ፈልግ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ ፍቅር ታማኝነትን እና ሃላፊነትን የሚጠይቅ መሆኑን አሳሰቡ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ወደ ስሎቫኪያ ባደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት ወቅት ከአገሩ ወጣቶች ጋር መገናኘታቸው ታውቋል። ቅዱስነታቸው በስሎቫኪያ ዋና ከተማ ብራቲስላቫ በሚገኝ ኮሺሴ ሎኮሞቲቫ ስቴዲዬም ተገኝተው ለወጣቶች ባደረጉት ንግግር፣ እርስ በእርስ ስለ መዋደድ እና ስለ ቅዱስ መስቀል ፍቅር በማስመልከት ከወጣቶች ለቀረበላቸው ሦስት ጥያቄዎች መልስ ሰጥተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ወደ ስሎቫኪያ ላደረጉት ሐዋርያው ጉብኝት የመጨረሻ ክፍል በሆነው ዝግጅት፣ እ. አ. አ በ2018 ዓ. ም የአገሩ ተወላጅ ወጣት ሐና ኮሌሳሮቫ ብጽዕና በታወጀበት በኮሺሴ ሎኮሞቲቫ ስቴዲዬም ከተሰበሰቡት በርካታ ወጣቶች ጋር ቅዱስነታቸው መገናኘታቸው ታውቋል። ቅዱስነታቸው ከወጣቶች ለቀረበላቸው ሦስት ጥያቄዎች መልስ ሰጥተዋል።

በሁለት ሰዎች መካከል ስለሚኖር ፍቅር በተመለከተ ለቀረባላቸው ጥያቄ ቅዱስነታቸው በሰጡት መልስ፣ በሕይወት ውስጥ ሊያጋጥሙ ከሚችሉ ሌሎች ነገሮች ሁሉ ፍቅር ድንቅ እንደሆነ ገልጸው ነገር ግን ቀላል ጉዳይ አለመሆኑንም አስረድተው፣ ማስረዳቱ ቀላል ባይሆንም የሁላችን ታላቅ ምኞት መሆኑን ተናግረዋል። ፍቅርን ለመገንዘብ በውጫዊ ገጽታ ብቻ የማይመካ እና ለፍቅር ዝቅተኛ ግምትን የማይሰጥ አዲስ መለካከት ሊኖር እንደሚጋባ አስረድተዋል። ፍቅር በቀላሉ በስሜት የሚገልጽ ሳይሆን ታማኝነትን እና ሃላፊነትን የሚጠይቅ ስጦታ መሆኑን አስረድተዋል። “እዚህ የተገኘንበት ምክንያት እንዲሁ ለመገኘት ብቻ ሳይሆን በሕይወታችን መካከል አንድ ነገር ለማከናወን ነው” ብለው ወጣቶች ሕይወታቸውን በከንቱ ሳያሳልፉ የሚያልሙትን በድፍረት እና በቆራጥነት ማከናወን እንደሚገባ አሳስበዋል።

መሠረትን አለመዘንጋት

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ለወጣቶች በሰጡት ምክር አዘል መልሳቸው፣ ፍቅር ፍሬያማ እንዲሆን ከተፈለገ የዕድገታቸውን መሠረት መዘንጋት እንደሌለባቸ አሳስበው፣ ባሁኑ ጊዜ በዓለማችን ውስጥ ያለማንም ምክር እና አስተያየት ነገሮችን በችኮላ በራስ ውሳኔ እና አስተያየት የማከናወን አደጋ መኖሩን አስታውሰዋል። ይህ ከሚሆን ቆም በማለት ለሌሎች ራስን ክፍት ማድረግ እና ሌሎችን ለማዳመጥ ዝግጁ መሆን እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል። ዛሬ ላይ መንገድን ሊያደናቅፉ የሚሞክሩ በርካታ እንቅፋቶች ወይም ኃይሎች መኖራቸውን የተናገሩት ቅዱስነታቸው፣ ሁሉንም ለመውቀስ የተዘጋጁ ብዙ ሰዎች መኖራቸውን፣ አሉታዊነትን የሚያሰራጩ፣ ቅሬታን ብቻ በማቅረብ የታወቁ በርካታ ሰዎች መኖራቸውን ገልጸዋል። አፍራሽ አስተሳሰብ እና ማጉረምረም ክርስቲያናዊ ተግባር ባለመሆኑ ወጣቶች ጥንቃቄን እንዲያደርጉ አሳስበዋል።

እንቅፋቶችን ማለፍ

የእግዚአብሔርን ምሕረት ለመቀበል በሚደረግ ጉዞ ወቅት የሚያጋጥሙ መሰናክሎችን እንዴት ማለፍ እንደሚቻል ለቀረበላቸው ጥያቄ ቅዱስነታቸው ሲመልሱ፣ “ይህም ቢሆን ነገሮችን እንዴት እንደምናይ እና በጣም አስፈላጊ የሆነውን ነገር የመመልከት ጉዳይ ነው” ብለዋል። “ለመናዘዝ በምትሄዱበት ጊዜ ስለ ምን እንደምታስቡ ብጠይቃችሁ ‘ስለ ሠራናቸው ኃጢአቶች’ ብላችሁ እንደምትመልሱልኝ አስባለሁ” ያሉት ቅዱስነታቸው፣ ነገር ግን ኃጢአቶች በእውነቱ የኑዛዜው ዋና ማዕከል አይደሉም ብለው፣ ሁሉን ነገር ይቅር የሚል እግዚአብሔር አባታችን ከሁሉ የሚቀድም መሆኑን አስርድተዋል። ለኑዛዜ የምንቀርበው ቅጣትን እና ውርደት ለመቀበል ሳይሆን ፣ ነገር ግን ወደ አፍቃሪ አባት እጆች እንደሚሮጡ ልጆች ሆነን ነው ብለው፣ ወጣቶች ከኑዛዜ በኋላ ከእግዚአብሔር ስለተቀበሉት የምሕረት ጸጋ የሚያስቡበት አጭር ጊዜ ሊኖር ይጋባል በማለት ምክራቸውን ሰጥተዋል።

መስቀልን መያዝ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመጨረሻ ጥያቄዎቻቸውን ያቀረቡት ሁለቱ ወጣቶች፣ ቅዱስ መስቀልን አጥብቀው ለመያዝ ፍርሃት እንዳይዛቸው አደራ ብለዋል። መስቀልን አጥብቆ መያዝ ፍርሃትን ለማሸነፍ እንደሚረዳ አስረድተው፣ አንድ ሰው ባቀፈን ቁጥር በራሳችን እና በሕይወታችን ውስጥ በራስ መተማመንን እናሳድጋለን ብለው፣ በመሆኑም ራሳችንን በኢየሱስ ክርስቶስ ለመታቀፍ መፍቀድ ያስፈልጋል ብለዋል። ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበትን መስቀል ማቀፍ ከኢየሱስ ክርስቶስ የሚገኝ ደስታን የሚያጎናጽፍ መሆኑን አስረድተው፣ ከኢየሱስ ክርስቶስ የሚገኝ እውነተኛ ደስታን እንደሚመኙላቸው በመግለጽ ንግግራቸውን ደምድመዋል።                          

15 September 2021, 17:12