ፈልግ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ አገራት የአፍጋኒስታን ስደተኞችን ተቀብለው እንዲያስተናግዱ ተማጸኑ

በዚህ የችግር ወቅት በርካታ አፍጋኒስታዊያን ዜጎች ጥገኝነትን በመጠየቅ ላይ እንዳሉ አስታውሰው፣ በተለይም አቅመ ደካማ እና ተጋላጭ የሆኑትን በሙሉ በጸሎታቸው የሚያስታውሷቸው መሆኑን ገልጸዋል። በአፍጋኒታን ውስጥ በተፈጠረው የፖለቲካ ቀውስ ምክንያት ለተፈናቀሉት በርካታ ቤተሰቦች ሰብዓዊ ዕርዳታ እንዲደርሳቸው፣ አስፈላጊው ጥበቃ እንዲደረግላቸው፣ ለሕይወታቸው ደህንነትን እንዲያገኙ በጸሎታቸው አስታውሰዋል። በአገሪቱ ሰላም እና መረጋጋት ሆኖ ወጣቶች ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዲመለሱ እና ለሰብዓዊ ዕድገት የሚያስፈልጉ ድጋፎችን እንዲያገኙ ተመኝተዋል። አገር ውስጥ ያሉት፣ በስደት ጉዞ ላይ የሚገኙ እና በሌሎች አገራት የጥገኝነት ሕይወት የሚኖሩ አፍጋኒያውያን በሙሉ ክብራቸው ተጠብቆ፣ ከጎረቤቶቻቸው ጋር በሰላም እና በወንድማማችነት የሚኖሩበትን ዕድል ተመኝተውላቸዋል።

ቀጥለውም በቅርቡ በኃይለኛ አውሎ ነፋስ የተጠቁ የሰሜን አሜሪካ ሕዝቦችን በጸሎታቸው እንደሚያስታውሷቸው አረጋግጠው፣ ሕይወታቸውን ላጡት እግዚአብሔር ምሕረቱን እንዲሰጣቸው፣ በአደጋው ምክንያት በችግር እና በስቃይ ውስጥ ለሚገኙት እግዚአብሔር ድጋፍ እንዲሆናቸው በጸሎታቸው አስታውሰዋል።

06 September 2021, 15:57