ፈልግ

ለቤተክርስቲያን መንፈሳዊ ማኅበራት እና እንቅስቃሴዎች አስተባባሪዎች የተዘጋጀ ስብሰባ ለቤተክርስቲያን መንፈሳዊ ማኅበራት እና እንቅስቃሴዎች አስተባባሪዎች የተዘጋጀ ስብሰባ  

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ የምዕመናን ማኅበራት ሐዋርያዊ ሃላፊነታቸውን በሚገባ እንዲያውቁት አሳሰቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ለቤተክርስቲያን መንፈሳዊ ማኅበራት እና አዳዲስ እንቅስቃሴዎች አስተባባሪዎች ባስተላለፉት መልዕክት፣ የምዕመናን ማኅበራት ሐዋርያዊ ሃላፊነታቸውን ለይተው እንዲያውቁ እና ከሥልጣን ምኞት አደጋ መጠንቀቅ እንዳለባቸው አሳስበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ለቤተክርስቲያን መንፈሳዊ ማኅበራት እና አዳዲስ እንቅስቃሴዎች አስተባባሪዎች የተዘጋጀውን ስብሰባ ያስተባበረው፣ በቅድስት መንበር የምእመናንና የቤተሰብ ሕይወት መምሪያ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት መሆኑ ታውቋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ የስብሰባው ተውካዮች ከምዕመናን በኩል ሆነው በማኅበራዊ ሕይወት ዘርፎች ተሰማርተው ለሚያበረክቱት ሐዋርያዊ አገልግሎት እና የወንጌል ምስክነት ምስጋናቸውን አቅርበውላቸዋል። የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በርካታ ሰዎችን ለስቃይ መዳረጉን ቅዱስነታቸው አስታውሰው፣ አደጋው በተለይም በማደግ ላይ ባሉት አገሮች ውስጥ የከፋ እንደሆነ እና በየአገሮቻቸው ይህን አስከፊ ማኅበራዊ ችግር ለመቀነስ ላደረጉት ጥረት ምስጋናቸውን አቅርበውላቸዋል።

የስብሰባው ተካፋዮቹ እውነተኛ የቤተክርስቲያን ተልዕኮን በመፈጸም ላይ እንደሚገኙ የገለጹት ቅዱስነታቸው፣ ተልዕኮዋቸው በችግር ላይ የሚገኙትን፣ ከማኅበረሰቡ የተገለሉ አቅመ ደካሞችን ለመርዳት ያለመ መሆኑን አስታውሰዋል። ቅዱስነታቸው አክለውም፣ የሌሎችን ድህነት ብቻ ሳይሆን ፣ ከሁሉም በላይ የራሳችንንም ድህነት ማስታወሱ መልካም ይሆንልናል ብለዋል።

አዲስ ድንጋጌ ይፋ ስለመሆኑ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ ዓለም አቀፍ ካቶሊካዊ የቤተክርስቲያን ማኅበራትን የሚመለከት አዲስ ድንጋጌ በሰኔ ወር 2013 ዓ. ም ይፋ መሆኑን አስታውሰው፣ ድንጋጌው አዳዲስ ደንቦችን ተቀብለን ለመጭ ጊዜ ከወዲሁ መዘጋጀት እንድሚያስፈልግ ያሳስባል ብለዋል። የአዲሱ ድንጋጌ መሠረታዊ ሃሳብ፣ ከቅርብ አስርት ዓመታት ወዲህ የታዩት ለውጦች በቀድሞ ድንጋጌ ላይ ለውጦችን ማድረግ እንደሚያስፈልግ ይጠይቁናል ብለዋል። የስብሰባቸው ዋና ጭብጥ “በቤተክርስቲያን ማህበራት ውስጥ የምዕመናን መሪዎች ኃላፊነት” የሚል መሆኑን ቅዱስነታቸው አስታውሰው፣ የቤተክርስቲያን አገልግሎት ሃላፊነት ለተሰጣቸው የቤተክርስቲያን ማኅበራት ሃላፊዎች ብቻ ሳይሆን ለመላዋ ቤተክርስቲያንም እጅግ አስፈላጊ መሆኑን አስረድተዋል። ቅዱስነታቸው አክለውም ቅድስት መንበር ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በርካታ ያልተስተካከሉ ነገሮች ለማቃናት ጥረት በማድረግ ላይ መሆኗን ገልጸው፣ እነዚህ ችግሮች የተነሱለት ተልዕኮ ፍላጎትን በማዳከም እና ማራኪነቱን በመቀንስ እንቅፋት ሆነው መቆየታቸውን ገልጸዋል።          

