ፈልግ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ በቡዳፔስት ከምዕመናን ጋር በመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት ላይ ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ በቡዳፔስት ከምዕመናን ጋር በመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት ላይ 

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ ቅዱስ መስቀል የሃንጋሪ ሕዝብ ያለፈውን እና መጭውን ታሪክ የሚያገናኝ ይሁን ማለታቸው ተገለጸ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በሃንጋሪ ዋና ከተማ ቡዳፔስት የመሩትን የ52ኛ ዓለም አቀፍ የቅዱስ ቁርባን ጉባኤ መዝጊያ መስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ሥነ-ሥርዓት ከመፈጸማቸው በፊት ባደረጉት ንግግር፣ በአገሪቱ የሚገኙ የሐይማኖት መሪዎችን፣ የመንግሥት ባለሥልጣናትን እና መላውን የሃንጋሪ ሕዝብን አመስግነው፣ ቅዱስ መስቀልን ካለፈው ታሪክ ወደ መጭው ታሪክ የሚሸጋገሩበት ድልድይ አድርገው እንዲጠቀሙት አሳስበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በዋና ከተማ ቡዳፔስት በሚገኝ የአርበኞች አደባባይ ከተሰበሰቡት በርካታ ምዕመና ጋር ያቀረቡትን መስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ፈጽመው የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት ከማቅረባቸው በፊት ባደረጉት ንግግር፣ የቅዱስ ቁርባን ሥርዓት ምስጋና የሚቀርብበት ሥርዓት እንደሆነ አስረድተዋል። “በዓለም አቀፍ የቅዱስ ቁርባን ጉባኤ መዝጊያ ላይ ለመገኘት ወደ ሃንጋሪ ቡዳፔስት ያደረጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝት ከማጠናቀቃቸው በፊት ልባዊ ምስጋናቸውን ማቅረብ እንደሚፈልጉ ገልጸዋል። በዚህም ለሃንጋር ክርስቲያን ማኅበረሰብ ምስጋናቸውን አቅርበው ለሥርዓተ አምልኮአቸው ያላቸውን ክብር ገልጸዋል። በማከልም ለታሪካቸው፣ በአገሩ የሚገኙ ካቶሊካዊ ምዕመናንን ጨምሮ የሌሎች እምነቶች ተከታይ የሆኑ ወንድሞች እና እህቶች ወደ አንድነት የሚያደርጉትን የጋራ ጉዞን የሚደግፉት መሆኑን ገልጸዋል። ቅዱስነታቸው በአገሩ ቋንቋ ምስጋናቸውን አቅርበው፣ ቅዱስ መስቀልን ካለፈው ታሪክ ወደ መጭው ታሪክ የሚሸጋገሩበት ድልድይ እንዲያደርጉት ተመኝተው፣ ይህ አንድነታቸው በጠንካራ መሠረት ላይ እንዲቆም እና ለሌሎችም ዕድል የሚያመቻች እንዲሆን መመኘታቸውን ገልጸዋል።  

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የ52ኛው ዓለም አቀፍ የቅዱስ ቁርባን ጉባኤ መዝጊያ የቅዳሴ ጸሎት ከመፈጸማቸው በፊት፣ በፖላንድ ዋርሶ ከተማ ውስጥ እሑድ መስከረም 2/2014 ዓ. ም ብጽዕናቸው የታወጀላቸው ሁለት የቤተክርስቲያን አገልጋዮችን እነርሱም ካርዲናል ስቴፋን ዊዝንስኪን እና የቅዱስ መስቀል አገልጋዮች ፍራንችስካዊ እህቶች ማኅበር መሥራች የሆኑትን እህት ኤልሳቤጥ ዛካን አስታውሰዋል። ሁለቱም ለቅዱስ መስቀል የነበራቸው ፍቅር ከፍተኛ እንደነበር አስታውሰዋል። በፖላንድ አምባ ገነን መንግሥት ተይዘው የታሰሩት እና የፖላንድ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ጳጳሳት ጉባኤ መሪ የነበሩት ካርዲናል ስቴፋን፣ የነጻነት እና የሰው ልጅ ክብር ተሟጋች የነበሩ ደፋር የቤተክርስቲያን አገልጋይ እንደነበር አስታውሰዋል። የዓይን ብርሃኗን በወጣትነት ዕድሜ ያጣች እህት ኤልሳቤጥ ሕይወቷን በሙሉ ዓይነ ስውራንን ስታገለግል መኖሯን አስታውሰው፣ በመጨረሻም ምዕመናን በሙሉ በሚያቀርቡት የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቅዱስ ስም ውዳሴን እና ክብርን በመስጠት ጸሎታቸውን እንዲያቅርቡ በማሳሰብ “የሃንጋሪን ሕዝብ እግዚአብሔር ይባርክ” ብለው ንግግራቸውን አጠቃልለዋል።

13 September 2021, 12:07