ፈልግ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ ክርስቲያኖች የጋራ መኖሪያ ምድርን ከውድመት ለማዳን እንዲተባበሩ አሳሰቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ረቡዕ ነሐሴ 26/2013 ዓ. ም. ባቀረቡት ሳምንታዊ ጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ፣ ክርስቲያኖች የጋራ መኖሪያ ምድራችንን ከጥፋት ለማዳን እንዲሰሩ አሳስበዋል። እ. አ. አ የ2021 ዓ. ም. የፍጥረት መታሰቢያ ወቅት ዛሬ ነሐሴ 26/2013 ዓ. ም መጀመሩን ገልጸው፣ ከቁንስጣንጢንያው ፓትሪያርክ ብጹዕ ወቅዱስ በርተሎሜዎስ ቀዳማዊ እና ከካንተር በሪው የአንግሊካን ቤተክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ አቡነ ጃስቲን ዌልቢ ጋር በኅብረት ያዘጋጁትን መልዕክት በሚቀጥሉት ቀናት ውስጥ ይፋ የሚያደርጉ መሆኑን ገልጸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ዛሬ ረፋዱ ላይ በቅዱስ ጳውሎስ 6ኛ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ለተገኙት ምዕመናን ባስተላለፉት መልዕክት፣ የጋራ መኖሪያ ምድራችን በከፍተኛ አደጋ ውስጥ የምትገኝ መሆኑኗን ገልጸው፣ ለምድራችን ጸሎት የሚደረግበት ዓለም አቀፍ የፍጥረት መታሰቢያ ቀን፣ የልዩ ልዩ አብያተ ክርስቲያናት ምዕመናን በጸሎት እንዲተባበሩ፣ የጋራ መኖሪያ ምድራችንን ከጥፋት ለማዳን በርትተው እንዲሠሩ አደራ ብለዋል።

ዛሬ ረቡዕ ነሐሴ 26/2013 ዓ. ም. በቅዱስ ጳውሎስ 6ኛ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ሳምንታዊ ጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ባቀረቡበት ወቅት፣ ከቁንስጣንጢንያው ፓትሪያርክ ብጹዕ ወቅዱስ በርተሎሜዎስ ቀዳማዊ እና ከካንተር በሪው የአንግሊካን ቤተክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ አቡነ ጃስቲን ዌልቢ ጋር በየዓመቱ በሚያስተላልፉት መልዕክት ከእግዚአብሔር እና ከፍጥረታቱ ሁሉ ጋር ያላቸውን ግንኙነት የሚያድሱ መሆኑ አስረድተዋል።

ቅዱስነታቸው ለምዕመናኑ ባቀረቡት መልዕክት፣ ዛሬ የተጀመረው ዓለም አቀፍ የፍጥረታት መታሰቢያ ቀን፣ የአሲሲው ቅዱስ ፍራንችስኮስ ዓመታዊ በዓል በሚከበርበት መስከረም 24/2014 የሚጠናቀቅ መሆኑን ገልጸዋል። ለዘንድሮ በዓል የተመረጠው መሪ ቃልም “የሁላችን መኖሪያ ምድራችን የሆነውን የእግዚአብሔርን ቤት እናድስ” የሚል መሆኑን ተናግረዋል። ከቁንስጣንጢንያው ፓትሪያርክ ብጹዕ ወቅዱስ በርተሎሜዎስ ቀዳማዊ እና ከካንተር በሪው የአንግሊካን ቤተክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ አቡነ ጃስቲን ዌልቢ ጋር በኅብረት ያዘጋጁትን መልዕክት በሚቀጥሉት ቀናት ውስጥ ይፋ እንደሚሆን ገልጸው፣ ከሌሎች ልዩ ልዩ የእምነት ተከታይ ወንድሞች እና እህቶች ጋር በኅብረት የጋራ መኖሪያ ምድራችንን ከጥፋት ለማዳን በርትቶ መሥራት እንደሚያስፈልግ አደራ ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በዛሬው ዕለት ባቀረቡት ሳምንታዊው ጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ላይ በመቶዎች የሚቆጠሩ የ “ውዳሴ ላንተ ይሁን” እንቅስቃሴ አባላትም መገኘታቸው የታየ ሲሆን፣ የጋራ መኖሪያ ምድራችንን ለሚጋሩ ሁሉ ቦታን የሚሰጥ፣ ቁርጠኝነትን ለማሳየት የታሰበ፣ የፍጥረት መታሰቢያ ወቅትን ለመጀመር እና በትክክል ለማክበር እንዲቻል የቀረበ የዚህ ዓመት ምልክት የአብርሃም ድንኳን መሆኑ ታውቋል። እ. አ. አ. በ 2015 የተመሠረተው “ውዳሴ ላንተ ይሁን” እንቅስቃሴ፣ አብርሃምን እና የዘፍጥረት መጽሐፍን በመጥቀስ ፣ ከማህበረሰብ ለተገለሉት እና ተጋላጭ ለሆኑት በሙሉ የእንግዳ ተቀባይነት ምልክት እንዲሆን ድንኳን በመትከል፣ ለሁሉም ሰው የጋራ ቤት ለመፍጠር ያለውን ቁርጠኝነት ገልጸዋል።

01 September 2021, 16:38