ፈልግ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ በስሎቫኪያ ሕዝብ መካከል የመረዳዳት ባሕል እንዲያድግ አሳሰቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በስሎቫኪያ ዋና ከተማ ብራቲስላቫ ውስጥ ለመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት፣ ለውጭ አገር ዲፕሎማቶች፣ ከሕዝባዊ ማኅበራት ተወካዮች እና ለሐይማኖት መሪዎች ባስተላለፉት መልዕክት፣ በስሎቫኪያ ሕዝብ መካከል የወንድማማችነት፣ የእንግዳ መቀበል እና የመረዳዳት ባሕልን ማሳደግ እንዲችሉ ብርታትን ተመኝተውላቸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ቅዱስነታቸው ለመላው የስሎቫኪያ ሕዝብ ባቀረቡት የአደራ መልዕክት፣ በጀመሩት የሰላም ጎዳና ወንድማማችነት እና የእንግዳ መቀበል ባሕል እንዲያድግ፣ ያላቸውን ከሌሎች ጋር በመጋራት በማኅበራዊ ሕይወት ውስጥ የመረዳዳት ባሕል እንዲያድግ አደራ ብለዋል። ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ይህን መልዕክት ያስተላለፉት በብራቲስላቫ በሚገኝ ፕሬዚደንታዊ ቤተመንግሥት ለተሰበሰቡት ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ ለውጭ አገር ዲፕሎማቶች፣ ለሕዝባዊ ማኅበራት ተወካዮች እና ለሐይማኖት መሪዎች መሆኑ ታውቋል።

ወንድማማችነት

ከ28 ዓመት በፊት ቼክስሎቫኪያ ተብላ የምትጠራ የመካከለኛው አውሪፓ አገር በሰላማዊ መንገድ ለሁለት መከፈሏን ቅዱስነታቸው አስታውሰው፣ ስሎቫኪያ በመካከለኛው አውሮፓ ውስጥ የሰላም ምልክት መሆኗን ገልጸዋል። በስሎቫኪያ ሰንደቅ ዓላማ ላይ የተቀመጠው ሰማያዊ ቀለም በስሎቫኪያ ሕዝብ መካከል ያለውን ወንዳማማችነት እንደሚያሳይ የገለጹት ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ ይህ ሰላም ከጊዜ ወደ ጊዜ አስፈላጊነቱ እየጨመረ የሄደውን የመግባባት እና የሰላም ሂደት ለማፋጠን ይረዳል ብለዋል። ቅዱስነታቸው አክለውም የአውሮፓ አገሮች ድንበር ሳያግዳቸው ወደ አንድነት ታሪካቸው እንደሚመለሱ ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል። ሁለቱ ቅዱሳን፣ ቅዱስ ሲሪል እና ቅዱስ ሜቶዲዮስ የስሎቫኪያ ሐዋርያት፣ እንዲሁም የመላው አውሮፓ ባልደረባዎች፣ ለላቲን፣ ለግሪክ እና ለስሎቫኪያ ሕዝቦች የጋራ የወንድማማችነት ምሳሌዎች መሆናቸውን አስረድተዋል።

ዳቦን የመቁረስ ምሳሌ

በስሎቫኪያ ባሕል እንግዳን የሚቀበሉት ዳቦ እና ጨው በመስጠት እንደሆነ ያስታወሱት ቅዱስነታቸው፣ ይህን የወንድማማችነት እና የእንግዳ መቀብል ባሕልን ለማሳደግ ብርታትን ተመኝተዋል። እግዚአብሔር በሰዎች መካከል ራሱን ለመግለጽ ዳቦን መምረጡን ያሳታወሱት ቅዱስነታቸው፣ ቅዱሳት መጻሐፍትም ቢሆኑ እንጀራችን እንድናከማች ሳይሆን እንድንካፈል ያዙናል ብለዋል። የቅዱስ ወንጌል የሕይወት እንጀራን ሁል ጊዜ ከሌሎች ጋር መካፈል እንደሚያስፈልግ ሁሉ፣ እውነተኛ ሀብት ማለት፣ ያሉንን ነገሮች አባዝቶ ማከማቸት ብቻ ሳይሆን፣ በአካባቢያችን ካሉት ሰዎች ጋር በፍትሃዊነት መካፈል ያስፈልጋል ብለዋል። በሕዝቦች መካከል መድልዎ ሊታይ አይገባም ያሉት ቅዱስነታቸው፣ በክርስትና ሕይወት ውስጥ አንዱ ሌላውን እንደ ሸክም መመልከት ሳይሆን እንደ ወንድም እና እህት መተጋገዝ እና ከአደጋ መከላከል እንደሚያስፈልግ አሳስበው፣ ዳቦን ከሌላው ጋር በእኩል መካፈል ማለት ሕግ እና ፍትህ እንዲረጋግገጥ ማድረግ እና ሙስናን መዋጋት እንደሚያስፈልግ ያሳስባል ብለዋል።

ባሕልን ጠብቆ ማቆየት

ጨው ምግብ ሳይበላሽ እንዲቆይ ያግዛል ያሉት ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ የስሎቫኪያ ባሕልም በፍጆታ ፍላጎቶች መጨመር እና በቅኝ ግዛት ርዕዮተ ዓለም ሳይበረዝ እንዲቆይ አሳስበዋል። በኮሚኒስት ሥርዓት ቼኮስሎቫኪያ በአንድ አስተሳሰብ ብቻ የምትመራ እንደነበር ያስታወሱት ቅዱስነታቸው፣ ዛሬ በዘመናችንም አዲስ የአንድ አስተሳሰብ ሥርዓት ትርፍን በማሳደግ  ላይ ብቻ የተመሠረተ ግለኝነትን ማስተዋወቁን አስረድተው፣ ይህ በሚሆንበት ወቅት እምነት፣ በትህትና የእግዚአብሔርን መንግሥት ዘር በመዝራት ፣ በተለይም በበጎ አድራጎት ምስክርነትን ይገልጻል ብለዋል። አክለውም ሁለቱ ቅዱሳን፣ ቅዱስ ሲሪል እና ቅዱስ ሜቶዲዮስ የክርስቲያን ማኅበረተሰብ ራዕይ መነሻ ናቸው ብለው፣ ቅዱሳኑ በአስተምሮአቸው፣ “መልካም ባሕልን ጠብቆ ማቆየት ማለት ያለፈውን መድገም ማለት ሳይሆን ፣ የመላክም ባሕል መሠረት ሳይጠፋ ለመታደስ ዝግጁ መሆን ነው” ማለታቸውንም አስታውሰዋል።

የወቅቱን አስከፊ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ከዚህ ቀውስ ለመውጣት ስለራስ ብቻ ከማሰብ ይልቅ ሁላችንም የሌሎች ድጋፍ የሚያስፈልገን አቅመ ደካሞች መሆናችንን መገንዘብ እንደሚያስፈልግ አሳስበው፣ ግለሰብ ይሁን አገር ማንም ተነጥሎ ከዚህ ወረርሽኝ ራሱን ብቻ ማዳን አይችልም ብለዋል።

14 September 2021, 16:26