የአገልግሎት ጥሪ

ለምዕመናን የሚሰጥ የቤተክርስቲያን ማኅበራት ሃላፊነት እጅግ አስፈላጊ መሆኑን ቅዱስነታቸው ገልጸው፣ ሃላፊነቱ ከአገልግሎት ጥሪ ባለፈ ሌላ ምንም እንዳልሆነ አስረድተዋል። “ነገር ግን ለአንድ ክርስቲያን፣ ማገልገል ማለት ምን ማለት ነው?” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ከዚህ በፊት ባስተላለፉት መልዕክት፣ አንድ ክርስቲያን የእግዚአብሔር እና የሌሎች አገልጋይ ከመሆን የሚያግዱ ሁለት እንቅፋቶች መኖራቸውን ገልጸው፣ እነርሱም የስልጣን ጥማት እና ታማኝነት ማጣት ናቸው ብለዋል።

የስልጣን ጥማት

ስንት ጊዜ ሌሎች የእኛን “የሥልጣን ምኞት” እንዲሰማቸው አድርገናል? ያሉት ቅዱስነታቸው፣ በቤተክርስቲያን ሕይወት የስልጣን ምኞት በተለያዩ መንገዶች እንደሚገልጽ እና ከእነዚህም አንዱ ለምሳሌ በቤተክርስቲያን ማኅበራት ውስጥ ያለንን ሚና በመጠቀም፣ በተግባር ተተርጉመው የማይታዩ ሃላፊነቶችን በሌሎች ጫንቃ ላይ መጣል እንደሆነ እና ይህም በእያንዳንዱ እንቅስቃሴ ውስጥ ገብቶ ለመታየት ያለውን ምኞት በማሳየት የቤተክርስቲያን አገልግሎት አቅምን የሚያዳክም መሆኑን አስረድተዋል።

ታማኝነት ማጣት

አንድ ክርስቲያን የእግዚአብሔር እና የሌሎች አገልጋይ ከመሆን የሚያግድ ሌላው እንቅፋት ታማኝነትን ማጣት እንደሆነ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አስረድተዋል። በቤተክርስቲያን አገልግሎት መካከል ታማኝነትን ማጣት የሚመጣው አንድ ክርስቲያን እግዚአብሔርን እና የእግዚአብሔር ያልሆነ ሌላ ነገርን ማገልገል ሲጀምር ነው ብለዋል። ታማኝነትን ማጣት የሚመጣው ራሳችንን ብቸኛ ችግር ፈቺዎች አድርገን ስናቀርብ እና ሃላፊነት ካለባቸው ሰዎች በላይ ውሳኔን ለመስጠት ስንሞክር ነው ብለዋል። በመሆኑም “ለቤተክርስቲያን ጥቅም እንዲሆን በተቀበሉት ስጦታዎች ላይ ማንም ጌታ ሊሆን አይችልም፣ ማንም ሊያደናቅፈው አይገባም” ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ፍራንችስኮስ ብጹዓን ጳጳሳት ለቤተክርስቲያን መንፈሳዊ ማኅበራት እና አዳዲስ እንቅስቃሴዎች አስተባባሪዎች ያስተላለፉትን መልዕክት ባጠቃለሉበት ወቅት፣ የቤተክርስቲያን ሕያው አባላት በመሆናችን በእያንዳንዱ የቤተክርስቲያን ማኅበራት እና እንቅስቃሴዎች እና በእኛ መካከል በሚሠራ በመንፈስ ቅዱስ መታመን ይኖርብናል ብለዋል። በአገልግሎት ጥሪ ላይ ቤተክርስቲያን እንድታስብበት ስልጣን እና አደራ የተሰጣት ለዚህ ነው ብለው፣ የመንፈሳዊ ማኅበራት እና አዳዲስ እንቅስቃሴዎች አስተባባሪዎች፣ ዛሬ በአዲስ መልክ የተሰጣቸውን ሐዋርያዊ ሃላፊነት እና ትንቢታዊ ስጦታን በሚገባ እንዲገነዘቡት ቅዱስነታቸው አሳስበዋል።

17 September 2021, 16:15