ፈልግ

በቅድስት መንበር የስብከተ ወንጌል አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት የተዘጋጀ ስብሰባ በቅድስት መንበር የስብከተ ወንጌል አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት የተዘጋጀ ስብሰባ  

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ “የትምህርተ ክርስቶስ መምህራን ቅዱስ ቁርባንን በኑሮአቸው የሚመሰክሩ ናቸው።”

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ የአውሮፓ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ የትምህርተ ክርስቶስ አገልግሎት መምሪያ ተወካዮች ጋር ተገናኝተው መልዕክት አስተላልፈዋል። ተወካዮቹ በሮም የተገኙት የትምህርተ ክርስቶስ አገልግሎት ስርጭትን አስመልክቶ በቫቲካን የሚካሄደውን ስብሰባ ለመካፈል መሆኑ ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ቅዱስነታቸው በመልዕክታቸው፣ የትምህርተ ክርስቶስ መምህራን “ካቴክስቶች” በቅዱስ ቁርባን ክብረ በዓል ወይም በመስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ-ሥርዓት ላይ በመገኘት ከመንፈስ ቅዱስ በሚያገኙት ጥበብ በመታገዝ እምነትን ወደ ሌሎች የሚያስተላልፉ መሆናቸውን አስረድተዋል። “የትምህረተ ክርስቶስ መምህራን የሚገኙበት ሥፍራ የቅዱስ ቁርባን ክብረ በዓል ነው” ያሉት ቅዱስነታቸው፣ ይህም እግዚአብሔርን በሕይወታቸው መካከል ሊያገኙት የሚችሉባቸውን መንገዶች ከወንድሞቻቸው እና ከእህቶቻቸው ጋር ሆነው ለማወቅ ጥረት የሚያደርጉበት ሥፍራ መሆኑን ገልጸዋል። 

በቅድስት መንበር የስብከተ ወንጌል አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ዓርብ መስከረም 7/2014 ዓ. ም. ባዘጋጀው ስብሰባ ላይ፣ ከአውሮፓ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤዎች የተወጣቱ ሰማንያ የሚሆኑ የትምህርተ ክርስቶስ አገልግሎት መምሪያ ተጠሪዎች ተካፋይ ሆነዋል።

በሃንጋሪ ዋና ከተማ ቡዳፔስት፣ ከነሐሴ 30/2013 ዓ. ም. እስከ እሑድ መስከረም 2/2014 ዓ. ም. ድረስ የተካሄደውን 52ኛ ዓለም አቀፍ የቅዱስ ቁርባን ጉባኤ ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ “የትምህረተ ክርስቶስ መምህራን በወንጌል አገልግሎታቸው ውጤታማ ሊሆኑ የሚችሉት ትኩረታቸውን በቅዱስ ቁርባን ምስጢር ላይ ሲያደርጉ ነው” ብለዋል።

እምነት ተጨባጭ የሚሆነው በዕለት ተዕለት ሕይወት ነው

ኢየሱስ ክርስቶስ የአይሁድን የፋሲካ ራት ከሐዋርያቱ ጋር ለመብላት ሁሉን ካዘጋጀ በኋላ፣ ከሐዋርያቱ መካከል ሁለቱን ወደ ከተማው እንደላካቸው ቅዱስነታቸው አስታውሰው፣ ሁለቱ ሐዋርያት ቀድመው ወደ ከተማው የተላኩትም በከተማው የሚገኙ ክርስቲያኖች የእምነት ምስጢርን ለማክበር እንዲዘጋጁ ለማሳሰብ መሆኑን አስታውሰዋል። ትምህርተ ክርስቶስ የቃላት ቀመር ወይም የንድፈ ሀሳብ ዕውቀት ሳይሆን ፣ በሚኖሩበት እና በሚሠሩበት አካባቢ ኢየሱስ ክርስቶስን ካገኙት ወንድሞች እና እህቶች ጋር ለመገናኘት የሚማሩት የእምነት ምስጢራት ተሞክሮ መሆኑን ቅዱስነታቸው አስረድተዋል። አክለውም፣ የትምህርተ ክርስቶስ ዋና ዓላማ፣ ከሞት የተነሳው ኢየሱስ ክርስቶስ ሰውን ሁሉ እንደሚወድ እና መቼም ቢሆን እንደማይተዋቸው አጉልቶ ለማሳየት ነው ብለው፣ በትምህርተ ክርስቶስ አገልግሎት፣ በተለያዩ ደረጃዎችም ይህ ምስክርነት መቋረጥ የለበትም ብለዋል።

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ በግንቦት ወር 2013 ዓ. ም. የትምህርተ ክርስቶስ አገልግሎትን በአዲስ መልክ እንዲቋቋም ማድረጋቸውን ገልጸው የአገልግሎት መጀመሪያ ሥነ-ሥርዓቱም በዝግጅት ላይ መሆኑን አስረድተዋል። ለመምሪያው ተወካዮች ባስተላለፉት መልዕክት፣ የትምህርተ ክርስቶስ መምህራን በመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት የሚያከብሩት የቅዱስ ቁርባን ምስጢር የክርስቲያን ማህበረሰብ እምነት እንገለጽ በዕለት ተዕለት ሕይወት ምስክርነትን የሚሰጡ መሆናቸውን አስረድተዋል። ደከመን ሰለቸን ሳይሉ የሚያቀርቡት የወንጌል ምሕረት ምስክርነት፣ ምዕመናን ወደ ቅዱስ ቃሉ ቀርበው የቅዱስ ቁርባንን ምስጢር በተሻለ መንገድ ለማክበር እንዲችሉ የሚያደርግ የመልካም ሥራ ውጤት መሆኑንም አስረድተዋል።

አዳዲስ ማራኪ ዘዴዎች የታከሉበት የወንጌል አገልግሎት

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ የወንጌል አገልግሎት የቀደሙ ትምህርቶችን መደጋገም ሳይሆን መንፈስ ቅዱስ የሚያሳየውን መንገድ በመከተል ወንጌል የሚሰበክለትን ሕዝብ ድምጽ ማድመጥ፣ ባሕላቸውን፣ ታሪካቸውን፣ ልባቸውን እና አመለካከታቸውን መረዳት መቻል መሆኑን አብራርተዋል። የወንጌል አገልግሎት፣ ከሁሉም በላይ በእግዚአብሔር ቃል ፣ ሕያው ወንጌል ከሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ጋር በመሆን ያልተገለፁትን ቋንቋዎች ማዳመጥን ይጠይቃል ብለዋል።

የአውሮፓ ተጨባጭ እውነታ

በመሆኑም ትምህርተ ክርስቶስ በአውሮፓ ውስጥ የቤተክርስቲያኒቱ አስቸኳይ ተልዕኮ መሆኑን ገልጸው፣ የአህጉሪቱ ክርስቲያናዊ ባሕል በታሪክ ብቻ የሚነገር እንዳይሆን አሳስበዋል። ትምህርተ ክርስቶስ ከልብ ወደ ልብ፣ ከአእምሮ ወደ አእምሮ፣ ከሕይወት ወደ ሕይወት በተግባር ሲኖሩት የቆየ መሆኑን አስረድተው፣ የትምህርተ ክርስቲያን መምህራን በአገልግሎታቸው መካከል ከመንፈስ ቅዱስ በሚያገኙት የፈጠራ ችሎታ እንዲመሩ በማለት አሳስበዋል።

18 September 2021, 16:51