዎች እና ከትምህርተ ክርስቶስ መምህራን ጋር በመገናኘት ሰላምታቸውን አቅርበውላቸዋል። በመካከላቸው መገኘት ያስደሰታቸው መሆኑን ገልጸው፣ ለተደረገላቸው ግብዣ እና መልካም አቀባበል ምስጋናቸውን አቅርበውላቸዋል። የክርስትና ሕይወት ልምዳቸውን ለማድመጥ፣ ጥያቄዎቻቸውን ለመቀበል፣ የስሎቫኪያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ምኞት እና ተስፋን ለመጋራት መምጣታቸውንም ገልጸዋል። የመጀመሪያዎቹን ክርስቲያኖች ያስታወሱት ቅዱስነታቸው፣ ሳያቋርጡ የሚጸልዩ፣ ተግባብተው በኅብረት የሚጓዙ መሆናቸውን ስታውሰዋል።

በዓለም ውስጥ የምትኖር ቤተክርስቲያን

ከሁሉ በላይ የሚያስፈልገን፣ የቅዱስ ወንጌልን ደማቅ ብርሃን ከፍ አድርጋ ይዛ በኅብረት መጓዝ የምትችል ቤተክርስቲያን ታስፈልገናለች ብለዋል። ይህች ቤተክርስትያን እንደ ቤተመንግስት ራሷን በከፍታ ላይ በማስቀመጥ፣ በምሽጎች ታጥራ ራሷን ከጥቃት መከላከል በመቻል ከታች ያለውን ዓለም ከላይ ሆና የምትመለከት አይደለችም ብለዋል። ቤተክርስቲያን፣ በወንጌል ደስታ ሰዎችን ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ የምታቀርብ፣ በዓለማችን ውስጥ የእግዚአብሔርን መንግሥት በፍቅር እና በሰላም ለመገንባት የሚጥሩ ሰዎች አንድነት ወይም እርሾ ናት ብለዋል። ቅዱስነታቸው ቤተክርስቲያን ለምታሳየው ትህትና ምስጋናቸውን አቅርበው፣ ቤተ ክርስቲያን እኛን ሀብታም ሊያደርገን ለራሱ ያለውን በመገፈፍ ድሃ የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን በመምሰል ትሑት መሆን አለባት ብለዋል። አክለውም ቤተክርስቲያን በዓለም ውስጥ የምትኖር፣ የሰዎችን ብሶት፣ ተስፋን እና ምኞት ተረድታ በጋራ ለመካፈል ፍላጎት ያላት መሆን ይኖርባታል ብለዋል። የሰዎችን ትክክለኛ ሕይወት በመረዳት፣ መንፈሳዊ ጥማታቸው እና ምኞታቸው ምን እንደሆነ፣ ከቤተክርስቲያን ምን እንደሚፈልጉ ማወቅ ያስፈልጋል ብለዋል። ቅዱስነታቸው ሦስት መሠረታዊ ቃላት ላይ፣ እነርሱም ነጻነት፣ አዲስ ሃሳብ ማፍለቅ መቻል እና ውይይት በሚሉት ቃላት ላይ በማስተንተን የሚከተለውን ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ነጻነት፣

የሰው ልጅ ነጻ እንዲሆን በነጻ እንደተፈጠረ ሁሉ ያለ ነጻነው እውነተኛ ስብዕናን ማግኘት እንደማይቻል ቅዱስነታቸው አስረድተዋል። የስሎቫኪያ ታሪክ ትልቅ ትምህርት ያስተምረናል ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ምን ጊዜም ቢሆን የሰው ልጅ ነጻነት የተጠቃ፣ የተጣሰ ወይም የተጨቆነ እንደሆነ፣ ሰብአዊነት ቀውስ ውስጥ በመግባት የአመፅ እና የመብቶች ማጣት አደጋ ውስጥ ይገባል ብለዋል። ነጻነት ወዲያ የሚገኝ ሳይሆን በሂደት የሚገኝ፣ ካገኙት በኋላም ለአንዴ እና ለሁሌ የሚያገለግል ነው ብለዋል። ካልተንከባከቡት ሊደበዝዝ የሚችል፣ ሁል ጊዜ እድሳትን የሚፈልግ መሆኑን አስረድተዋል። በዚህም  መሠረት ነጻ መሆን ብቻውን የማይበቃ መሆኑን ገልጸዋል። በመሆኑም በቤተክርስቲያን ውስጥ ሁሉም ነገር በቀላሉ እንዲገለፅ ከመፈልግ ይልቅ ክርስቲያኖች የሚያሰላስሉ፣  ሕሊናቸውን የሚጠይቁ እና ራሳቸውን ለተግዳሮት የሚፈቅዱ መሆን ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

