ፈልግ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ ፍቅር ብቻውን የሰውን ልብ ያረካል ማለታቸው ተገለጸ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ የአውሮጳ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ምሥረታ 50ኛ ዓመት የወርቅ ኢዮቤልዩ በዓል ምክንያት በማድረግ ሐሙስ መስከረም 13/2014 ዓ. ም የምስጋና መስዋዕተ ቅዳሴን አሳርገዋል። በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ውስጥ ባሳረጉት የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ላይ የምክር ቤቱ ብጹዓን ካርዲናሎች እና ጳጳሳት ተካፋይ ሆነዋል። በአውሮፓ የሚገኙ ክርስቲያኖች እና ብጹዓን ጳጳሳትን ሊያስቡባቸው የሚገቡ ሶስት ቃላት መኖራቸውን ቅዱስነታቸው ገልጸው፣ እነርሱም ማሰላሰል ፣ መገንባት እና መመልከት ናቸው ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ከመስከረም 13-16/2014 ዓ. ም ድረስ በሚከበረው የአውሮጳ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ምክር ቤት 50ኛ ዓመት የወርቅ ኢዮቤልዩ ክብረ በዓል ላይ፣ እንዲሁም በምክር ቤቱ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ለመገኘት የአውሮጳ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት በሮም ከተማ የሚገኙ መሆናቸው ታውቋል። ቅዱስነታቸው በጸሎት ሥነ-ሥርዓቱ ወቅት ባሰሙት ስብከት፣ ብጹዓን ጳጳሳቱ ሐዋርያዊ ጉዞአቸውን እንዲያሰቡት፣ የእግዚአብሔርን ቤት መልሰው እንዲገነቡት እና ሌሎች ሰዎችን መመልከት እንደሚገባ አሳስበዋል።

ማሰላሰል

እግዚአብሔር በብሉይ ኪዳኑ፣ በነቢዩ ሐጌ በኩል፣ ሕይወታችንን እንዴት እንደምንኖር እንድናሰላስል ይጋብዘናል ያሉት ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ ነብይ ሐጌ በትንቢቱ በምዕ. 1: 5 . 7 ላይ “በልባችሁ መንገዳችሁን አስቡ” በማለት ሁለት ጊዜ መናገሩን በማስታወስ፣ ብጹዓን ጳጳሳቱም ሐዋርያዊ መንገዳቸው እንዲያስቡት አደራ ብለዋል። “በልባችሁ መንገዳችሁን አስቡ” የሚሉ ቃላት ፈታኝ ቃላት መሆናቸውን ገልጸው ምክንያቱም “ዛሬ በአውሮፓ ውስጥ የምንገኝ ክርስቲያኖች ባህሎቻችን በሚሰጡን ደህንነት ፣ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን በጋራ መግባባት በመዋቅሮቻችን ፣ በቤቶቻችን እና በቤተክርስቲያኖቻችን ውስጥ በምቾት ተረጋግተን በመኖራችን ፈተና ውስጥ ልንወድቅ እንችላለን” ብለው፣ “ነገር ግን በሌላ ወገን በዙሪያችን የሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት ባዶ መሆናቸውን እና ኢየሱስ ክርስቶስም እየተረሳ መሄዱን እናስተውላለን” ብለዋል። ከዚህም ጋር በማያያዝ ለብጹዓን ጳጳሳቱ እና መስዋዕተ ቅዳሴውን ለተካፈሉት እንግዶች ባቀረቡት ጥያቄ “እግዚአብሔር የማይርባቸው እና የማይጠማቸው ሰዎች ስንት አሉ?” ብለዋል።

“ይህ የሆነው ክፉዎች ስለሆኑ ሳይሆን፣ ነገር ግን በእነርሱ ልብ ውስጥ የእምነትን ረሃብ የሚቀሰቅስ እና ጥማትን የሚያረካ ባለመኖሩ ነው” ብለው “በሁኔታው የሚንጨነቅ ቢንሆንም ምላሽ መስጠት ይኖርብናል” ብለዋል። በእግዚአብሔር የማያምኑ ቢኖሩ ልንፈርድባቸው አይገባም ብለው “ኢየሱስን በለማግኘታቸው የተነሳ ደስታ ላልነበራቸው፣ ያንን ደስታ ላጡ ሰዎች ርህራሄ ሊሰማን ይገባል” ብለዋል።

