ፈልግ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ “የሰላም መሪዎች” ፋውንዴሽን ልኡካንን በቫቲካን በተቀበሏቸው ጊዜ ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ “የሰላም መሪዎች” ፋውንዴሽን ልኡካንን በቫቲካን በተቀበሏቸው ጊዜ  

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ ለሰላም ከምን ጊዜም በላይ ጥረት ማድረግ እንደሚያስፈልግ አሳሰቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ነሐሴ 29/2013 ዓ. ም. በቫቲካን ለተቀበሏቸው “የሰላም መሪዎች” የተባለ ፋውንዴሽን ልኡካን ባደረጉት ንግግር፣ ለሰላም ከምን ጊዜም በላይ ጥረት ማድረግ እንደሚያስፈልግ አሳሰበው፣ በአገልግሎታቸው መካከል የመንግሥት መሪዎችን እና ዜጎችን በመርዳት፣ ለሰላም ወሳኝ በሆኑ ርዕሠ ጉዳዮች ላይ ተወያይተው የመፍትሄ መንገዶችን በማግኘት የበለጠ ፍትሃዊ እና የወንድማማችነት ማኅበረሰብን ለመፍጠር እንዲሠሩ ብርታት ተመኝተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“የሰላም መሪዎች” የተባለ ፋውንዴሽን ዋና ጽሕፈት ቤቱ በፈረንሳይ መዲና ፓሪስ የሚገኝ ሲሆን ዓላማው ለዜጎች እና ውሳኔ ሰጭ የመንግሥት መሪዎች እና እና ክፍል ትምህርት እና ስልጠናን በመስጠት ግጭቶች ባሉባቸው አካባቢዎች ሰላም እንዲወርድ ጥረት የሚያደርግ መሆኑ ታውቋል። “የሰላም መሪዎች” ፋውንዴሽኑ ከዓለም መንግሥታት መሪዎች መካከል፣ ለሰላም እና ለሰብዓነት ጠንካራ ተነሳሽነት ያላቸውን ሃያ መሪዎች ያሉበት መሆኑ ታውቋል።

“በታሪክ ውስጥ እጅግ አስቸጋሪ በሚባል ወቅት ላይ እንገኛለን” ያሉት ቅዱስነታቸው፣ በዓለማችን የተከሰተው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ዛሬም  ቢሆን ያልተገታ መሆኑን አስታውሰው፣ ወረርሽኙ ባስከተለው ኤኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ቀውስ ደሃው ማኅበረሰብ እጅግ የተጎዳ መሆኑን አስታውሰዋል። በመሆኑም ፋውንዴሽኑ ለሰላም የሚያደርገውን ጥረት ከምን ጊዜም በላይ በማጠናከር፣ በፖለቲካ እና በአካባቢ ጉዳዮች ዙሪያ የሚታዩ   ችግሮች፣ ከእነዚህም መካከል የረሃብ፣ የአየር ንብረት ለውጥ እና ኒውክሌር የጦር መሣሪያ ምርትን ለመከላከል ጥረት ማድረግ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣  የሰላም አስፈላጊነትን የመንግሥታት መሪዎች እና ዜጎች እንዲገነዘቡት ለማድረግ “የሰላም መሪዎች” ፋውንዴሽን በማድረግ ላይ ላለው ጥረት ምስጋናቸውን አቅርበውላቸዋል። በአካባቢ ላይ እየደረሰ ያለው አደጋ፣ የዓለም መንግሥታት መሪዎች እና ዜጎች አንዳንድ ጠቃሚ እርምጃዎችን እንዲወስዱ ያግዛቸዋል ብለው፣ ዜጎች የሚያቀርቡት ጠቃሚ ሃሳቦች እና አስተያየቶች ወደ ውሳኔ ሰጭ ክፍል ሊደርስ ይችላል ብለዋል። በዚህ ጥረት መካከል በአስተሳሰብ ልዩነት ምክንያት የግል ጥቅማቸውን የሚያስቀድሙ እንደማይጠፉ አስረድተዋል። መልካም ለውጦችን ለማምጣት ዋናው መንገድ ሃሳብን በመጋራት፣ ችግሮችን እና መነሻዎቻቸውን ለይቶ በማወቅ እና በማሳዎች መፍትሄን ማግኘት የሚቻል መሆኑን አስረድተዋል።

በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት የተፈጠረው መራራቅ እና ውጥረት ለፖለቲካዊ ተግባር እንቅፋት የፈጠረ ቢሆንም፣ የተሻለ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ለማድረግ ልዩ ዕድል እንደሚሰጥ የገለጹት ቅዱስነታቸው፣ በዚህ በመታገዝ በወዳጅነት ላይ የተመሠረተ ዓለም አቀፋዊ ማኅበራዊ ወንድማማችነትን ለማሳደግ ያግዛል ብለዋል (“ሁላችንም ወንድማማቾች ነን” ቁ. 154)። ሰላምን ለመገንባት የተለያዩ የማኅበራዊ ተቋማት ተሳትፎ ሊኖር እንደሚጋባ የገለጹት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በተጨማሪም ለሰላም የእራሳችን እና የብልህ ማኅበረሰብ አስተዋጽዖ ሊታከልበት ያስፈልጋን ብለዋል።

“ባህላዊ እና ተቋማዊ” ዘርፎች ተጨማሪ እገዛን ሊያበረክቱ እንደሚችሉ ያስታወሱት ቅዱስነታቸው፣ ባህላዊ ዘርፍ የሰውን ልጅ ክብር በማስጠበቅ ከፍተኛ ቦታ የሚሰጠው መሆኑን አስረድተው፣ ለጋራ ውይይት መንገድ በመክፈት፣ በሰዎች ልብ ውስጥ መልካምነትን በመጨመር እርግጠኝነትን የሚያሳድግ መሆኑን አስረድተዋል። ተቋማትን ማሳተፉ ለጋራ ውይይት እና መደጋገፍ ጥሩ ዕድልን የሚፈጥር መሆኑን ገልጸው፣ በመንግሥታት መካከል የሚደረጉ ዘርፈ ብዙ ስምምነቶች ዕድል መሰጠት ያስፈልጋል ብለዋል። አክለውም  ከሁለትዮሽ ስምምነቶች ይልቅ ለዘርፈ ብዙ ስምምነቶች ዕድል መሰጠቱ ሁለ ገብነት ያለው እውነተኛ የጋራ ጥቅምን ለማሳደግ እና ለደካማ መንግሥታት ዋስትና ለመስጠት ያግዛል ብለዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በንግግራቸው ማጠቃለያ ላይ፣ ፋውንዴሽኑ ሰላምን፣ ፍትህን እና ወንድማማችነት ያለበት ማህበረሰብን ለመገንባት ባለው ቁርጠኝነት ብርታትን ተመኝተው፣ እግዚአብሔር በቃል ኪዳኑ ደስታን እንዲሰጥ ጸሎታቸውን አቅርበዋል። 

04 September 2021, 16:46