አዲስ ሃሳብ ማፍለቅ መቻል

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቅዱሳን ሲሬል እና መቶዲዮስ የወንጌል አገልግሎት የተገኘውን ታላቅ ሃይማኖታዊ ቅርስን በማስታወስ እንደተናገሩት፣ ወንጌላዊነት ያለፈውን ብቻ መድገም እንዳልሆነ፣ የወንጌል ደስታ ሁል ጊዜ ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ መሆኑን፣ ነገር ግን የምሥራቹ ቃል የሚጓዝባቸው መንገዶች በጊዜ እና በታሪክ ውስጥ ሊለያዩ እንደሚችሉ አስተምረውናል ብለዋል። ቅዱስ ስሬል እና ቅዱስ ሜቶዲዮስ በጋራ ሆነው መጽሐፍ ቅዱስን በሌሎች ቋንቋዎች መተርጎም እንዲቻል፣ የአምልኮ ሥርዓቶችን እና የቤተክርስቲያን አስተምህሮችን ለማዘጋጀት አዳዲስ ፊደላትን በመፍጠር እምነትን ከባሕል ጋር ለማዋሃድ ጥረት ማድረጋቸውን አስታውሰዋል። ወንጌልን እና ክርስቲያናው መልዕክቶችን ለመጭው ትውልድ ለማስተላለፍ የሚያመቹ አዳድስ ቋንቋዎች መጠቀማቸውን፣ በዘመኑ ይኖሩ ከነበሩ ሰዎች ታሪክ ጋር በቀራረብ እንዲቻል ቋንቋዎቻቸውን እና ባሕሎቻቸውን እንደተማሩ አስታውሰው፣ በአውሮፓ ውስጥ እምነትን ለማወጅ አዳዲስ ዘዴዎች እና መንገዶች እንደሚያስፈልጉ ቅዱስነታቸው አሳስበዋል።

የጋራ ውይይት

የውስጥ ነጻነት እና ሃላፊነት እንዲኖር የምታስተምር ቤተክርስቲያን፣ ታሪክን እና ባሕልን መሠረት ያደረጉ የወንጌል አገልግሎቶችን የምታቀርብ ቤተክርስቲያን፣ ከዓለም ጋር፣ ኢየሱስ ክርስቶስ የጋራ ፈጣሪያችን እንደሆነ ከሚቀበሉት ጋር፣ ቤተክርስቲያንን ከሚታገሉት እና ከማያምኑትም ጋር ለመወያየት የተዘጋጀች መሆኗን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ገልጸዋል። አንድነትን እና ወዳጅነትን ጠብቃ ለማቆየት ቤተክርስቲያን የተለያዩ ባሕሎች እንዳሏት የገለጹት ቅዱስነታቸው፣ ሕብረት፣ አንድነት እና የጋራ ውይይት የቀድሞ ቁስሎችን ለመጠገን እና የእግዚአብሔርን የምሕረት ጸጋን ለማግኘት የሚረዱ መንገዶች መሆናቸውን አስረድተዋል። ሐዋ. ጳውሎስ ወደ ሮም ሰዎች በጻፈው መልዕክቱ በምዕ. 12:21 ላይ “ክፉውን ነገር በመልካም አሸንፍ እንጂ በክፉ ነገር አትሸነፍ” ማለቱንም አስታውሰው፣ ወንጌል በሕይወት እና በታሪክ ውስጥ የሚያድገው ትህትና እና ትዕግስት በተሞላበት ፍቅር ሲታገዝ መሆኑን አስረድተዋል። ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ለስሎቫኪያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ምዕመናን ያስተላለፉትን መልዕክት ሲደመድሙ፣ ጉዞአቸውን በወንጌል ነፃነት እንዲያጸኑት፣ ምንጩን የጋራ ውይይት እና አዲስ የእምነት ማስፋፊያ መንገድ ባደረገ፣ ወንድሞች እና እህቶች ባደረገን፣ የስምምነት እና የሰላም ገንቢዎች እንድንሆን በጠራን በእግዚአብሔር ምህረት እንዲያደርጉ በማለት የማበረታቻ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።        

14 September 2021, 16:17