እግዚአብሔር በነቢዩ ሐጌ በኩል ሕዝቡ እንዲያስብበት የሚጠይቀው ሌላው ጉዳይ ቸርነት መሆኑን ቅዱስነታቸው ገልጸው፣ የቸርነት ተግባር አለመኖር ደስታን እንደሚያሳጣ፣ ምክንያቱም የሰውን ልብ ሊያረካ የሚችል ፍቅር ብቻ መሆኑን አስረድተዋል። ቅዱስነታቸው አክለውም “ለችግሮች መፍትሄ የሚሆነው እና ራስን ከመውቀስ ማዳን የሚቻለው ዘወትር በነጻ የሚሰጥ የቸርነት ስጦታ በመሆኑ ሊታሰብበት ይገባል” ብለዋል።

መልሶ መገንባት      

እግዚአብሔር በብሉይ ኪዳኑ፣ በትንቢተ ሐጌ ምዕ. 1:8 ላይ “ወደ ተራራው ውጡ፣ እንጨትንም ቁረጡ፣ ቤቱንም ሥሩ፣ እኔም በእርሱ ደስ ይለኛል፣ እመሰገናለሁም” በሚለው ትዕዛዝ መሠረት ሕዝቡ ቤተመቅደሱን መልሶ የሚገነባ መሆኑን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አስታውሰዋል። በአውሮጳ ውስጥም የጋራ መኖሪያ ቤታችንን መልሰን መገንባት እንድንችል የአጭር ጊዜ ልምድን በመተው ወደ አባቶቻችን ትንቢታዊ የጋራ ራዕይ መመለስ ያስፈልጋል ብለዋል። ይህን ለማድረግ ከመሠረቱ መጀመር እንደሚያስፈልግ አስረድተው፣ በመልካም ዜና፣ በመቀራረብ እና በምስክርነት ላይ የተመሠረተውን የቤተክርስቲያን ሕያው ባሕል መከተል ያስፈልጋል ብለዋል።

ለሁል ጊዜ የምትሆን እና በሁሉ ቦታ የምትገኝ ቤተክርስቲያንን መልሰን መገንባት ያለብን ለራሳችን በሚመች መንገድ ሳይሆን ለእግዚአብሔር የምናቀርበውን አምልኮ እና ለጎረቤቶቻችን ያለንን ፍቅር መሠረት በማድረግ መሆን እንዳለበት ቅዱስነታቸው አሳስበዋል። “መልሶ መገንባት የጋራ ጥረትን እና አንድነትን ይጠይቃል” ያሉት ቅዱስነታቸው፣ “መልሶ መገንባት ማለት በሁሉም የሕይወት ደረጃ አንድነትን በማጉላት ኅብረትን የማሳደግ ጥበበ ነው” ብለዋል።

መመልከት

ለሁል ጊዜ የምትሆን እና በሁሉም ቦታ የምትገኝ ቤተክርስቲያንን መልሰን የምንገነባ ከሆነ ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን መመልከት እንችላለን ብለዋል። “በአውሮፓ ውስጥ ብዙ ሰዎች እምነትን እንደ ቅርስ ይመለከቱታል ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ይህ የሆነበት ምክንያት በሕይወታቸው ውስጥ የኢየሱስ ክርስቶስን ሥራ ገና ስላላዩት እና እኛም በሕይወት ምስክርነት ስላላሳየናቸው ነው” ብለው፣ በጎቹን የሚወድ፣ እያንዳንዱን በስማቸው የሚጠራውን፣ በትከሻው የሚሸከማቸውን ኢየሱስን፣ እኛ የምንሰብክላቸውን እና ሊታይ የማይችል ስሜቱን በቀላሉ ሊያዩት አይችሉም” ብለዋል። በመጨረሻም ይህ መለኮታዊ ፣ መሐሪ እና ኃያል ፍቅር፣ በቅዱስ ወንጌል መታደስ የሚገኝ መሆኑን እና  ከኢየሱስ ክርስቶስ የተገኘውን ድነት ማወቅ የሚቻለው በፍቅር በሚደረግ ቆራጥ ውሳኔ አማካይነት መሆኑን በማስረዳት ስብከታቸውን አጠቃልለዋል።  

24 September 2021, 14:22