ፈልግ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ “ኢየሱስ ክርስቶስ በመከራ ጊዜ ብቻችን አይተወንም!”

34ኛ ዓለም አቀፍ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን በሁለት የመካከለኛው አውሮፓ አገሮች፣ በሃንጋሪ እና ስሎቫኪያ ውስጥ ያደረጉት ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ በጉብኝታቸው ወቅት ከሁለቱ አገሮች ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናት እና የሐይማኖት መሪዎች ጋር ተገናኝተው በመወያየት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል። በስሎቫኪያ ባደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት ወቅት በዋና ከተማ ብራቲስላቫ የሚገኝ የችግረኛ ቤተሰብ መጠለያ ቤተልሔም ማዕከልን ጎብኝተዋል። በቅድስት “ማዘር” ተሬዛ የቸርነት ሥራ ሚሲዮናዊያን በሚመራ ማዕከል ውስጥ ለሚገኙት ቤተሰቦች ባደረጉት ንግግር፣ ኢየሱስ ክርስቶስ በመከራ ውስጥ የሚገኙትን ብቻቸውን እንደማይተው በመግለጽ አጽናንተዋቸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በስሎቫኪያ ውስጥ ባደረጉት የሐዋርያዊ ጉብኝታቸው ወቅት ለድሆች እና ከማኅበረሰቡ ለተገለሉት በሰጡት ትኩረት፣ በዋና ከተማ ብራቲስላቫ ወደሚገኘውን ቤተልሔም ማዕከል የግል ጉብኝት አድርገዋል። በማዕከሉ በተዘጋጀላቸው መዝገብ ውስጥ ፊርማቸውን ካኖሩ በኋላ በማዕከሉ በጎ ፈቃደኞች የቀረቡ ምስክርነቶችን አዳምጠው አገልግሎታቸውን በማዕከሉ ውስጥ በማበርከት ላይ ለሚገኙ የቸርነት ሥራ ማኅበር እህቶችን አመስግነዋቸዋል። ቅዱስነታቸው የማዕከሉ እህቶችን በጸሎታቸው እንደሚያስታውሷቸው ገልጸው የእመቤታችን ጥበቃን ተመኝተውላቸዋል።

በቅድስት ተሬዛ የቸርነት አገልግሎት ማኅበር የሚመራው የችግረኞች መጠለያ ማዕከሉ አገሪቱ በኮሚኒስት ሥርዓት በምትመራበት እ. አ. አ በ1970ዎቹ እና ሰማንያዎቹ የተቋቋመ መሆኑ ታውቋል። ቤተልሔም የችግረኛ ቤተሰብ መጠለያ ማዕከል በብራቲስላቫ ከተማ ዳርቻ አገሪቱ ከአውስትሪያ ጋር በምትዋሰበት በዳኑቤ ወንዝ ዳርቻ የሚገኝ መንደር እና በአካባቢው 110,000 ነኣዋሪዎች የሚገኙበት መሆኑ ታውቋል።

ሚሲዮናዊያኑ ወደ አካባቢው የመጡት እ. አ. አ በ1997 ዓ. ም ሲሆን፣ በሥፍራው የነበረውን የመዋዕለ ሕጻናት ትምህርት ቤት ወደ መጠለያነት ለውጠው በአካባቢው የነበሩ በርካታ መጠለያ አልባ እና ድሃ ቤተሰቦችን ወደ ማዕከሉ ተቀብለው አገልግሎት መስጠት መጀመራቸው ታውቋል። የቸርነት ሥራ ማኅበር እህቶች በከተማው ውስጥ በመጠለያ እጦት ተቸግረው በየጎዳናው የሚገኙ ቤተሰቦችን ሰብስበው ወደ ማዕከሉ በማምጣት አገልግሎት መስጠት መጀመራቸው ይታወሳል። በአካባቢው የሚገኝ የቅድስት ቤተሰብ ቁምስና መሪ ካህን የሆኑት ክቡር አባ ጁራጅ ቪቴክ፣ የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ እ. አ. አ በ2003 ዓ. ም ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን በስሎቫኪያ ባደረጉበት ወቅት ማዕከሉን መጎብኘታቸውን አስታውሰዋል።

ማዕከሉ ከቁምስናው ጋር ያለው ግንኙነት

ክቡር አባ ጁራጅ፣ ቁምስናቸው በማዕከሉ ለሚገኙ ተረጂዎች ሐዋርያዊ አገልግሎት በማቅረብ ላይ መሆኑን አስረድተዋል። በማዕከሉ አገልግሎት በማበርከት ላይ የሚገኙ እህቶች ወደ ቅድስት ቤተሰብ ቁምስና በመምጣት የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎትን የሚካፈሉ መሆናቸውን አስረድተው፣ የቁምስናው ካኅናትም ወደ ማዕከሉ በመሄድ ሕሙማንን የሚጠይቁ እና ምስጢራትን የሚሰጡ መሆኑን ገልጸዋል። ከዚህም በተጨማሪ የቁምስናው አዳጊ ሕጻናት ወደ ማዕከሉ በመሄድ ለዕኩዮቻቸው ስጦታን በማቅረብ እና በመዝሙርአገልግሎት  የሚያጽናኗቸው መሆኑን ገልጸዋል።

የተቸገሩትን መርዳት

የቅድስት ቤተሰብ ቁምስና መሪ ካኅን ክቡር አባ ጁራጅ እንደገለጹት፣ በማዕከሉ ውስጥ የሚገኙ ተረጂ ቤተሰቦች ከድህነት ሕይወት የሚመጡ በመሆናቸው ከዕለት ቀለብ አንስቶ እስከ ጤና አገልግሎት ድረስ ልዩ ልዩ ሰብዓዊ ዕርዳታዎች የሚያስፈልጋቸው መሆኑን ገልጸዋል። በስሎቫኪያ ዋና ከተማ ብራቲስላቫ ውስጥ የሚታየው የመኖሪያ ቤት እጥረት ከፍተኛ መሆኑን የገለጹት ክቡር አባ ጁራጅ፣ ትክክለኛ መረጃ ባይኖርም ባሁኑ ጊዜ ከ2,000 እስከ 4,000 ድረስ የሚደርሱ መጠለያ አልባ ሰዎች በዋና ከተማ ውስጥ መኖራቸውን ተናግረዋል። በከታማው ውስጥ የሚገኙ መጠለያ አልባ ሰዎች ከመላው የአገሪቱ ክፍሎች የሚመጡ መሆናቸውን አስረድተዋል።

ለር. ሊ. ጳ ፍራንቸስኮስ የተደረገ አቀባበል

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ወደ ስሎቫኪያ ያደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት እጅግ ያስደሰታቸው መሆኑን የተናገሩት ክቡር አባ ጁራጅ ቪቴክ፣ በተለይም ወደ ብራቲስላቫ እና ወደ ቁስናቸው መምጣታቸው ያስደሰታቸው መሆኑን ገልጸዋል። አባ ጁራጅ አክለውም የቁምስናው ምዕመናን እና የአካባቢው ነዋሪዎች፣ ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ተረስቶ ወደቆየው ቁምስናቸው እና አካባቢያቸው ጉብኝት ማድረጋቸው ማመን የሚያስቸግር እጅግ አስደሳች ክስተት እንደነበር መናገራቸውን ገልጸዋል።                

15 September 2021, 17:04