ፈልግ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ በሮም ከተማ በሚገኝ ታላቁ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ባዚሊካ ውስጥ ጸሎት ሲያቅረቡ  ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ በሮም ከተማ በሚገኝ ታላቁ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ባዚሊካ ውስጥ ጸሎት ሲያቅረቡ  

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ የቅድስት ድንግል ማርያምን ጥበቃ እና ድጋፍ ተማጸኑ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ከመስከረም 2 - 5/2014 ዓ. ም. ድረስ ወደ ሁለቱ የምሥራቅ አውሮፓ አገራት የሚያደርጉትን 34ኛ ዓለም አቀፍ ጉዞአቸውን ከመጀመራቸው አስቀድመው ፣ በሮም ከተማ ውስጥ ወደሚገኝ ታላቁ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ባዚሊካ ደርሰው ጸሎታቸውን አቅርበዋል። ቅዱስነታቸው በጸሎታቸው የእመቤታችንን ጥበቃ እና እርዳታ መለመናቸውን የቅድስት መንበር ጋዜጣዊ መግለጫ ክፍል አስታውቋል። መንፈሳዊ ጉብኝት የሚያደርጉባቸው አገራት ሃንጋሪ እና ስሎቫኪያ መሆናቸውን ከዚህ በፊት መግለጻቸው ይታወሳል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ከጣሊያን ውጭ የሚያደርጉትን ዓለም አቀፍ ሐዋርያዊ ጉብኝት ከመጀመራቸው አስቀድመው ሮም ከተማ ውስጥ ወደሚገኝ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ታላቁ ባዚሊካ በመሄድ ጸሎት የሚያደርጉ መሆኑ ይታወቃል። የቅድስት መንበር ጋዜጣዊ መግለጫ ክፍል እንዳስታወቀው፣ ቅዱስነታቸው ዓርብ ጳጉሜ 5/2013 ዓ. ም. ከማታው 12 ሰዓት ላይ ወደ ባዚሊካው ደርሰው ጸሎት ማድረጋቸውን አስታውቆ፣ በመንበረ ታቦቱ ሥር የአበባ ጉንጉን ማስቀመጣቸውንም ገልጿል። ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ባዚሊካ ውስጥ ካቀረቡት ጸሎት በኋላ በቫቲካን ውስጥ ወደሚገኝ መኖሪያቸው መመለሳቸውን የቅድስት መንበር ጋዜጣዊ ክፍል አስታውቋል።    

በባዚሊካው ውስጥ የሚገኝ ጥንታዊው የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቅዱስ ምስል፣ የሮም ከተማ ሕዝብ በስቃይ፣ በበሽታ በወደቀበት ወቅት ወደ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዘንድ የለመነበት እና የርሷን እርዳታ ያገኘበት እንደሆነ ይታመናል። ቅዱስ ምስሉ  በባዚሊካው ውስጥ በክብር እንዲቀመጥ በማለት ወደ 590 ዓ. ም. አካባቢ የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ግሬጎሪ ታላቁ  ማዘዛቸው ይታወሳል

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ እሑድ ጠዋት በሃንጋሪ ዋና ከተማ ቡዳፔስት የሚቀርበውን 52ኛ ዓለም አቀፍ የቅዱስ ቁርባን ጉባኤ መዝጊያ መስዋዕተ ቅዳሴን የሚመሩ መሆናቸው ታውቋል። በቡዳፔስት ከተማ ከሚያቀርቡት የመዝጊያ መስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ቀጥለው ወደ ስሎቫኪያ ዋና ከተማ ብራቲስላቪያ በመድርስ በአገሪቱ ወደሚገኝ የሐዘንተኛይቱ ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ መቅደስ ንግደት የሚያደርጉ መሆኑ ታውቋል። ከአገሪቱ ምዕመናን ጋር ሆነው የሚያሳልፏቸው ቀናት የውዳሴ እና የጸሎት ቀናት እንደሚሆንም ታውቋል።

በስሎቫኪያ በሚያደርጉት ንግደትም፣ የአገሪቱ ባልደረባ የሆነች ሐዘንተኛይቱ ማርያም ዓመታዊ በዓል ላይ ተገኝተው የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት እንደሚያቀርቡ የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን አስታውቀዋል። ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን፣ ቅዱስነታቸው በስሎቫኪያ የሚያደርጉትን መንፈሳዊ ጉብኝት ያራዘሙበት ምክንያት፣ ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የሚሰጧትን ክብር እና ውዳሴ በማሳደግ፣ በቅርቡ ባደረጉት የቀዶ ጥገና ሕክምና ዕርዳት ወቅት ቅድስት ድንግል ማርያም ላደረገችላቸው ዕርዳታ ምስጋናቸውን ለማቅረብ መሆኑን አስረድተዋል።

የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን በመግለጫቸው፣ ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በስሎቫኪያ የሚያደርጉት ንግደት ወይም መንፈሳዊ ጉዞ ዓላማ፣ ለመከራ እና ለስቃይ የተጋለጡትን፣ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ያስከተለውን ቀውስ ጨምሮ በሌሎች አካላዊ ሥቃይ ውስጥ የሚገኙ ሰዎችን ወደ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዘንድ በአደራ ለማቅረብ መሆኑን አስረድተዋል።  

11 September 2021, 14:08