ፈልግ

በሊዝቦን እ. አ. አ በ2023 ዓ. ም ለሚከበረው ዓለም አቀፍ የወጣቶች ፌስቲቫል ዝግጅት በሊዝቦን እ. አ. አ በ2023 ዓ. ም ለሚከበረው ዓለም አቀፍ የወጣቶች ፌስቲቫል ዝግጅት  

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ “ወጣቶች ተነስታችሁ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ መስክሩ!”

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ዘንድሮ ኅዳር 12/2014 ዓ. ም በካቶሊካዊ ሀገረ ስብከቶች ዘንድ ለ36ኛ ጊዜ ለሚከበረው ዓለም አቀፍ የወጣቶች ቀን መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል። በዚህ መልዕክታቸው ወጣት ክርስቲያኖች የቅዱስ ጳውሎስን ፈለግ በመከተል ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ በድፍረት እንዲመሰክሩ አሳስበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን በፖርቱጋል ዋና ከተማ ሊዝቦን እ. አ. አ በ2023 ዓ. ም ለሚከበረው ዓለም አቀፍ የወጣቶች ፌስቲቫል ዝግጅት ላይ መሆኗ ታውቋል። ይህ በእንዲህ እንዳለ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሰኞ መስከረም 17/2014 ዓ. ም ይፋ ያደረጉት መልዕክት በመላው ዓለም የሚገኙ ካቶሊካዊ ሀገረ ስብከቶች ዘንድ ለ36ኛ ጊዜ የሚያከብሩትን ዓለም አቀፍ የወጣቶች ቀን የሚመለከት መሆኑ ታውቋል። የመልዕክታቸው ዋና ርዕሥ በሐዋ. 26:16 ላይ “አሁን ግን ተነስና በእግርህ ቁም፤ እኔ የተገለጥኩልህ፣ አሁን እኔን ባየህበትና ወደፊትም እኔ ለአንተ በምገለጥበት ነገር አገልጋይና ምስክር እንድትሆነኝ ልሾምህ ፈልጌ ነው።”         ከሚለው ጥቅስ የተወሰደ መሆኑ ታውቋል። ቅዱስነታቸው ወጣቶች በዓለም ውስጥ ሊጫወቱ የሚችሏቸው አስፈላጊ ሚናዎች መኖራቸውን ገልጸው፣ በተለይም በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት እጅግ በርካታ መሰናክሎች እና ችግሮች ያጋጠሟቸው መሆኑን ገልጸዋል።

የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ባስከተለው ቀውስ ምክንያት ብዙ ወጣቶች በቤተሰባዊ ችግሮች፣ በሥራ አጥነት፣ በብቸኝነት እና ሱስ የሚያስይዝ ባህሪይ መጎዳታቸውን አስታውሰዋል። በሌላ ወገን የወረርሽኙ ተሞክሮ የወጣቶችን የአለኝታነት እና የበጎነት ዝንባሌያቸውን ግልጽ አግርጓል ብለዋል። በወጣት ማኅበረሰብ ውስጥ ጉዳት ሲደርስ ሁሉም የማኅበረሰብ ክፍል እንደሚጎዳ ያስረዱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ እንደዚሁም የወጣት ማኅበረሰብ ከወደቀበት ሲነሳ መላው ዓለም በእግሩ መቆም የሚችል መሆኑን አስረድተዋል። በመሆኑም ወጣት ክርስቲያኖች በጋለ ስሜት እና ፍላጎት ተነሳስተው ዓለም ጉዞዋን እንደገና እንድትጀምር እገዛቸውን እንዲያደርጉ አሳስበዋል።

በብርሃን ብዛት ዓይኑን ታውሯል

ከሐዋ. 26:16 በተወሰደው ጥቅስ ላይ በማስተንተን መልዕክታቸውን ለወጣቶች ያስተላለፉት ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ በዚህ ጥቅስ አማካይነት ሐዋርያው ጳውሎስ በሕይወት ለመለወጥ ምክንያት የሆኑ ታሪኮችን መናገሩን አስታውሰዋል። ጳውሎስ በሕይወቱ ውስጥ ይህን ያህል ትልቅ ለውጥ ከማየቱ ከሃያ አምስት ዓመታት በፊት ክርስቲያኖችን ያሰቃይ እንደነበር፣ በዓይኑ ኃይለኛ የብርሃን ጮራ እንደተንጸባረቀበት እና  ከተቀመጠበት ፈረስ በወደቀ ጊዜ የኢየሱስን ድምጽ መስማቱን ቅዱስነታቸው አስታውሰዋል። ከዚያ በፊትም እንደሚያውቀው ለመግለጽ ኢየሱስ ጳውሎስን በስሙ መጥራቱንም ቅዱስነታቸው አስረደተዋል። የጳውሎስን ሕይወት ሊቀየር የቻለው ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር በተፈጠረ የግል ግንኙነት መሆኑን ገልጸው፣ ቅድመ ሁኔታ የሌለው የኢየሱስ ክርስቶስ ፍቅር የጳውሎስን ሕይወት የሚቀይር የብርሃን ጸጋ መሆኑን ቅዱስነታቸው አስረድተዋል።

