ፈልግ

የቅዱስ መስቀል የቅዱስ መስቀል  

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ “የእግዚአብሔር ምሕረት ሁሉንም የሰው ልጅ የሕይወት ገጽታን ያካትታል”

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ለኢየሱስ ሕማማት ዓለም አቀፍ ገዳማዊያን ማኅበር የበላይ አለቃ ለሆኑት ለክቡር አባ ኢያቄም ሬጎ በላኩት መልዕክት፣ ዓለም አቀፍ ሥነ-መለኮታዊ ጉባኤያቸው፣ ከቅዱስ መስቀሉ በሚገኝ ጥበብ በመታገዝ በወቅታዊ ተግዳሮቶች ላይ አዲስ ግንዛቤን ለማስያዝ አስተዋጽኦን እንደሚያደርግ ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ቅዱስነታቸው ለማኅበሩ የበላይ አለቃ መልዕክታቸውን የላኩት፣ “የመስቀሉ ጥበብ በብዙሃኑ ዓለም ውስጥ” በሚል ርዕሥ፣ ገዳማዊያኑ ዓለም አቀፍ ጉባኤያቸውን በማድረግ ላይ ባሉበት ወቅት መሆኑ ታውቋል። ጉባኤውን ያዘጋጀው፣ ሮም በሚገኝ የላቴራን ጳጳሳዊ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ “ግሎሪያ ክሩቺስ” በመባል የሚታወቅ፣ ከኢየሱስ ሕማማት ገዳማዊያን ማኅበር እንቅስቃሴዎች መካከል አንዱ ሲሆን፣ ጉባኤው የተዘጋጀው ማኅበሩ የተመሰረተበት 300ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ መሆኑ ታውቋል።

የፋሲካን ምስጢር ማወጅ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለማኅበሩ አባላት በላኩት መልዕክታቸው፣ ጉባኤው የሚካሄደው በማኅበሩ መሥራች እና የቅዱስ መስቀል ወዳጅ ከሆነው ከቅዱስ ጳውሎስ ምኞት ጋር እንደሚመሳሰል ገልጸዋል። ቅዱስነታቸው በማከልም ፣ የክርስትና እምነት ማዕከል የሆነውን የፋሲካ ምስጢር ለማረጋገጥ መሆኑን ገልጸው፣ የኢየሱስ ሕማማት ገዳማዊያን ማኅበር፣ ለመለኮታዊ ቸርነት ምላሽ ለመስጠት በሚያደርገው የወንጌል አገልግሎቱ የሚጠበቅበትን የዓለም ተስፋ የሚመሰክት መሆኑን አስረድተዋል። በመስቀል ላይ የተሰቀለውን ኢየሱስን በማስታወስ፣ እያንዳንዱ የሰዎች ሕይወት ገጽታ በእግዚአብሔር ምሕረት ውስጥ መካተቱን እንመለከታለን ብለዋል። አክለውም የእግዚአብሔር ፍቅር ለሰው ልጆች በሙሉ ነው ብለው፣ ከእግዚአብሔር ጋር ግንኙነት ያላቸውን ሁሉን የሰው ልጅ የሕይወት መንገድን የሚመለከት መሆኑን አስረድተዋል።   

የቃሉ ዘሮች

መስቀል፣ ትህትና በተመላበት ልብ አንድ የመሆን አስፈላጊነትን የሚያመለክተን መሆኑን ቅዱስነታቸው አስረድተው፣ ሥነ-መለኮት ደግሞ የሰዎችን ደካማ የሆኑ ተጨባጭ የሕይወት አካሄዶችን ገልጾ ለማሳየት፣ ለአደጋ መጋለጥን በማስወገድ፣ በልበ ሙሉነት፣ አንዳንድ ጊዜም እርስ በእርሱ በሚጋጩ ባህሎች መካከል የእግዚአብሔርን ቃል ለመዝራት የሚያገለግል ነው ብለዋል። “ቅዱስ መስቀል ለመላው ዓለም፣ በዘመናት ሁሉ የመዳን ምንጭ ነው” ብለው፣ በተለይም የሰው ልጅ መንታ መንገድ ላይ በሚሆንበት ጊዜ መስቀል የመዳን ተስፋ መሆኑን አስረድተዋል።

ወቅታዊ ፈተናዎችን መጋፈጥ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ መልዕክታቸውን ባጠቃለሉበት ጊዜ እንደተናገሩት፣ የኢየሱስ ሕማማት ገዳማዊያን ማኅበር አባላት በማካሄድ ላይ የሚገኙት ዓለም አቀፍ ሥነ-መለኮታዊ ጉባኤ፣ ለእግዚአብሔር ዕቅድ ታማኝ መሆን፣ ለሰው ልጅ ትኩረትን በመስጠት፣ ከመስቀሉ በሚገኝ የጥበብ ብርሃን የዘመኑን ተግዳሮቶች ለመገንዘብ የሚያስችል አስተዋፅኦን እንደሚያበረክት ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል። 

21 September 2021, 16:36