ኢየሱስ እና ቤተክርስቲያን አንድ ናቸው

ቅዱስ ጳውሎስ ለኢየሱስ መልስ ሲሰጥ “አንተ ማን ነህ?” ብሎ መጠየቁን ያስታወሱት ቅዱስነታቸው፣ ይህን ጥያቄ እኛም ጊዜን ሳናባክን ለኢየሱስ ማቅረብ አለብን ብለዋል። ይህ ጥያቄ በጸሎት አማካይነት ከኢየሱስ ክርቶስ ጋር የምናደርገውን ውይይት እና ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ያለንን ግንኙነት ሙሉ በሙሉ ይገልጻል ብለዋል። ኢየሱስም ለቅዱስ ጳውሎስ ሲመልስ፣ “እኔ አንተ የምታሳድደኝ ኢየሱስ ነኝ” ባለው ጊዜ፣ ጳውሎስ ቤተክርስቲያንን ብቻ ሳይሆን ኢየሱስንም ያሳድደው እንደነበር እና በዚህም ኢየሱስ እና ቤተክርስቲያ አንድ መሆናቸው እንዲገነዘብ ኢየሱስ ያገዘው መሆኑን ቅዱስነታቸው አስረድተዋል። ቤተክርስቲያንን የማያውቅ ኢየሱስን ሊያውቅ እንደማይችል የገለጹት ቅዱስነታቸው፣ ኢየሱስን የሚያውቅ ማንም በማኅበረሰቡ ውስጥ ከሚገኙ ወንድሞች እና እህቶች ነጥሎ ብቻውን ሊያውቀው አይችልም ብለዋል። አክለውም የቤተክርስቲያንን የእምነት ልኬት እስካልተገነዘብን ድረስ ራሳችንን ሙሉ ክርስቲያኖች ነን ማለት አንችልም ብለዋል።

እውነተኛው መልካችን የሚገለጥበት ነው

ኢየሱስ ጳውሎስን ሲመርጠው ማንም ሰው ከእግዚአብሔር እይታ ሊሰወር እንደማይችል ማሳየቱን ያስረዱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በዚህም በእያንዳንዱ ሰው ልብ ውስጥ የእግዚአብሔር የፍቅር እሳት የሚነድ መሆኑን ይገነዘቡታል ብለዋል። ጳውሎስ ኢየሱስን ሲያገኘው ዓይኑ ለጊዜው እንደታወረ እና የሚጓዝበት መንገድም የተሳሳተ መሆኑን ገልጦለት ለትክክለኛ ቁመና ራሱን ዝቅ ማድረጉን አስረድተዋል። ከዚያ በኋላ ሳውል ስሙን ቀይሮ ጳውሎስ ተብሎ እንደተጠራ እና ትርጉሙም ዝቅተኛ ማለት መሆኑን ገልጸው፣ ይህም ጳውሎስ በሕይወቱ ያመጣውን ትልቅ ለውጥ የሚያመለክት መሆኑን አስረድተዋል። ቅዱስነታቸው ከዚህም ጋር በማያያዝ ባሁኑ ጊዜ በርካታ ወጣቶች በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ ረጅም ጊዜን በማባከን፣ ትክክለኛ መልካቸውን የማይገልጹ ፎቶግራፎቻቸውን ሲለዋወጡ ይስተዋላሉ ብለዋል። ኢየሱስ ስለሚወደን በብርሃኑ የእኛን ትክክለኛ ማንነት በመግለጥ ወደ ብርሃን እንደሚያወጣን ተናግረው፣ ጳውሎስም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ከተገናኘ በኋላ ወደ ደማስቆ በመሄድ እዚያም ጊዜውን በጸሎት እና በዝምታ በማሳለፍ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ያለውን አዲስ ግንኙነት ማጠናከሩን አስረድተዋል።      

አሳዳጅ የነበረው ለታላቅ ምስክርነት በቃ

ርዕሠ ሊቃነ ፍራንችስኮስ ለወጣት ካቶሊካውያን በላኩት መልዕክት፣ ሐዋርያው ጳውሎስ፣ የወጣትነት ስሜቱን እና ጥንካሬውን “ለወንጌል ምስክርነት” ያዋለው መሆኑን ገልጸው፣ ኢየሱስ እምነቱን በጳውሎስ ላይ ካደረገበት ዕለት ጀምሮ የአገራት ሐዋርያ ሊሆን መብቃቱን አስታውሰዋል። ቀጥለውም ወጣቶች በሚገኙበት ሁሉ በመነሳሳት ፣ የሰዎችን የተሰበረ ልብ ለመፈወስ፣ ስለ ኢየሱስ እና ስለ ኃይሉ በመመስከር ተልዕኳቸውን እንዲቀበሉ ጥሪ አቅርበዋል።

28 September 2021, 17:14